2 ሳሙኤል 7:18-29
2 ሳሙኤል 7:18-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ንጉሡ ዳዊትም ገባ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፥ “ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህን ያህል የወደድኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እኔ በፊትህ እጅግ ታናሽ ስሆን ስለ ባሪያህ ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድን ነው? ለባሪያህም ታስታውቀው ዘንድ ስለ ቃልህ ምክንያትና እንደ ልብህ አሳብ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ አደረግህ። ስለዚህም አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እንዳንተ ያለ የለምና፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለምና አንተ ታላቅ ነህ። ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ታላቅ ስምን ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና ሰፈሮቻቸውን በመበተን ከግብፅ በተቤዠኸው ሕዝብህ ፊት ታምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ መራው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘለዓለም ሕዝብ አድርገህ አዘጋጅተኸዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነሃቸዋል። አቤቱ ሁሉን የምትገዛ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የተናገርኸውን ለዘለዓለም አጽናው፤ አሁንም እንደ ተናገርህ አድርግ። ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሁን። አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን ጆሮ ከፈትህ። አንተ፦ እኔ ቤት እሠራልሃለሁ አልህ፤ ስለዚህም ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ አሰበ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አሁንም አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም እውነት ነው፤ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተናግረሃልና አሁን እንግዲህ ለዘለዓለም በፊትህ ይሆን ዘንድ የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘለዓለም ይባረክ።”
2 ሳሙኤል 7:18-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ አንተ ግን ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው? “ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህና! ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል። “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! ከቶ የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። “ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፣ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፣ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክታቸውን ከፊቱ አሳድዶ ታላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብፅም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ? ሕዝብህን እስራኤልን ለዘላለሙ ያንተው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል። “አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም ጠብቅለት፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ ስለዚህ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሆናል፤ ሰዎችም፣ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ። የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። “አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለባሪያህ ገልጸህለታል። ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ በልቡ ደፈረ። ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል፤ በፊትህ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር፣ አሁንም የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ። ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረካል።”
2 ሳሙኤል 7:18-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፦ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድር ነው? ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፥ ስለ ባሪያህም ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፥ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድን ነው? ለባሪያህም ታስታውቀው ዘንድ ስለ ቃልህ ምክንያትና እንደ ልብህ አሳብ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ አደረግህ። ስለዚህም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ የለምና፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለምና አንተ ታላቅ ነህ። ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ በአሕዛብና በአምላኮቻቸውም ፊት ከግብጽ በተቤዠው ሕዝብ ፊት ተአምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ሄደለት እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፥ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነሃቸዋል። አቤቱ አምላክ ሆይ፥ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የተናገርኸውን ለዘላለም አጽናው፥ እንደ ተናገርህም አድርግ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሁን፥ የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን። አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ፦ እኔ ቤት እሠራልሃለሁ ብለህ ለባሪያህ ገልጠሃልና ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ ደፈረ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አሁንም አንተ አምላክ ነህ፥ ቃልህም እውነት ነው፥ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተናግረሃልና አሁን እንግዲህ ለዘላለም በፊትህ ይሆን ዘንድ የባሪያህን ቤት፥ እባክህ፥ ባርክ፥ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረክ።
2 ሳሙኤል 7:18-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝ፤ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤስ ምንድን ነው? እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህም በዐይንህ ፊት ያነሰ ሆኖ አሁንም የበለጠ ነገር እያደረግህ ነው፤ ስለ ባሪያህ ልጆች ለሚመጡት ዘመናት ብዙ የተስፋ ቃል ተናግረሃል፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህ ለሰው ሁሉ የተለመደ ድርጊትህ ነውን? እንግዲህ ምን ልልህ እችላለሁ? እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እኔን ባሪያህን ታውቀኛለህ። ይህን ታላቅ ነገር በቃልህ መሠረትና እንደ ልብህ ፈቃድ ያደረግኸው አገልጋይህ ያውቅ ዘንድ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ ታላቅ ነህ፤ እንደ አንተ ማንም የለም፤ በሰማነው መሠረት ከአንተ በቀር አምላክ የለም። ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ያድን ዘንድ፥ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያደርግ ዘንድ፥ ሕዝቦችንና አማልክቶቻቸውን በፊታቸው ያስወግድ ዘንድ እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት እንዳዳነው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? እስራኤልንም ለዘለዓለም ሕዝብህ አደረግህ፤ ጌታ ሆይ፥ አንተም አምላካቸው ሆንክ። “አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ስለ እኔና ስለ ዘሮቼ የተናገርከውን የተስፋ ቃል ሁሉ ለዘለዓለም ፈጽም፤ ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሆን ዘንድ የተናገርከውን ፈጽም፤ ሰዎችም ልዑል እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይላሉ። የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ለአገልጋይህ ቤት እሠራለሁ ብለህ ስለ ገለጥክለት አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት አግኝቶአል። “አሁንም ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህ ታማኝ ነው፤ እነሆ፥ አሁንም ይህን መልካም የተስፋ ቃል ለአገልጋይህ ሰጥተሃል። በፊትህ ለዘለዓለም ይኖር ዘንድ የአገልጋይህን ቤት ለመባረክ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ በበረከትህ እንደ ተናገርክ የአገልጋይህ ቤት ለዘለዓለም የተባረከ ይሁን።”
2 ሳሙኤል 7:18-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በጌታ ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድንነው? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ አንተ ግን ስለ ወደ ፊቱ የአገልጋይህ ቤት ተናገርህ፤ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው? ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አገልጋይህን አንተ ታውቀዋለህና! ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ አገልጋይህንም እንዲያውቀው አደረግህ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ታላቅ ነህ! የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሮአችን እንደሰማነው ሁሉ፥ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፥ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፥ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክቶቻቸውን ከፊቱ አሳዶ ታላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብጽም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ? ሕዝብህን እስራኤልን ለዘለዓለም ያንተው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ ጌታ ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል። አሁንም ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአገልጋይህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘለዓለም ጠብቅለት፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ ስለዚህ ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሆናል፤ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይባላል። የአገልጋይህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለአገልጋይህ ገልጸህለታል። ስለዚህ አገልጋይህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት አግኝቶአል። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንንም መልካም የተስፋ ቃል ለአገልጋይህ ሰጥተሃል። በፊትህ ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር፥ አሁንም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የአገልጋይህ ቤት ለዘለዓለም ይባረክ።”