ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7
7
ናታን ለዳዊት የተናገረው ቃል
(1ዜ.መ. 17፥1-15)
1እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉ ስለ ጠበቀው ንጉሥ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በሰላም ይኖር ነበር። 2ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩ ናታንን “እነሆ እኔ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል!” አለው።
3ናታንም “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ በልብህ ያሰብከውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት። 4ነገር ግን በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ናታንን እንዲህ አለው፤ 5“ሂድና ለአገልጋዬ ለዳዊት እኔ ስለ እርሱ የምለውን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ ነህን? 6የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ በመታደግ ካዳንኩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በድንኳን ውስጥ ሆኜ በየስፍራው ስዘዋወር ኖርኩ እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም፤ 7ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው መሪዎች መካከል በሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቤት እንዲሠራልኝ የጠየቅሁት አለን?’
8“ስለዚህም ለአገልጋዬ ለዳዊት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ አንተን የበግ መንጋ ከምትጠብቅበት መስክ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ፤ 9በሄድክበት ስፍራ ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርኩ፤ ወደፊትም በተራመድህ መጠን ጠላቶችህን ድል አደረግሁልህ፤ ገና ደግሞ በዓለም እንደ ታወቁት ታላላቅ መሪዎች ዝነኛ አደርግሃለሁ። 10-11ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ አዘጋጅቴ በራሳቸው ቦታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ለእነርሱ መሳፍንትን ከሾምኩበት ጊዜ ጀምሮ ክፉ አድራጊዎች ቀድሞ ያደርጉት እንደ ነበረው አያስጨንቋቸውም፤ አንተንም ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ከቤትህ አልጋህን የሚወርሱ ልጆች እተካልሃለሁ ብሎ ይገልጥልሃል። 12ዘመንህ ተፈጽሞ ከቀድሞ አባቶችህ ጋር በምታርፍበት ጊዜ ከአብራክህ የሚወጣውን ልጅህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ የእርሱንም መንግሥት አጸናለሁ። #መዝ. 89፥3-4፤ 132፥11፤ ዮሐ. 7፥42፤ ሐ.ሥ. 2፥30። 13ለስሜ መጠሪያ ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘለዓለም አጸናለሁ። 14እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል፤ ስሕተት በሚፈጽምበትም ጊዜ አባት ልጁን እንደሚቀጣ እቀጣዋለሁ፤ #መዝ. 89፥26-27፤ 2ቆሮ. 6፥18፤ ዕብ. 1፥5። 15ይሁን እንጂ በእርሱ ቦታ አንተ ትነግሥ ዘንድ ባስወገድኩት በሳኦል ላይ እንዳደረግሁ ዘለዓለማዊ ፍቅሬን ከልጅህ አላርቅም። 16ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ይጠነክራል፤ ዙፋንህም ለዘለዓለም የጸና ይሆናል።’ ” #መዝ. 89፥36-37።
17በዚህም ቃልና ራእይ ሁሉ መሠረት ናታን ለዳዊት ገለጠለት።
ዳዊት ለእግዚአብሔር ያቀረበው የምስጋና ጸሎት
(1ዜ.መ. 17፥16-27)
18ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝ፤ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤስ ምንድን ነው? 19እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህም በዐይንህ ፊት ያነሰ ሆኖ አሁንም የበለጠ ነገር እያደረግህ ነው፤ ስለ ባሪያህ ልጆች ለሚመጡት ዘመናት ብዙ የተስፋ ቃል ተናግረሃል፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህ ለሰው ሁሉ የተለመደ ድርጊትህ ነውን? 20እንግዲህ ምን ልልህ እችላለሁ? እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እኔን ባሪያህን ታውቀኛለህ። 21ይህን ታላቅ ነገር በቃልህ መሠረትና እንደ ልብህ ፈቃድ ያደረግኸው አገልጋይህ ያውቅ ዘንድ ነው። 22እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ ታላቅ ነህ፤ እንደ አንተ ማንም የለም፤ በሰማነው መሠረት ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 23ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ያድን ዘንድ፥ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያደርግ ዘንድ፥ ሕዝቦችንና አማልክቶቻቸውን በፊታቸው ያስወግድ ዘንድ እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት እንዳዳነው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? #ዘዳ. 4፥34። 24እስራኤልንም ለዘለዓለም ሕዝብህ አደረግህ፤ ጌታ ሆይ፥ አንተም አምላካቸው ሆንክ።
25-26“አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ስለ እኔና ስለ ዘሮቼ የተናገርከውን የተስፋ ቃል ሁሉ ለዘለዓለም ፈጽም፤ ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሆን ዘንድ የተናገርከውን ፈጽም፤ ሰዎችም ልዑል እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይላሉ። የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። 27የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ለአገልጋይህ ቤት እሠራለሁ ብለህ ስለ ገለጥክለት አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት አግኝቶአል።
28“አሁንም ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህ ታማኝ ነው፤ እነሆ፥ አሁንም ይህን መልካም የተስፋ ቃል ለአገልጋይህ ሰጥተሃል። 29በፊትህ ለዘለዓለም ይኖር ዘንድ የአገልጋይህን ቤት ለመባረክ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ በበረከትህ እንደ ተናገርክ የአገልጋይህ ቤት ለዘለዓለም የተባረከ ይሁን።”
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997