2 ሳሙኤል 21:1-14
2 ሳሙኤል 21:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል በተከታታይ ራብ ሆነ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ቃል ጠየቀ። እግዚአብሔርም አለ፥ “የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት፥” ንጉሡ ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፤ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፤ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፤ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች፥ “የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተስረያውስ ምንድን ነው?” አላቸው። የገባዖን ሰዎችም፥ “ከሳኦልና ከቤቱ ወርቅ ወይም ብር አንፈልግም፤ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም” አሉት። እርሱም፥ “ምን ትላላችሁ? ተናገሩ፤ እኔም አደርግላችኋለሁ” አላቸው፤ እነርሱም ለንጉሡ አሉት፥ “በእኛ ላይ ክፉ ያደረገውን፥ ያሳደደንንና ሊያጠፋን ያሰበውን ሰው እናጥፋው፤ እርሱም በእስራኤል ዳርቻ እንዳይቆም እናደርገዋለን። ከልጆቹ ሰባት ሰዎች ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል ሀገር በገባዖን ለእግዚአብሔር እንሠቅላቸዋለን።” ንጉሡም፥ “እሰጣችኋለሁ” አለ። ንጉሡም በእነርሱ መካከል፥ በዳዊትና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፌቡስቴን ራራለት። ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄልን ልጅ የሩጻፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንስቴንና ሜምፌቡስቴን፥ ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድራ የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፤ በገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ እህል በሚታጨድበትም ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ። የኢዮሔል ልጅ ሩጻፋም ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው፤ በቀንም የሰማይ ወፎች፥ በሌሊትም የዱር አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም። የሳኦልም ዕቅብት የኢዮሔል ልጅ ሩጻፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ሄደ፤ ሳአልንም በጌላቡሄ በገደሉት ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቤስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልን አጥንትና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ። ከዚያም የሳኦልን አጥንትና የልጁን የዮናታንን አጥንት አመጣ፤ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ። የሳኦልን አጥንትና የልጁን የዮናታንን አጥንት፥ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት በብንያም በአባቱ በቂስ መቃብር አጠገብ ቀበሩአቸው፤ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ምድርን ሰማት።
2 ሳሙኤል 21:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፣ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። ንጉሡ ገባዖናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ ከእስራኤል ወገን አልነበሩም፤ እስራኤላውያን ሊጠብቋቸው ቢምሉላቸውም፣ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ካለው ቅናት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር፤ ዳዊትም ገባዖናውያንን፣ “ምን ላድርግላችሁ? የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ማስተስረያውን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቃቸው። ገባዖናውያንም፣ “ከሳኦልም ሆነ ከቤተ ሰቡ ብር ወይም ወርቅ የመጠየቅ መብት የለንም፤ እንዲሁም ከእስራኤል ማንንም ለመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት። ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን ላድርግላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ንጉሡን፣ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው ከርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ፣ “ዕሺ እሰጣችኋለሁ” አለ። ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በእግዚአብሔር ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፣ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን ከሞት አተረፈ። ነገር ግን ንጉሡ፣ የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን፤ የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለመሓላታዊው ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደችለትን ዐምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤ ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ የተገደሉትም በመከሩ ወራት የመጀመሪያ ቀኖች፣ የገብስ ዐጨዳ በተጀመረበት ዕለት ነበር። የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፣ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከ ወረደ ጊዜ ድረስ፣ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤ የሳኦል ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፣ ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ወሰደ፤ የኢያቢስ ገዦች፣ ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ ከገደሉ በኋላ እነርሱን ከሰቀሉት ከቤትሳን አደባባይ በድብቅ ወስደዋቸው ነበር። ዳዊትም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አመጣ፤ እንዲሁም የእነዚያን የተገደሉትን ሰዎች ዐፅም ሰበሰቡ። የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።
2 ሳሙኤል 21:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ቀጥሎ ራብ ሆነ፥ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦ የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ። ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፥ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፥ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፥ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች፦ የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተሰረያውስ ምንድር ነው? አላቸው። የገባዖን ሰዎችም፦ በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ነገር አይደለም፥ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም አሉት። እርሱም፦ የምትናገሩትን አደርግላችኋለሁ አለ። ንጉሡንም፦ እኛን ካጠፋ፥ ከእስራኤል ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት። ንጉሡም፦ እሰጣችኋለሁ አለ። ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ። ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥ ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፥ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ። የኢዮሄልም ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው በቀንም ወፎች በሌሊትም አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም። የሳኦልም ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ሄደ፥ ሳኦልንም በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፥ ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ይዞ መጣ፥ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ። የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩት፥ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ አገሩ የተለመነውን ሰማ።
2 ሳሙኤል 21:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዳዊት ዘመነ መንግሥት ሦስት ዓመት ሙሉ ጽኑ ራብ ነበር፤ ዳዊትም ስለዚህ ጉዳይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጠየቀ ጊዜ እግዚአብሔር “ሳኦልና ቤተሰቡ ግድያ በመፈጸም በደል ሠርተዋል፤ ሳኦልም የገባዖንን ሰዎች ፈጅቶአል” ሲል መለሰለት። እንደሚታወቀው ሁሉ የገባዖን ሰዎች እስራኤላውያን አልነበሩም፤ እነርሱ እስራኤላውያን ሊጠብቁአቸው ቃል ስለ ገቡላቸው ከአሞራውያን ተከፍለው ብቻቸውን የሚኖሩ ነበሩ፤ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ በነበረው ቀኖች ሊያጠፋቸው ዐቅዶ ነበር። ስለዚህም ዳዊት የገባዖንን ሰዎች በአንድነት ጠርቶ “የእግዚአብሔርን ሕዝብ ትመርቁ ዘንድ ቀድሞ በተፈጸመባችሁ ግፍ ፈንታ ካሣ የሚሆን አንድ ነገር ላደርግላችሁ እፈልጋለሁ፤ ታዲያ፥ ምን ላድርግላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ከሳኦልና ከቤተሰቡ ጋር ያለን ጥል በብርና በወርቅ የሚገታ አይደለም፤ ከዚህም በቀር እኛ ከእስራኤል ወገን ማንንም መግደል አንፈልግም” ሲሉ መለሱለት። ዳዊትም “ታዲያ ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሳኦል በሙሉ ሊያጠፋንና ከእኛ መካከል ማንም ሰው በእስራኤል ምድር በየትኛውም ስፍራ በሕይወት እንዳይኖር ፈልጎ ነበር፤ ስለዚህ ከሳኦል ዘሮች ሰባት ወንዶችን ለእኛ አሳልፈህ ስጠን፤ እኛም እነርሱን እግዚአብሔር መርጦ ባነገሠው በንጉሥ ሳኦል ከተማ በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንሰቅላቸዋለን” ሲሉ መለሱ። ንጉሥ ዳዊትም “እነርሱን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው። ነገር ግን ዳዊትና ዮናታን እርስ በርሳቸው በገቡት የተቀደሰ ቃል ኪዳን ምክንያት ዳዊት የሳኦልን የልጅ ልጅ የዮናታንን ልጅ መፊቦሼትን አሳልፎ አልሰጣቸውም። ይሁን እንጂ ዳዊት የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች አርሞኒንና መፊቦሼትን ወሰደ፤ እንዲሁም የሳኦል ልጅ ሜራብ የመሖላን ተወላጅ ለሆነው ለባርዚላይ ልጅ ለዐድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጨምሮ ወሰደ። ዳዊት እነዚህን ሁሉ ለገባዖን ሰዎች አሳልፎ ሰጠ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፤ ሰባቱም በአንድነት ሞቱ፤ እነርሱም የተገደሉት በጸደይ ወራት ማለቂያና በገብስ መከር መጀመሪያ ላይ ነበር። ከዚህ በኋላ የሳኦል ቊባት የነበረችው የአያ ልጅ ሪጽፋ ሬሳዎቹ ባሉበት ስፍራ አጠገብ በሚገኘው ቋጥኝ ድንጋይ ላይ ማቅ ዘርግታ ከስሩ ተቀመጠች፤ እርስዋም ከመከር ጊዜ መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ እስከሚጥልበት ጊዜ ድረስ እዚያ ቈየች፤ ቀን ቀን ወፎች በሬሳዎቹ ላይ እንዳያርፉ እየተከላከለች፥ ሌሊት ሌሊትም አውሬ እንዳይበላቸው ትጠብቃቸው ነበር። ዳዊት፥ የሳኦል ቁባት የነበረችው ሪጽፋ ያደረገችውን በሰማ ጊዜ፥ በገለዓድ ምድር ወደምትገኘው ወደ ያቤሽ ሕዝብ ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም አመጣ፤ የያቤሽ ሕዝብ ዐፅሙን ያገኙት ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ በገደሉበት ቀን ሬሳዎችን ከሰቀሉበት ከቤትሻን አደባባይ በመስረቅ ነበር። ዳዊት የሳኦልንና የዮናታንን ዐፅም ወሰደ፤ እንዲሁም ተሰቅለው የነበሩትን የሰባቱን ሰዎች አስከሬን ሰበሰበ፤ ከዚህ በኋላ የሳኦልንና የዮናታንን ዐፅም ወስደው በብንያም ጼላዕ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ውስጥ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ቀበሩ፤ ይህ ሁሉ ከተፈጸመም በኋላ ሕዝቡ ስለ አገራቸው ያቀረቡትን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።
2 ሳሙኤል 21:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት ጌታን ጠየቀ፤ ጌታም፥ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፥ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። ንጉሡም ገባዖናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ ከእስራኤል ወገን አልነበሩም፤ እስራኤላውያን ሊጠብቋቸው ቢምሉላቸውም፥ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ካለው ቅናት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር፤ ዳዊትም ገባዖናውያንን፥ “ምን ላድርግላችሁ? የጌታን ርስት ትባርኩ ዘንድ ማስተሰረያውን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቃቸው። ገባዖናውያንም፥ “በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ጉዳይ አይደለም፥ እንዲሁም ከእስራኤል ማንንም ለመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት። ዳዊትም፥ “ታዲያ ምን ላድርግላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው ከእርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከጌታ በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በጌታ ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ፥ “እሺ! እሰጣችኋለሁ” አለ። ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በጌታ ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፥ የዮናታንን ልጅ መፊቦሼትን ከሞት አተረፈ። ነገር ግን ንጉሡ የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች አርሞኒንና መፊቦሼትን፤ የሳኦል ልጅ ሜራብ ለመሖላታዊው ለባርዚላይ ልጅ ለአድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤ ከዚያም ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በጌታ ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ሞቱ፤ የተገደሉትም እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ነበር። የአያ ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፥ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከወረደ ጊዜ ድረስ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤ የሳኦል ዕቁባት የአያ ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፥ ዳዊት ሄዶ፥ ሳኦልን በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤት ሻን አደባባይ ከሰረቁት ከያቤሽ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፥ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አምጥቶ፥ የእነዚያን የተሰቀሉትን ሰዎች ዐፅምም ሰበሰቡ። የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።