2 ሳሙኤል 7:1-11
2 ሳሙኤል 7:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹን ሁሉ ባወረሰው ጊዜ፥ ንጉሡ ነቢዩ ናታንን፥ “እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጣለች” አለው። ናታንም ንጉሡን፥ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና፥ ሂድና በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው። በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ፤ እንዲህም አለው፦ “ሂድ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድና እመላለስ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና፥ ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ ስለምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው፦ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፤ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ስምህን ታላቅ አደረግሁ። ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርጋለሁ፤ እተክላቸውማለሁ፤ ብቻቸውን ይቀመጣሉ፤ ከዚያም በኋላ የሚጠራጠሩት የለም፤ እንደ ቀድሞው ዘመን የኀጢአት ልጅ መከራ አያጸናባቸውም። በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆችን በሾምሁ ጊዜ ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እንደምትሠራለት ይነግርሃል፤ እሠራለታለሁ ብለሃልና።
2 ሳሙኤል 7:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣ ንጉሡ ነቢዩ ናታንን፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። ናታንም፣ ንጉሡን “እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ስለ ሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት። በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን እንዲህ ሲል መጣ፤ “ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን፣ ‘እንዲህ ብለህ ንገረው፤ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ ነህን? በለው። እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። በእስራኤል ሕዝብ መካከል ባለፍሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው ነገዶች “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም” ያልሁት አለን?’ “አሁንም ባሪያዬ ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋራ ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው፣ ከእንግዲህ በኋላም እንዳይናወጡ ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጣቸዋለሁ። ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ክፉዎች ከእንግዲህ አይጨቍኗቸውም፤ ለሕዝቤ ለእስራኤልም መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉበትም፤ እንዲሁም ከጠላቶችህ ሁሉ እጠብቅሃለሁ። “ ‘እግዚአብሔር ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤
2 ሳሙኤል 7:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ባሳረፈው ጊዜ፥ ንጉሡ ነቢዩን ናታንን፦ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ ተቀመጠ እይ አለው። ናታንም ንጉሡን፦ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ አለው። በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው፦ ሂድ፥ ለባሪዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፥ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፥ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ። ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፥ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፥ ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል።
2 ሳሙኤል 7:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉ ስለ ጠበቀው ንጉሥ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በሰላም ይኖር ነበር። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩ ናታንን “እነሆ እኔ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል!” አለው። ናታንም “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ በልብህ ያሰብከውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት። ነገር ግን በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሂድና ለአገልጋዬ ለዳዊት እኔ ስለ እርሱ የምለውን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ ነህን? የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ በመታደግ ካዳንኩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በድንኳን ውስጥ ሆኜ በየስፍራው ስዘዋወር ኖርኩ እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም፤ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው መሪዎች መካከል በሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቤት እንዲሠራልኝ የጠየቅሁት አለን?’ “ስለዚህም ለአገልጋዬ ለዳዊት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ አንተን የበግ መንጋ ከምትጠብቅበት መስክ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ፤ በሄድክበት ስፍራ ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርኩ፤ ወደፊትም በተራመድህ መጠን ጠላቶችህን ድል አደረግሁልህ፤ ገና ደግሞ በዓለም እንደ ታወቁት ታላላቅ መሪዎች ዝነኛ አደርግሃለሁ። ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ አዘጋጅቴ በራሳቸው ቦታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ለእነርሱ መሳፍንትን ከሾምኩበት ጊዜ ጀምሮ ክፉ አድራጊዎች ቀድሞ ያደርጉት እንደ ነበረው አያስጨንቋቸውም፤ አንተንም ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ከቤትህ አልጋህን የሚወርሱ ልጆች እተካልሃለሁ ብሎ ይገልጥልሃል።
2 ሳሙኤል 7:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ከተቀመጠና ጌታም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፥ ነቢዩን ናታንን፥ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። ናታንም፥ “ጌታ ካንተ ጋር ስለሆነ፥ በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ” አለው። በዚያች ሌሊት ግን የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፤ “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን፥ ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ ነህን?’ እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም ከእስራኤላውያን ሕዝብ ጋር በተጓዝሁበት ስፍራ ሁሉ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው አንዱን፥ ‘ከዝግባ ዕንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?’ ያልሁት አለን? አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አስወገድሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቁነውም፤ ከዚህ በፊት እንደ ሆነው፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ። ከዚህም በላይ ጌታ ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤