የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 10:1-47

ሐዋርያት ሥራ 10:1-47 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በቂሳርያ፣ “የኢጣሊያ ክፍለ ጦር” በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምጽዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ነበር። አንድ ቀን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” ሲለው በግልጽ አየ። ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኵር ብሎ እያየው፣ “ጌታ ሆይ፤ ምንድን ነው?” አለው። መልአኩም እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ለመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐርጎልሃል። አሁንም ሰዎች ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤ እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፏል።” ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለእርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤ የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው። የተላኩትም ሰዎች በማግስቱም ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ። በዚያን ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤ ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱ ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበርሩ አዕዋፍ ነበሩበት። በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኩስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ። ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው” አለው። ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨርቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጕም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለሆንሁ፣ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ።” ጴጥሮስም ወርዶ፣ “እነሆ፤ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ጕዳይ ምንድን ነው?” አላቸው። ሰዎቹ፣ “የመጣነው ቆርኔሌዎስ ከተባለው መቶ አለቃ ዘንድ ነው፤ እርሱም ጻድቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተከበረ ሰው ነው። አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት። ጴጥሮስም ሰዎቹን ሊያስተናግዳቸው ወደ ቤት አስገባቸው። ጴጥሮስም በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ከኢዮጴ የመጡ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ፤ በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር። ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው። ጴጥሮስም እያነጋገረው አብሮት ሲገባ፣ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋር እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል። ስለዚህም በተጠራሁ ጊዜ፣ እነሆ ሳላመነታ መጣሁ፤ እንግዲህ፣ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፤ “ከአራት ቀን በፊት በዚህ ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ሆኜ እጸልይ ነበር፤ ድንገትም ብሩህ ልብስ የለበሰ ሰው መጥቶ በፊቴ ቆመና እንዲህ አለኝ፤ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም ለመታሰቢያነት በእግዚአብሔር ፊት ደርሷል። ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ እርሱም በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፏል።’ እኔም ወዲያው ላክሁብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ እኛ ሁላችን ጌታ ያዘዘህን ስትነግረን ለመስማት በእግዚአብሔር ፊት አለን።” ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በርግጥ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል። እግዚአብሔር፣ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የላከውም የሰላም የምሥራች መልእክት ይኸው ነው። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በመላው ይሁዳ የሆነውን ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ። “እርሱ በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ላደረገው ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ ደግሞም ሰዎች እርሱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሣው፤ እንዲታይም አደረገው፤ የታየውም ለሁሉ ሰው ሳይሆን፣ ከሙታን ከተነሣ በኋላ አብረነው ለበላንና ለጠጣን፣ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለመረጠን ለእኛ ለምስክሮቹ ነው። ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን እንድንመሰክር እርሱ ራሱ አዘዘን፤ በእርሱም የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ስርየት እንደሚቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” ጴጥሮስ ይህን እየተናገረ ሳለ፣ ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። ከጴጥሮስ ጋር የመጡት፣ ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ ተገረሙ። ይኸውም በልሳን ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ስለ ሰሟቸው ነው። በዚያ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፤ “እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉ፣ እንግዲህ በውሃ እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው ማን ነው?”

ሐዋርያት ሥራ 10:1-47 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በቂ​ሳ​ር​ያም ቆር​ኔ​ሌ​ዎስ የሚ​ባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢጣ​ሊቄ ለሚ​ሉት ጭፍ​ራም የመቶ አለቃ ነበር። እር​ሱም ጻድ​ቅና ከነ​ቤተ ሰቡ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሚ​ፈራ ነበር፤ ለሕ​ዝ​ቡም ብዙ ምጽ​ዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወ​ት​ርም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይጸ​ልይ ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አ​ክም በራ​እይ ከቀኑ በዘ​ጠኝ ሰዓት በግ​ልጥ ታየው፤ ወደ እር​ሱም ገብቶ፥ “ቆር​ኔ​ሌ​ዎስ ሆይ፥” አለው። ወደ​እ​ር​ሱም ተመ​ል​ክቶ ፈራና፥ “አቤቱ፥ ምን​ድን ነው?” አለ፤ መል​አ​ኩም እን​ዲህ አለው፥ “ጸሎ​ት​ህም ምጽ​ዋ​ት​ህም መል​ካም መታ​ሰ​ቢያ ሆኖ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዐር​ጎ​አል። አሁ​ንም ጴጥ​ሮስ የሚ​ባ​ለ​ውን ስም​ዖ​ንን ይጠ​ሩ​ልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎ​ችን ላክ። እር​ሱም ቤቱ በባ​ሕር አጠ​ገብ ባለው በቍ​ር​በት ፋቂው በስ​ም​ዖን ቤት እን​ግ​ድ​ነት ተቀ​ም​ጦ​አል። ልታ​ደ​ር​ገው የሚ​ገ​ባ​ህን እርሱ ይነ​ግ​ር​ሃል።” ያነ​ጋ​ገ​ረ​ውም መል​አክ ከሄደ በኋላ ከሎ​ሌ​ዎቹ ሁለት፥ ከማ​ይ​ለ​ዩት ጭፍ​ሮ​ቹም አንድ ደግ ወታ​ደር ጠራ። ነገ​ሩ​ንም ሁሉ ነግሮ ወደ ኢዮጴ ከተማ ላካ​ቸው። በማ​ግ​ሥ​ቱም ሄደው ወደ ከተ​ማ​ዪቱ በር ደረሱ፤ ጴጥ​ሮ​ስም በቀ​ትር ጊዜ ሊጸ​ልይ ወደ ሰገ​ነት ወጥቶ ነበር። በተ​ራበ ጊዜም ምሳ ሊበላ ወደደ፤ እነ​ር​ሱም እያ​ዘ​ጋጁ ሳሉ ተመ​ስጦ መጣ​በት። ሰማ​ይም ተከ​ፍቶ በአ​ራቱ ማዕ​ዘን የተ​ያዘ እንደ ታላቅ መጋ​ረጃ ያለ ዕቃ ወደ ምድር ሲወ​ርድ አየ። በው​ስ​ጡም አራት እግር ያለው እን​ስሳ ሁሉ፥ አራ​ዊ​ትም፥ የሚ​ን​ቀ​ሳ​ቀ​ስም፥ የሰ​ማ​ይም ወፎች ነበ​ሩ​በት። “ጴጥ​ሮስ ሆይ፥ ተነ​ሥና አር​ደህ ብላ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ጴጥ​ሮስ ግን፥ “አቤቱ፥ ከቶ አይ​ሆ​ንም፤ ርኩስ፥ የሚ​ያ​ጸ​ይ​ፍም ከቶ በልች አላ​ው​ቅም” አለው። ዳግ​መ​ኛም፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ንጹሕ ያደ​ረ​ገ​ውን አንተ አታ​ር​ክስ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ይህ​ንም ሦስት ጊዜ አለው፤ ወዲ​ያ​ው​ኑም ዕቃዉ ወደ ሰማይ ተመ​ለሰ። ጴጥ​ሮ​ስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደ ሆነ ሲያ​ወ​ጣና ሲያ​ወ​ርድ ከቆ​ር​ኔ​ሌ​ዎስ ተል​ከው የመጡ ሰዎች የስ​ም​ዖ​ንን ቤት እየ​ጠ​የቁ በደጅ ቁመው ነበር። ተጣ​ር​ተ​ውም፦ ጴጥ​ሮስ የተ​ባለ ስም​ዖን በእ​ን​ግ​ድ​ነት በዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥ​ሮ​ስም ስለ ታየው ራእይ ሲያ​ወጣ ሲያ​ወ​ርድ መን​ፈስ ቅዱስ እን​ዲህ አለው፥ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈ​ል​ጉ​ሃል። ተነ​ሥና ውረድ፤ ምንም ሳት​ጠ​ራ​ጠር ከእ​ነ​ርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬ​አ​ቸ​ዋ​ለ​ሁና።” ጴጥ​ሮ​ስም ወደ እነ​ዚያ ሰዎች ወረ​ደና፥ “እነሆ፥ የም​ት​ፈ​ል​ጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥ​ታ​ች​ኋል?” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “የመቶ አለቃ ቆር​ኔ​ሌ​ዎስ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሚ​ፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ በአ​ይ​ሁ​ድም ወገ​ኖች ሁሉ የተ​መ​ሰ​ከ​ረ​ለት ነው፤ ቅዱስ መል​አክ ተገ​ልጦ አን​ተን ወደ ቤቱ እን​ዲ​ጠ​ራህ የም​ታ​ስ​ተ​ም​ረ​ው​ንም እን​ዲ​ሰማ አዝ​ዞ​ታል፤” አሉት። እር​ሱም ተቀ​ብሎ አሳ​ደ​ራ​ቸው፤ በማ​ግ​ሥ​ቱም ተነ​ሥቶ አብ​ሮ​አ​ቸው ሄደ፤ በኢ​ዮጴ ከተማ ከሚ​ኖ​ሩት ወን​ድ​ሞ​ችም አብ​ረ​ውት የሄዱ ነበሩ። በማ​ግ​ሥ​ቱም ወደ ቂሳ​ርያ ከተማ ገባ፤ ቆር​ኔ​ሌ​ዎ​ስም ዘመ​ዶ​ቹ​ንና የቅ​ርብ ወዳ​ጆ​ቹን ጠርቶ ይጠ​ብ​ቃ​ቸው ነበር። ጴጥ​ሮ​ስም በገባ ጊዜ ቆር​ኔ​ሌ​ዎስ ተቀ​በ​ለው፤ ከእ​ግሩ በታ​ችም ወድቆ ሰገ​ደ​ለት። ጴጥ​ሮ​ስም፥ “ተነሥ እኔም እንደ አን​ተው ሰው ነኝ” ብሎ አነ​ሣው። ከእ​ር​ሱም ጋር እየ​ተ​ነ​ጋ​ገረ ገባ፤ ወደ እር​ሱም የመጡ ብዙ ሰዎ​ችን አገኘ። ጴጥ​ሮ​ስም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ለአ​ይ​ሁ​ዳዊ ሰው ሄዶ ከባ​ዕድ ወገን ጋር መቀ​ላ​ቀል እን​ደ​ማ​ይ​ገ​ባው ታው​ቃ​ላ​ችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማን​ንም ቢሆን እን​ዳ​ል​ጸ​የ​ፍና ርኩስ ነው እን​ዳ​ልል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አሳ​የኝ። አሁ​ንም ስለ ላካ​ች​ሁ​ብኝ ሳል​ጠ​ራ​ጠር ወደ እና​ንተ መጣሁ፤ በምን ምክ​ን​ያት እንደ ጠራ​ች​ሁኝ እጠ​ይ​ቃ​ች​ኋ​ለሁ።” ቆር​ኔ​ሌ​ዎ​ስም እን​ዲህ አለው፥ “የዛሬ አራት ቀን በዘ​ጠኝ ሰዓት በዚች ሰዓት በቤቴ ስጸ​ልይ የሚ​ያ​ን​ፀ​ባ​ርቅ ልብስ የለ​በሰ አንድ ሰው በፊቴ ቆሞ ታየኝ። እን​ዲ​ህም አለኝ፦ ቆር​ኔ​ሌ​ዎስ ሆይ፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ጸሎ​ትህ ተሰማ፤ ምጽ​ዋ​ት​ህም ታሰ​በ​ልህ። አሁ​ንም ወደ ኢዮጴ ከተማ ላክና በባ​ሕር አቅ​ራ​ቢያ ባለ​ችው በቍ​ር​በት ፋቂው በስ​ም​ዖን ቤት የሚ​ኖ​ረ​ውን ጴጥ​ሮስ የተ​ባ​ለ​ውን ስም​ዖ​ንን ይጥ​ሩ​ልህ፤ እርሱ መጥቶ የም​ት​ድ​ን​በ​ትን ይነ​ግ​ር​ሃል። ስለ​ዚ​ህም ወዲ​ያ​ውኑ ወደ አንተ ላክሁ፤ ወደ እኛ በመ​ም​ጣ​ት​ህም መል​ካም አደ​ረ​ግህ፤ አሁ​ንም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያዘ​ዘ​ህን ሁሉ ልን​ሰማ እነሆ፥ እኛ ሁላ​ችን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በዚህ አለን።” ጴጥ​ሮ​ስም አፉን ከፈ​ተና እን​ዲህ አለ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለሰው ፊት እን​ደ​ማ​ያ​ዳላ በእ​ው​ነት አየሁ። ነገር ግን በሕ​ዝብ ሁሉ ዘንድ እር​ሱን የሚ​ፈ​ራና እው​ነ​ትን የሚ​ያ​ደ​ርግ በእ​ርሱ ዘንድ የተ​ወ​ደደ ነው። ቃሉን ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ላከ፤ በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስም ሰላ​ምን ነገ​ራ​ቸው፤ እር​ሱም የሁሉ ገዢ ነው። ዮሐ​ንስ ከሰ​በ​ከው ጥም​ቀት በኋላ ከገ​ሊላ ጀምሮ በይ​ሁዳ የሆ​ነ​ውን ነገር ሁሉ እና​ንተ ራሳ​ችሁ ታው​ቃ​ላ​ችሁ። ስለ ናዝ​ሬቱ ስለ ኢየ​ሱስ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በመ​ን​ፈስ ቅዱስ በኀ​ይ​ልም እንደ ቀባው፥ እየ​ዞ​ረም መል​ካም እንደ አደ​ረገ፥ ሰይ​ጣን ያሸ​ነ​ፋ​ቸ​ው​ንም እንደ ፈወሰ ታው​ቃ​ላ​ችሁ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከእ​ርሱ ጋር ነበ​ርና። በይ​ሁ​ዳና በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ባደ​ረ​ገ​ውም ሁሉ እኛ ምስ​ክ​ሮች ነን፤ እር​ሱ​ንም በዕ​ን​ጨት ላይ ሰቅ​ለው ገደ​ሉት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን በሦ​ስ​ተ​ኛው ቀን ከሙ​ታን ለይቶ አስ​ነ​ሣው፤ በግ​ልጥ እን​ዲ​ታ​ይም አደ​ረ​ገው። ይኸ​ውም ለሕ​ዝቡ ሁሉ አይ​ደ​ለም፤ ነገር ግን አስ​ቀ​ድሞ ለመ​ረ​ጣ​ቸ​ውና ምስ​ክ​ሮች ለሚ​ሆ​ኑት ብቻ ነው እንጂ፤ የመ​ረ​ጣ​ቸው የተ​ባ​ል​ንም እኛ ነን፤ ከሙ​ታ​ንም ተለ​ይቶ ከተ​ነሣ በኋላ ከእ​ርሱ ጋር የበ​ላን የጠ​ጣ​ንም እኛ ነን። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ በሕ​ያ​ዋ​ንና በሙ​ታን ላይ ፈራጅ ሆኖ የተ​ሾመ እርሱ እንደ ሆነ ለሕ​ዝብ እና​ስ​ተ​ምር ዘንድ አዘ​ዘን። ለሚ​ያ​ም​ኑ​በ​ትም ሁሉ ኀጢ​አ​ታ​ቸው በስሙ እን​ደ​ሚ​ሰ​ረ​ይ​ላ​ቸው ነቢ​ያት ሁሉ ምስ​ክ​ሮቹ ናቸው።” ጴጥ​ሮ​ስም ይህን ነገር ሲነ​ግ​ራ​ቸው ይህን ትም​ህ​ርት በሰ​ሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መን​ፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴ​ጥ​ሮስ ጋር የመጡ ከአ​ይ​ሁድ ወገን የሆኑ ምእ​መ​ናን ሁሉ ደነ​ገጡ፤ የመ​ን​ፈስ ቅዱስ ጸጋ በአ​ሕ​ዝብ ላይ ወር​ዶ​አ​ልና። በልዩ ልዩ ሀገር ቋንቋ ሲና​ገሩ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ሲያ​መ​ሰ​ግኑ ሰም​ተ​ዋ​ቸ​ዋ​ልና። ጴጥ​ሮ​ስም፥ “እንደ እኛ መን​ፈስ ቅዱ​ስን ከተ​ቀ​በሉ በኋላ እን​ግ​ዲህ በውኃ እን​ዳ​ይ​ጠ​መቁ ውኃን ሊከ​ለ​ክ​ላ​ቸው የሚ​ችል ማነው?” አለ።

ሐዋርያት ሥራ 10:1-47 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፦ “ቆርኔሌዎስ ሆይ” የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ፦ “ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው?” አለ። መልአኩም አለው፦ “ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ። እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።” የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው። እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን፦ “ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና” አለ። ደግሞም ሁለተኛ፦ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ፦ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፦ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ፦ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ” አለው። ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ፦ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ” አሉት። እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፦ “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ” ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ፦ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ” አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ “በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና፦ “ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ። እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ እንግድነት ተቀምጦአል” አለኝ። ስለዚህ ያን ጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፥ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን። ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ። የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ “እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?” አለ።

ሐዋርያት ሥራ 10:1-47 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በቂሳርያ የሚኖር ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሮማውያን ጦር ሠራዊት ሥር “የኢጣልያ ብርጌድ” በሚባለው ውስጥ የመቶ አለቃ ነበር። እርሱ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ሰው ነበረ፤ ለድኾችም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር ይጸልይ ነበር። አንድ ቀን በዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባና “ቆርኔሌዎስ!” ብሎ ሲጠራው በራእይ በግልጥ ታየው። ትኲር ብሎ ወደ መልአኩ ተመለከተና በመደንገጥ “ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?” አለ። መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህና ለድኾች የምታደርገው ምጽዋት መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል፤ አሁንም ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ላክና ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ አሁን በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጦአል።” ይህን የነገረው መልአክ ተለይቶት በሄደ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ከአገልጋዮቹ ሁለቱንና የእርሱ ክፍል ከሆኑት ወታደሮች እግዚአብሔርን የሚፈራውን አንዱን ጠራና፥ ሁሉንም ነገር ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው። በማግስቱ እነርሱ ሄደው ወደ ከተማው ሲቀርቡ ስድስት ሰዓት ገደማ ጴጥሮስ ወደነበረበት ቤት ሰገነት ሊጸልይ ወጣ። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ራበውና አንዳች ነገር መብላት ፈለገ፤ ምሳ በመዘጋጀት ላይ እንዳለም በተመስጦ ራእይ አየ። ያየውም ራእይ ሰማይ ተከፍቶ በአራት ማእዘን የተያዘ ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወደ ምድር ሲወርድ ነው። በዚያም ላይ ልዩ ልዩ እንስሳት በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችና በሰማይ የሚበርሩ ወፎች ነበሩበት። በዚያን ጊዜ “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!” የሚል ድምፅ ሰማ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም! እኔ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ። ደግሞም “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም” የሚል ድምፅ እንደገና ሰማ። ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስ የራእዩ ፍች “ምን ይሆን?” እያለ በሐሳቡ ሲጨነቅ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች በጥያቄ የስምዖንን ቤት አግኝተው በበር ቆመው ነበር፤ ተጣርተውም “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በእንግድነት የሚገኘው እዚህ ነውን?” ብለው ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “እነሆ! ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥና ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለ ሆንኩ ሳታመነታ ከእነርሱ ጋር ሂድ።” ጴጥሮስም ወርዶ ወደ ሰዎቹ ሄደና “እነሆ፥ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ከመቶ አለቃው ከቆርኔሌዎስ ዘንድ ነው፤ እርሱ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ የሚያከብረው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ደግ ሰው ነው፤ አንተን ወደ ቤቱ አስጠርቶ የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ገልጦ ነግሮታል” አሉት። ጴጥሮስም ወደ ቤት አስገባቸውና አስተናገዳቸው፤ ለምኖም አሳደራቸው። በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ በኢዮጴ ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹም አብረውት ሄዱ። በሁለተኛውም ቀን ወደ ቂሳርያ ደረሱ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ እነጴጥሮስን ይጠባበቅ ነበር። ጴጥሮስ ወደ ቤት ሲገባ ቆርኔሌዎስ ወደ እርሱ ቀረበና በእግሩ ሥር ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን “ተነሥ! እኔም እንደ አንተ ሰው ነኝ!” ብሎ አስነሣው። እያነጋገረውም ወደ ውስጥ ሲገባ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው አገኘ። እንዲህም አላቸው፦ “አይሁዳዊ ለሆነ ሰው ከሌላ ሕዝብ ጋር ለመተባበርና ወደ ቤቱም ለመግባት በሃይማኖታችን ሕግ እንደማይፈቀድ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ማንንም ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ እንዳልል እግዚአብሔር ገልጦልኛል። ስለዚህ በተላከብኝ ጊዜ ያለ አንዳች ተቃውሞ መጣሁ፤ እንግዲህ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለ፦ “ከአራት ቀን በፊት ልክ በዚህ ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆ፥ በድንገት አንድ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመ፤ እንዲህም አለኝ፦ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቶአል፤ ለድኾች የምታደርገውም ምጽዋት ታስቦልሃል፤ እንግዲህ ወደ ኢዮጴ መልእክተኛ ላክና ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጦአል፤’ ስለዚህ ወዲያውኑ መልእክተኞች ወደ አንተ ላክሁ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል፤ እንግዲህ እግዚአብሔር እንድትናገር ያዘዘህን ሁሉ ለመስማት እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት እዚህ ተሰብስበናል።” ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፦ “በእውነት እግዚአብሔር ሰውን ከሰው እንደማያበላልጥ አስተዋልኩ፤ የማንኛውም አገር ሰው ቢሆን እግዚአብሔርን የሚፈራና ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግ ከሆነ እግዚአብሔር ይቀበለዋል። እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ቃሉን መላኩ የታወቀ ነው፤ በሁሉ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ሰላምን እየሰበከ የመጣውም ለእነርሱ ነው። ዮሐንስ ስለ ጥምቀት ከሰበከበት ጊዜ ጀምሮ ከገሊላ አንሥቶ በይሁዳ ምድር ሁሉ የሆነውን ነገር ታውቃላችሁ። “ደግሞም እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ እንደ ቀባውና ኀይልም እንደ ሰጠው ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ እርሱን መልካም ነገርን እያደረገና በዲያብሎስ የተያዙትን ሁሉ እየፈወሰ ተዘዋወረ። “በይሁዳ ገጠርና በኢየሩሳሌም ከተማ እርሱ ስላደረገው ነገር ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ እርሱን ግን በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። ነገር ግን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን ከሞት አስነሣውና እንዲገለጥ አደረገው። የተገለጠውም አስቀድሞ በእግዚአብሔር ለተመረጡት ምስክሮች ነው እንጂ ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፤ እርሱ ከሞት ከተነሣ በኋላ እኛ ከእርሱ ጋር አብረን የበላንና የጠጣን ምስክሮቹ ነን፤ ይህን ነገር ለሕዝቡ እንድናበሥር እርሱ በሕያዋንና በሙታን ላይ እንዲፈርድ በእግዚአብሔር የተሠየመ መሆኑን እንድንመሰክር አዞናል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” ጴጥሮስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ ቃሉን በሰሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስ ጋር የመጡት ከተገረዙት አይሁድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለአሕዛብ መንፈስ ቅዱስን እንደ ሰጣቸው ባዩ ጊዜ ተደነቁ። ለአሕዛብ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተሰጠ ያወቁትም አሕዛብ በሌሎች ቋንቋዎች ሲናገሩና እግዚአብሔርን በምስጋና ሲያከብሩ በመስማታቸው ነው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፤ ታዲያ፥ እነርሱ በውሃ እንዳይጠመቁ ማን ይከለክላቸዋል?” ሲል ተናገረ።

ሐዋርያት ሥራ 10:1-47 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ “ጌታ ሆይ! ምንድነው?” አለ። መልአኩም አለው “ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ። እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ በእንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።” የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው፤ ወደ ኢዮጴም ላካቸው። እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ሰገነት ወጣ። ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሣና አርደህ ብላ፤” የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም፤ አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና፤” አለ። ደግሞም ሁለተኛ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፤” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ በእንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፤ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤” አለው። ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ፤” አሉት። እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፤ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ፤” ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ‘ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው’ እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ” አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው “በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ። እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቁርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ በእንግድነት ተቀምጦአል፤’ አለኝ። ስለዚህ ያንጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።” ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእውነት አስተዋልሁ። የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፤ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው፤ ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ “እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውሃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?” አለ።