ሐዋርያት ሥራ 10:13-31
ሐዋርያት ሥራ 10:13-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን፥ “አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ርኩስ፥ የሚያጸይፍም ከቶ በልች አላውቅም” አለው። ዳግመኛም፥ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክስ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ይህንም ሦስት ጊዜ አለው፤ ወዲያውኑም ዕቃዉ ወደ ሰማይ ተመለሰ። ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደ ሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር። ተጣርተውም፦ ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፥ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል። ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና።” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና፥ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው። እነርሱም፥ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ በአይሁድም ወገኖች ሁሉ የተመሰከረለት ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት። እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ። በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስም፥ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ። አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፥ “የዛሬ አራት ቀን በዘጠኝ ሰዓት በዚች ሰዓት በቤቴ ስጸልይ የሚያንፀባርቅ ልብስ የለበሰ አንድ ሰው በፊቴ ቆሞ ታየኝ። እንዲህም አለኝ፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ፤ ምጽዋትህም ታሰበልህ።
ሐዋርያት ሥራ 10:13-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኩስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ። ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው” አለው። ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨርቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጕም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለሆንሁ፣ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ።” ጴጥሮስም ወርዶ፣ “እነሆ፤ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ጕዳይ ምንድን ነው?” አላቸው። ሰዎቹ፣ “የመጣነው ቆርኔሌዎስ ከተባለው መቶ አለቃ ዘንድ ነው፤ እርሱም ጻድቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተከበረ ሰው ነው። አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት። ጴጥሮስም ሰዎቹን ሊያስተናግዳቸው ወደ ቤት አስገባቸው። ጴጥሮስም በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ከኢዮጴ የመጡ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ፤ በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር። ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው። ጴጥሮስም እያነጋገረው አብሮት ሲገባ፣ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋር እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል። ስለዚህም በተጠራሁ ጊዜ፣ እነሆ ሳላመነታ መጣሁ፤ እንግዲህ፣ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፤ “ከአራት ቀን በፊት በዚህ ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ሆኜ እጸልይ ነበር፤ ድንገትም ብሩህ ልብስ የለበሰ ሰው መጥቶ በፊቴ ቆመና እንዲህ አለኝ፤ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም ለመታሰቢያነት በእግዚአብሔር ፊት ደርሷል።
ሐዋርያት ሥራ 10:13-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን፦ “ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና” አለ። ደግሞም ሁለተኛ፦ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ፦ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፦ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ፦ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ” አለው። ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ፦ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ” አሉት። እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፦ “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ” ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ፦ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ” አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ “በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና፦ “ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ።
ሐዋርያት ሥራ 10:13-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!” የሚል ድምፅ ሰማ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም! እኔ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ። ደግሞም “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም” የሚል ድምፅ እንደገና ሰማ። ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስ የራእዩ ፍች “ምን ይሆን?” እያለ በሐሳቡ ሲጨነቅ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች በጥያቄ የስምዖንን ቤት አግኝተው በበር ቆመው ነበር፤ ተጣርተውም “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በእንግድነት የሚገኘው እዚህ ነውን?” ብለው ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “እነሆ! ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥና ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለ ሆንኩ ሳታመነታ ከእነርሱ ጋር ሂድ።” ጴጥሮስም ወርዶ ወደ ሰዎቹ ሄደና “እነሆ፥ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ከመቶ አለቃው ከቆርኔሌዎስ ዘንድ ነው፤ እርሱ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ የሚያከብረው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ደግ ሰው ነው፤ አንተን ወደ ቤቱ አስጠርቶ የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ገልጦ ነግሮታል” አሉት። ጴጥሮስም ወደ ቤት አስገባቸውና አስተናገዳቸው፤ ለምኖም አሳደራቸው። በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ በኢዮጴ ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹም አብረውት ሄዱ። በሁለተኛውም ቀን ወደ ቂሳርያ ደረሱ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ እነጴጥሮስን ይጠባበቅ ነበር። ጴጥሮስ ወደ ቤት ሲገባ ቆርኔሌዎስ ወደ እርሱ ቀረበና በእግሩ ሥር ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን “ተነሥ! እኔም እንደ አንተ ሰው ነኝ!” ብሎ አስነሣው። እያነጋገረውም ወደ ውስጥ ሲገባ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው አገኘ። እንዲህም አላቸው፦ “አይሁዳዊ ለሆነ ሰው ከሌላ ሕዝብ ጋር ለመተባበርና ወደ ቤቱም ለመግባት በሃይማኖታችን ሕግ እንደማይፈቀድ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ማንንም ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ እንዳልል እግዚአብሔር ገልጦልኛል። ስለዚህ በተላከብኝ ጊዜ ያለ አንዳች ተቃውሞ መጣሁ፤ እንግዲህ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለ፦ “ከአራት ቀን በፊት ልክ በዚህ ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆ፥ በድንገት አንድ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመ፤ እንዲህም አለኝ፦ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቶአል፤ ለድኾች የምታደርገውም ምጽዋት ታስቦልሃል፤
ሐዋርያት ሥራ 10:13-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ጴጥሮስ ሆይ! ተነሣና አርደህ ብላ፤” የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም፤ አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና፤” አለ። ደግሞም ሁለተኛ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፤” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ በእንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፤ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤” አለው። ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ፤” አሉት። እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፤ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ፤” ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ‘ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው’ እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ” አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው “በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ።