2 ሳሙኤል 19:1-23

2 ሳሙኤል 19:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ለኢ​ዮ​አብ፥ “ንጉሡ ስለ አቤ​ሴ​ሎም ያዝ​ናል፤ ያለ​ቅ​ሳ​ልም” ብለው ነገ​ሩት። በዚ​ያም ቀን፥ “ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ” ሲባል ሕዝቡ ሰም​ቶ​አ​ልና በዚ​ያው ቀን ሕይ​ወት በሕ​ዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኀዘን ተለ​ወጠ። ከሰ​ልፍ በሸሸ ጊዜ ያፈረ ሕዝብ ተሰ​ርቆ እን​ደ​ሚ​ገባ በዚያ ቀን ሕዝቡ ተሰ​ር​ቀው ወደ ከተማ ገቡ። ንጉ​ሡም ፊቱን ሸፈነ፤ ንጉ​ሡም በታ​ላቅ ድምፅ፥ “ልጄ አቤ​ሴ​ሎም፥ አቤ​ሴ​ሎም፥ ልጄ” እያለ ይጮህ ነበር። ኢዮ​አ​ብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እን​ዲህ አለ፥ “ዛሬ ነፍ​ስ​ህ​ንና የወ​ን​ዶ​ች​ንና የሴ​ቶች ልጆ​ች​ህን ነፍስ፥ የሚ​ስ​ቶ​ች​ህ​ንና የቁ​ባ​ቶ​ች​ህን ነፍስ ያዳ​ኑ​ትን የአ​ገ​ል​ጋ​ዮ​ች​ህን ሁሉ ፊት በዚች ቀን አሳ​ፍ​ረ​ሃል። አንተ የሚ​ጠ​ሉ​ህን ትወ​ድ​ዳ​ለህ፤ የሚ​ወ​ድ​ዱ​ህ​ንም ትጠ​ላ​ለህ፤ አለ​ቆ​ች​ህና አገ​ል​ጋ​ዮ​ችህ እን​ደ​ማ​ይ​ጠ​ቅ​ሙህ እን​ደ​ም​ታ​ስብ ዛሬ ገል​ጠ​ሃ​ልና፤ አቤ​ሴ​ሎ​ምም ድኖ ቢሆን ዛሬ እኛ ሁላ​ችን እን​ሞት እንደ ነበር አው​ቃ​ለሁ። ይህ በፊ​ትህ ላንተ ቀና ነበ​ረና። አሁ​ንም ተነ​ሥ​ተህ ወጥ​ተህ ለአ​ገ​ል​ጋ​ዮ​ችህ በል​ባ​ቸው የሚ​ገባ ነገር ንገ​ራ​ቸው። ዛሬ ወደ እነ​ርሱ ካል​ወ​ጣህ በዚች ሌሊት አንድ ሰው ስንኳ ከአ​ንተ ጋር የሚ​ያ​ድር እን​ዳ​ይ​ኖር በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እም​ላ​ለሁ፤ ከሕ​ፃ​ን​ነ​ትህ ጀምሮ እስ​ከ​ዚች ቀን ድረስ ካገ​ኘህ መከራ ሁሉ ዛሬ የም​ታ​ገ​ኝህ መከራ እን​ድ​ት​ከ​ፋ​ብህ እን​ግ​ዲህ አንተ ለራ​ስህ ዕወቅ” አለው። ንጉ​ሡም ተነ​ሥቶ በበሩ ተቀ​መጠ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ ተቀ​ም​ጧል ብለው ተና​ገሩ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ በበሩ ወደ ንጉሡ ፊት ወጡ። እስ​ራ​ኤ​ልም እያ​ን​ዳ​ንዱ ወደ ድን​ኳኑ ሸሽቶ ገብቶ ነበር። ከመ​ላው ነገደ እስ​ራ​ኤል የተ​ሰ​በ​ሰቡ ሕዝብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ከጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችን እጅ ታድ​ጎ​ናል፥ ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም እጅ አድ​ኖ​ናል፤ አሁ​ንም ስለ አቤ​ሴ​ሎም ከሀ​ገ​ሩና ከመ​ን​ግ​ሥቱ ሸሸ። በላ​ያ​ችን ላይ የቀ​ባ​ነው አቤ​ሴ​ሎ​ምም በጦ​ር​ነት ሞቶ​አል፤ አሁ​ንም ንጉ​ሡን ለመ​መ​ለስ ስለ​ምን ዝም ትላ​ላ​ችሁ?” አሉ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ቃል ወደ ንጉሥ ደረሰ። ንጉሡ ዳዊ​ትም ለካ​ህ​ናቱ ለሳ​ዶ​ቅና ለአ​ብ​ያ​ታር ልኮ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ለይ​ሁዳ ሽማ​ግ​ሌ​ዎች እን​ዲህ ብላ​ችሁ ተና​ገ​ሩ​አ​ቸው፦ የእ​ስ​ራ​ኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደር​ሶ​አ​ልና ንጉ​ሡን ወደ ቤቱ ከመ​መ​ለስ ስለ​ምን ዘገ​ያ​ችሁ? እና​ንተ ወን​ድ​ሞች፥ የአ​ጥ​ንቴ ፍላ​ጭና የሥ​ጋዬ ቍራጭ ናችሁ፤ እና​ንተ ንጉ​ሡን ወደ ቤቱ ከመ​መ​ለስ ስለ​ምን ዘገ​ያ​ችሁ? ለአ​ሚ​ሳ​ይም፦ አንተ የአ​ጥ​ንቴ ፍላ​ጭና የሥ​ጋዬ ቍራጭ አይ​ደ​ለ​ህ​ምን? በዘ​መ​ን​ህም ሁሉ በኢ​ዮ​አብ ፋንታ በፊቴ የሠ​ራ​ዊት አለቃ ሳት​ሆን ብት​ቀር ዛሬ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይህን ያድ​ር​ግ​ብኝ፤ ይህ​ንም ይጨ​ም​ር​ብኝ በሉት።” የይ​ሁ​ዳ​ንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድ​ርጎ አዘ​ነ​በለ፤ ወደ ንጉ​ሡም፥ “አን​ተና ብላ​ቴ​ኖ​ችህ፥ አገ​ል​ጋ​ዮ​ች​ህም ሁሉ ተመ​ለሱ” ብለው ላኩ​በት። ንጉ​ሡም ተመ​ልሶ እስከ ዮር​ዳ​ኖስ ድረስ መጣ። የይ​ሁዳ ሰዎ​ችም ንጉ​ሡን ሊቀ​በሉ፥ ንጉ​ሡ​ንም ዮር​ዳ​ኖ​ስን ሊያ​ሻ​ግሩ ወደ ጌል​ገላ መጡ። ከባ​ው​ሪም ሀገር የነ​በ​ረው የኢ​ያ​ሚን ልጅ የጌራ ልጅ ሳሚም ከይ​ሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊ​ትን ሊቀ​በል ፈጥኖ ወረደ። ከእ​ር​ሱም ጋራ ከብ​ን​ያም ወገን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳ​ኦ​ልም ቤት አገ​ል​ጋይ ሲባ ከእ​ር​ሱም ጋር ዐሥራ አም​ስቱ ልጆ​ቹና ሃያው አገ​ል​ጋ​ዮቹ ነበሩ፤ በን​ጉ​ሡም ፊት በቀ​ጥታ ወደ ዮር​ዳ​ኖስ ሄዱ። ንጉ​ሡ​ንም የማ​ሻ​ገር ሥራ ሠሩ። የን​ጉ​ሡ​ንም ቤተ ሰብእ ያነሡ ዘንድ፥ በፊ​ቱም የቀና ሥራን ይሠሩ ዘንድ ወደ ማዶ ተሻ​ገሩ። ንጉ​ሡም ዮር​ዳ​ኖ​ስን ከተ​ሻ​ገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በን​ጉሡ ፊት፦ በግ​ን​ባሩ ወደቀ። እር​ሱም ንጉ​ሡን አለው፥ “ጌታዬ! ኀጢ​አ​ቴን አት​ቍ​ጠ​ር​ብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም በወ​ጣህ ቀን ባሪ​ያህ የበ​ደ​ል​ሁ​ህን አታ​ስ​ብ​ብኝ፤ ጌታዬ ንጉ​ሡም በል​ብህ አታ​ኑ​ር​ብኝ። እኔ አገ​ል​ጋ​ይህ በደ​ለኛ እንደ ሆንሁ አው​ቄ​አ​ለ​ሁና እነሆ፥ ከዮ​ሴፍ ቤት ሁሉ አስ​ቀ​ድሜ ዛሬ መጣሁ፤ ጌታ​ዬ​ንም ንጉ​ሡን ልቀ​በል ወረ​ድሁ።” የሶ​ር​ህያ ልጅ አቢሳ ግን፥ “ሳሚ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የቀ​ባ​ውን ሰድ​ቦ​አ​ልና እን​ግ​ዲህ ሞት የተ​ገ​ባው አይ​ደ​ለ​ምን?” ብሎ መለሰ። ዳዊ​ትም፥ “እና​ንተ የሶ​ር​ህያ ልጆች! ዛሬ ታስ​ቱኝ ዘንድ በእ​ኔና በእ​ና​ንተ መካ​ከል ምን አለኝ? ዛሬስ ከእ​ስ​ራ​ኤል የሚ​ሞት አንድ ሰው የለም። ዛሬስ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ እንደ ነገ​ሥሁ አላ​ው​ቅ​ምን?” ንጉ​ሡም ሳሚን፥ “አት​ሞ​ትም” አለው። ንጉ​ሡም ማለ​ለት።

2 ሳሙኤል 19:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለኢዮአብ፣ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰ እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። ንጉሡ፣ “ስለ ልጁ ዐዝኗል” መባሉን በዚያ ቀን ሰራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሰራዊት ዘንድ ወደ ሐዘን ተለውጦ ዋለ። በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ተሸማቆ ወደ ከተማ ገባ። ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” እያለ ጮኸ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፣ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን ዐልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። በል አሁን ተነሥተህ ውጣና ሰዎችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው ዐብሮህ እንደማይሆን በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያስከትልብሃል።” ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፣ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጧል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ። በዚያ ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደ የቤታቸው ሸሽተው ነበር። በመላው የእስራኤል ነገዶችም፣ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዷል፤ በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቷል፤ ታዲያ ንጉሡን የመመለሱን ጕዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?” ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የይሁዳ ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለ ሆነ፣ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ? እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’ አሜሳይንም፣ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሰራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፣ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።” እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም ሰዎችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ወደ ንጉሡ ላኩበት። ከዚያም ንጉሡ ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ተቀብለው ዮርዳኖስን ለማሻገር እስከ ጌልገላ ድረስ መጥተው ነበር። የባሑሪም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋራ ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ወረደ። ከርሱም ጋራ አንድ ሺሕ ብንያማውያን፣ እንዲሁም የሳኦል ቤተ ሰብ አገልጋይ ሲባ ከዐሥራ ዐምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋራ ሆኖ ዐብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ በጥድፊያ ወረዱ። የንጉሡን ቤተ ሰው ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ በመልካው ተሻገሩ። የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፣ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አይቍጠርብኝ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከኢየሩሳሌም በወጣህባት ዕለት የፈጸምሁትን ስሕተት እርሳው፤ ከአእምሮህም አውጣው። እኔ አገልጋይህ ኀጢአት መሥራቴን ዐውቃለሁና፤ ዛሬ ግን ጌታዬን ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ እነሆ መጥቻለሁ።” ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፣ “ሳሚ በእግዚአብሔር የተቀባውን የረገመ ስለ ሆነ፣ መሞት አይገባውምን?” አለ። ዳዊትም፣ “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ እናንተንና እኔን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ? ዛሬ ጠላት ሆናችሁኛል! ማንስ ቢሆን ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ሰው መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ንጉሡ ሳሚን፣ “አትሞትም” አለው፤ ይህንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት።

2 ሳሙኤል 19:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢዮአብም ንጉሡ ስለ አቤሴሎም እንዳለቀሰና ዋይ ዋይ እንዳለ ሰማ። በዚያም ቀን፦ ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና የዚያ ቀን ድል በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኅዘን ተለወጠ። ሕዝቡም ከሰልፍ የሸሸ ሕዝብ አፍሮ ወደ ኋላው እንዲል በዚያ ቀን ወደ ከተማ ተሰርቆ ገባ። ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፥ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፦ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ እያለ ይጮኽ ነበር። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፦ ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የባሪያዎችህን ሁሉ ፊት ዛሬ አሳፍረሃል፥ አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፦ የሚወድዱህንም ትጠላለህ። መሳፍንትህና ባሪያዎችህን እንዳታስብ ዛሬ ገልጠሃል፥ ዛሬ ሁላችን ሞተን ቢሆን ኖር አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ኖሮ ደስ ያሰኘህ እንደ ነበረ ዛሬ አያለሁ። አሁን እንግዲህ ተነሥተህ ውጣ፥ ለባሪያዎችህም የሚያጽናናቸውን ነገር ተናገራቸው፥ ያልወጣህ እንደ ሆነ ግን አንድ ሰው ከአንተ ጋር በዚህች ሌሊት እንዳይቀር በእግዚአብሔር እምላለሁ፥ ይህም ከብላቴናነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ካገኘህ ክፉ ነገር ሁሉ ይልቅ ታላቅ መከራ ይሆንብሃል። ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፥ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ እንደተቀመጠ ሰማ፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ንጉሡ ፊት መጣ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ነበር። ሕዝቡም ሁሉ በእስራኤል ነገድ ሁሉ ውስጥ፦ ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፥ አሁንም ስለ አቤሴሎም ከአገር ሸሽቶአል። በላያችን እንዲሆን የቀባነው አቤሴሎም በሰልፍ ሞቶአል፥ አሁንም እንግዲህ ንጉሡን ለመመለስ ስለ ምን ዝም ትላላችሁ? እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር። ንጉሡም ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው፦ ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው፦ የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? እናንተ ወንድሞቼ፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ ናችሁ፥ እናንተ ንጉሡን ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? ለአሜሳይም፦ አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት። የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፥ ወደ ንጉሡም ልከው፦ አንተ ከባሪያዎችህ ሁሉ ጋር ተመለስ አሉት። ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ሊቀበሉ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ። ከብራቂምም አገር የነበረው ብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ። ከእርሱም ጋር ብንያማውያን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፥ የሳኦልም ቤት ባሪያ ሲባ ከእርሱም ጋር አሥራ አምስቱ ልጆችና ሀያው ባሪያዎች ነበሩ፥ በንጉሡም ፊት ፈጥነው ዮርዳኖስን ተሻገሩ። ታንኳውም የንጉሥን ቤተ ሰብ ያሻግር ዘንድ ንጉሡም ደስ ያሰኘውን ያደርግ ዘንድ ይሸጋገር ነበር። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በፊቱ ተደፋ። ንጉሡንም፦ ጌታዬ ሆይ፥ ኃጢአቴን አትቍጠርብኝ፥ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀነ ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ ንጉሡም በልቡ አያኑረው። ባሪያህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፥ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ አለው። የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን፦ ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት የተገባው አይደለምን? አለ። ዳዊትም፦ እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን? አለ። ንጉሡም ሳሚን፦ አትሞትም አለው። ንጉሡም ማለለት።

2 ሳሙኤል 19:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ንጉሥ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም ሞት በብርቱ አዝኖ በማልቀስ ላይ መሆኑን ኢዮአብ ሰማ፤ እንዲሁም ንጉሡ በልጁ ሞት ምክንያት በሐዘን ላይ መሆኑን ስለ ሰሙ ወታደሮቹ ያገኙት የድል አድራጊነት ደስታ በዚያ ቀን ወደ ሐዘን ተለወጠባቸው። ስለዚህ ከጦር ግንባር ተመልሰው ወደ ኋላ እንደሚሸሹ ወታደሮች ድምፃቸውን አጥፍተው በጸጥታ ወደ ከተማይቱ ገቡ፤ ንጉሡም ፊቱን ሸፍኖ “ልጄ ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! አቤሴሎም ልጄ!” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለቅስ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የቊባቶችህን ሕይወት ያዳኑትን ሰዎች ዛሬ አሳፍረሃቸዋል፤ አንተ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የሚጠሉህን ግን ትወዳለህ! ስለ ጦር መኰንኖችህና ስለ ወታደሮችህ ሁሉ ምንም የማይገድህ መሆኑን በግልጥ አሳይተሃል፤ አቤሴሎም በሕይወት ቢኖርና እኛ ሁላችን ብንጠፋ ኖሮ እጅግ እንደምትደሰት ተገንዝቤአለሁ፤ ይልቅስ አሁን ተነሥና ወታደሮችህን አበረታታ፤ ይህንን ባታደርግ ግን ነገ ጠዋት ከእነርሱ አንዱ እንኳ ከአንተ ጋር እንደማይሆን በእግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ይህም በሕይወትህ ከደረሰብህ መከራ ሁሉ እጅግ የከፋ ይሆንብሃል።” ከዚህ በኋላ ንጉሡ ከተቀመጠበት ተነሥቶ በመሄድ በከተማይቱ ቅጽር በር አጠገብ ተቀመጠ፤ ተከታዮቹም እዚያ መሆኑን ሰምተው ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ። በዚህን ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ሸሽተው እያንዳንዱ ወደየቤቱ ሄዶ ነበር፤ በመላ አገሪቱም ሕዝቡ እርስ በርስ መጣላት ጀመረ፤ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ንጉሥ ዳዊት ከጠላቶቻችን እጅ አድኖናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አውጥቶናል፤ አሁን ግን ከአቤሴሎም ፊት በመሸሽ አገሪቱን ትቶ ሄዶአል። መሪያችን ይሆን ዘንድ አቤሴሎምን ቀብተን አንግሠነው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ በጦርነት ላይ ተገደለ፤ ታዲያ፥ ንጉሥ ዳዊትን መልሶ ለማምጣት የሚሞክር ሰው እንዴት ታጣ?” ንጉሥ ዳዊትም እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው የተናገሩትን ሰማ፤ ስለዚህም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን በመላክ የይሁዳን መሪዎች እንዲህ ብለው እንዲጠይቁአቸው አዘዘ፤ “ንጉሡን ረድታችሁ ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ ስለምን እናንተ የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ? እናንተ እኮ ለእኔ የሥጋ ዘመዶቼ ናችሁ፤ ታዲያ፥ እኔን መልሶ ለመውሰድ የመጀመሪያዎቹ በመሆን ፈንታ ስለምን የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ?” እንዲሁም ለዐማሳ ሲናገር “አንተም ለእኔ የሥጋ ዘመድ ነህ፤ ከአሁን ጀምሮ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ አደርግሃለሁ፤ ይህንንም ባላደርግ እግዚአብሔር በሞት ይቅጣኝ!” ብላችሁ ንገሩት ሲል አዘዛቸው። የዳዊት አነጋገር የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለእርሱ ታማኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው፤ ስለዚህም ከመኳንንቱ ሁሉ ጋር ተመልሶ እንዲመጣ ላኩበት። ዳዊት በመመለስ ላይ እንዳለም የይሁዳ ሰዎች እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ሄደው ተቀበሉት፤ አጅበውም ወንዙን ለማሻገር አስበው እስከ ጌልጌላ ድረስ መጡ፤ በዚያኑ ጊዜም የባሑሪም ተወላጅ የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሺምዒ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ፈጥኖ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር የብንያም ነገድ የሆኑ አንድ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳኦል ቤተሰብ አገልጋይ የነበረው ጺባም ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከኻያ አገልጋዮቹ ጋር መጣ፤ ወደ ዮርዳኖስም ወንዝ እየተጣደፉ ደርሰው በንጉሡ ፊት ቀረቡ። እነርሱም ንጉሡንና ተከታዮቹን በጀልባ አጅበው ወደ ማዶ ለማድረስና ንጉሡ የሚፈልገውን ሁሉ ለማድረግ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ። ንጉሡ ወንዙን ለመሻገር ሲዘጋጅ ሳለ የጌራ ልጅ ሺምዒ መጥቶ በፊቱ ተዘረጋና እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! ከኢየሩሳሌም ወጥተህ በሄድክበት ቀን ያደረግኹትን በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ ቂም በቀልም አትያዝብኝ፤ ዳግመኛም ስለ እርሱ አታስብ፤ ጌታዬ ሆይ! ኃጢአት እንደ ሠራሁ ዐውቃለሁ፤ ዛሬ ግን ከሰሜን የእስራኤል ነገዶች የመጀመሪያው በመሆን አንተን ለመቀበል መጥቼአለሁ።” የጸሩያ ልጅ አቢሳም “እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠውን ስለተሳደበ ሺምዒ በሞት መቀጣት ይገባዋል” ሲል ተናገረ። ዳዊት ግን አቢሳንና ወንድሙን ኢዮአብን “ይህን አሳብ እንድታቀርቡ የጠየቃችሁ ማን ነው? ችግር ልታመጡብኝ ትፈልጋላችሁን? እነሆ፥ አሁን የእስራኤል ንጉሥ እኔ ነኝ፤ ደግሞም በዛሬው ዕለት ማንም እስራኤላዊ በሞት አይቀጣም” አላቸው። ሺምዒንም “በሞት እንደማትቀጣ ቃል እገባልሃለሁ!” አለው።

2 ሳሙኤል 19:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ንጉሡም እጅግ አዘነ፤ በቅጽር በሩ ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም፥ ልጄን፥ ወየው ልጄን!” ይል ነበር። ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰና እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። ንጉሡ፥ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሠራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፥ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሠራዊት ዘንድ ወደ ኀዘን ተለውጦ ዋለ። በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ድምፅ ሳያሰማ ወደ ከተማ ገባ። ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ፥ ልጄን! ልጄን!” እያለ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፥ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የዕቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳልሆኑ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። በል አሁን ተነሥተህ ውጣና አገልጋዮችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በጌታ ስም እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያሰከትልብሃል።” ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፥ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጦአል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ። በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደየቤታቸው ሸሽተው ነበር። በመላው የእስራኤል ነገዶችም፥ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዶአል፤ በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቷል፤ ታዲያ ስለ ንጉሡ የመመለስ ጉዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?” ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለሆነ፥ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ? እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፥ የሥጋዬ ቁራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’ አማሳይንም፥ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፥ የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፥ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፥ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።” እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም አገልጋዮችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት። ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳም ሰዎች ንጉሡን ተቀብለው ዮርዳኖስን ለማሻገር እስከ ጌልገላ ድረስ መጥተው ነበር። የባሑሪም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሺምዒ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ሄደ። ከእርሱም ጋር አንድ ሺህ ብንያማውያን፥ እንዲሁም የሳኦል ቤተሰብ አገልጋይ ጺባ ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋር ሆኖ አብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ፈጥነው ተሻገሩ። የንጉሡን ቤተሰብ ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ ዮርዳኖስን ተሻገሩ። የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፥ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አትቁጠርብኝ፥ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀነ አገልጋይህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ በልብህም አታኑርብኝ። እኔ አገልጋይህ ኃጢአት መሥራቴን አውቃለሁና፤ እነሆ፥ ዛሬ ግን ጌታዬ ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ መጥቻለሁ።” ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፥ “ሺምዒ በጌታ የተቀባውን የረገመ ስለሆነ፥ መሞት አይገባውምን?” አለ። ዳዊትም፥ “እናንት የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬ ማንስ ቢሆን በእስራኤል ዘንድ መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ።