3 ዮሐንስ 1:1-14
3 ዮሐንስ 1:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሽማግሌው በእውነት እኔ ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ። ወዳጅ ሆይ! ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ። ወንድሞች መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና። ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም። ወዳጅ ሆይ! ምንም እንግዶች ቢሆኑ፥ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ፤ እነርሱም በማኅበር ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳ መልካም ታደርጋለህ፤ ከአሕዛብ አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጥተዋልና። እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል። ወደ ቤተ ክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራፊስ አይቀበለንም። ስለዚህ እኔ ብመጣ፥ በእኛ ላይ በክፉ ቃል እየለፈለፈ የሚያደርገውን ሥራውን አሳስባለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሉአቸውም የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል። ወዳጅ ሆይ! በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል። በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው፤ ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። ለድሜጥሮስ ሁሉ ይመሰክሩለታል፤ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም ደግሞ እንመሰክርለታለን፤ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም፤ ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አፍ ለአፍም እንነጋገራለን።
3 ዮሐንስ 1:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሽማግሌው፤ በእውነት ለምወድደው ለውድ ወዳጄ ለጋይዮስ፤ ወዳጅ ሆይ፤ ነፍስህ በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለች ሁሉ መልካም ጤንነት እንዲኖርህና በነገር ሁሉ እንዲሳካልህ እጸልያለሁ። ለእውነት ታማኝ እንደ ሆንህና የምትመላለሰውም በእውነት እንደ ሆነ አንዳንድ ወንድሞች መጥተው ስለ አንተ ሲመሰክሩልኝ እጅግ ደስ አለኝ። ልጆቼ በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም። ወዳጅ ሆይ፤ ለአንተ እንግዶች ቢሆኑም እንኳ፣ ለወንድሞች በምታደርገው ነገር ሁሉ ታማኝ ነህ። እነርሱ አንተ ስላለህ ፍቅር በቤተ ክርስቲያን ፊት መስክረዋል፤ በመንገዳቸውም እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ ብትረዳቸው መልካም ታደርጋለህ፤ ስለ ስሙ የወጡት ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ ነውና። እንግዲህ አብረን ለእውነት እንድንሠራ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ልናስተናግድ ይገባናል። ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ መሆን የሚወድደው ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። ስለዚህ እኔ ከመጣሁ እርሱ በክፉ ቃላት ስማችንን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሁሉ ይፋ አወጣለሁ፤ ይህም አልበቃ ብሎት ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሏቸው የሚፈልጉትን ይከለክላቸዋል፤ ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል። ወዳጅ ሆይ፤ መልካም የሆነውን እንጂ ክፉውን አትምሰል። መልካም የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው። ክፉ የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። ለድሜጥሮስ፣ ሰው ሁሉ ይመሰክርለታል፤ እውነት ራሷም ትመሰክርለታለች፤ እኛ ደግሞ እንመሰክርለታለን፤ እናንተም ምስክርነታችን እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። የምጽፍልህ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በቀለምና በብርዕ እንዲሆን አልፈልግም። በቅርቡ ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ፊት ለፊትም እንነጋገራለን።
3 ዮሐንስ 1:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሽማግሌው በእውነት እኔ ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ። ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ። ወንድሞች መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና። ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም። ወዳጅ ሆይ፥ ምንም እንግዶች ቢሆኑ፥ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ፥ እነርሱም በማኅበር ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳ መልካም ታደርጋለህ፤ ከአሕዛብ አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጥተዋልና። እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል። ወደ ቤተ ክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። ስለዚህ፥ እኔ ብመጣ፥ በእኛ ላይ በክፉ ቃል እየለፈለፈ የሚያደርገውን ሥራውን አሳስባለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፥ ሊቀበሉአቸውም የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል። ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል። በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው፤ ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። ለድሜጥሮስ ሁሉ ይመሰክሩለታል፥ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም ደግሞ እንመሰክርለታለን፥ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም፤ ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አፍ ለአፍም እንነጋገራለን።
3 ዮሐንስ 1:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በእውነት ለማፈቅረው፥ ለተወደደው ጋይዮስ፥ ከእኔ ከሽማግሌው የተላከ መልእክት፦ ወዳጄ ሆይ! ኑሮህ ሁሉ እንዲሳካልህ፥ ጤንነት እንዲኖርህና እንዲሁም የመንፈስ እርካታ እንድታገኝ እመኝልሃለሁ። ለእውነት ታማኝነትህንና በእውነትም መኖርህን አንዳንድ ክርስቲያን ወንድሞች መጥተው በነገሩኝ ጊዜ በጣም ደስ ተሰኘሁ። ልጆቼ በእውነት እየተመላለሱ መኖራቸውን ከመስማት የበለጠ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። ወዳጄ ሆይ! ለአንተ እንግዶች ቢሆኑም እንኳ ለወንድሞች ታማኝ አገልግሎት ትሰጣለህ። እነርሱም ስለ አደረግህላቸው የፍቅር ሥራ በማኅበረ ምእመናን ፊት መስክረዋል፤ አሁንም እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ በጒዞአቸው ብትረዳቸው መልካም ነው። እነርሱ ክርስቶስን ለማገልገል ሲወጡ ከአሕዛብ ምንም ርዳታ አልተቀበሉም። የእውነት ሥራ ተካፋዮች እንድንሆን እንደእነዚህ ያሉትን ሰዎች መርዳት አለብን። ከዚህ በፊት ለቤተ ክርስቲያን ደብዳቤ ጽፌአለሁ፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን መሪ መሆን የሚፈልገው ዲዮትሬፊስ አሳቤን አልተቀበለም። ስለዚህ ወደ እናንተ ስመጣ እርሱ እየሰደበንና እያዋረደን ያደረገውን ክፉ ሥራ ሁሉ ለሁሉም እናገራለሁ፤ ይህም ሳይበቃው ቀርቶ፤ እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም። ሌሎችም እንዳይቀበሉአቸው ይከለክላል። ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል። ወዳጄ ሆይ! ደጉን ምሰል እንጂ ክፉውን አትምሰል። ደግ ሥራ የሚሠራ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። ክፉ ሥራ የሚሠራ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። ለድሜጥሮስ ሰው ሁሉ በመልካም ይመሰክርለታል። እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች። እኛም እንመሰክርለታለን፤ የእኛም ምስክርነት እውነት መሆኑን ታውቃለህ። ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን በደብዳቤ ልገልጽልህ አልፈልግም። በቅርቡ ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ ቃል በቃል እንነጋገራለን።
3 ዮሐንስ 1:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሽማግሌው፥ በእውነት ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ። ወዳጄ ሆይ! በመንፈስ እንዳደግህ ሁሉ፥ በነገር ሁሉ እንዲሳካልህና በመልካም ጤንነት እንድትኖር እጸልያለሁ። ወንድሞች መጥተው በአንተ ስላለው እውነትና አንተም በእውነት እንደምትመላለስ ሲመሰክሩልኝ እጅግ ደስ አለኝ። ልጆቼ በእውነት እንደሚመላለሱ ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም። ወዳጄ ሆይ! ምንም እንኳ እንግዶች ቢሆኑም ለወንድሞች የምታደርገውን ነገር ሁሉ በታማኝነት ታደርጋለህ፤ እነርሱም በቤተ ክርስቲያን ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳቸው መልካም ታደርጋለህ፤ ስለ ስሙ ብለው፥ ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ ወጥተዋልና። ስለዚህ የእውነት የሥራ ተባባሪዎች እንድንሆን እንደነዚህ ያሉትን ልንቀበል ይገባናል። ለቤተ ክርስቲያን አንድ ነገር ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ ለመሆን የሚፈልገው ዲዮጥራፊስ አልተቀበለንም። ስለዚህ እኔ ከመጣሁ፥ ስለ እኛ የተናገረውን ክፉ ቃል፥ የሠራውን ሥራ አሳስበዋለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሉአቸው የሚፈልጉትን ይከለክላቸዋል፥ ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል። ወዳጄ ሆይ! መልካሙን እንጂ ክፉን አትምሰል። መልካም የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። ድሜጥሮስ በሁሉም ተመስክሮለታል፤ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም እንመሰክርለታለን፤ ምስክርነታችን ደግሞ እውነት እንደሆነ ታውቃለህ። የምጽፈው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ነገር ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወደድሁም፤ ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ፊት ለፊት እንነጋገራለን።