2 ቆሮንቶስ 2:12-17
2 ቆሮንቶስ 2:12-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ፣ ጌታ በር ከፍቶልኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ ወንድሜን ቲቶን እዚያ ስላላገኘሁት መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ ተሰናብቻቸው ወደ መቄዶንያ ሄድሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ በድል አድራጊነት እያዞረ ለሚመራን፣ የዕውቀቱንም መዐዛ በእኛ አማካይነት በየስፍራው ለሚገልጥ አምላክ ምስጋና ይሁን፤ ምክንያቱም በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዐዛ ነን። ለሚጠፉት ወደ ሞት የሚወስድ የሞት ሽታ፣ ለሚድኑት ግን ወደ ሕይወት የሚወስድ የሕይወት ሽታ ነን፤ ታዲያ፣ ለዚህ ብቁ የሚሆን ማን ነው? እኛ እኮ ትርፍ ለማግኘት ብለን የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ ሰዎች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:12-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለክርስቶስም ወንጌል ጢሮአዳ በደረስሁ ጊዜ በእግዚአብሔር በሩ ተከፈተልኝ። ወንድሜን ቲቶን ስላላገኘሁት ለሰውነቴ ዕረፍት አላገኘሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ ተለይች ወደ መቄዶንያ ሄድሁ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ድል በመንሣቱ የሚጠብቀን፥ በየሀገሩም ሁሉ የዕውቀቱን መዓዛ በእኛ የሚገልጥ እግዚአብሔር ይመስገን። በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ እኛ ነንና። የሞት መዓዛ የሚገባቸው ለሞት፥ የሕይወት መዓዛ የሚገባቸውም ለሕይወት ናቸው፤ ነገር ግን ይህ የሚገባው ማነው? የእግዚአብሔርን ቃል በሌላ ቀላቅለው እንደሚሸቅጡ እንደ ብዙዎች አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላከ በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም፥ ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:12-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ የክርስቶስን ወንጌል ለማስተማር ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ ጌታ ሰፊ የአገልግሎት በር ከፍቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን ወንድሜን ቲቶን ባለማግኘቴ መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ እዚያ ያሉትን ክርስቲያኖች ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ሄድኩ። ነገር ግን እኛን ዘወትር በክርስቶስ ድል አድራጊዎች አድርጎ ለሚመራንና መልካም መዓዛ እንዳለው ሽቶ ስለ ክርስቶስ ያለንን ዕውቀት በየስፍራው ሁሉ እንድናዳርስ ለሚያደርገን አምላክ ምስጋና ይሁን! እኛ ለሚድኑትም ሆነ ለሚጠፉት መልካም ሽታ እንዳለው ዕጣን በክርስቶስ ለእግዚአብሔር የቀረብን ነን። ለአንዱ የሚገድል የሞት ሽታ ነን፤ ለሌላው ሕይወትን የሚሰጥ የሕይወት መዓዛ ነን፤ ታዲያ፥ ለዚህ አገልግሎት ብቁ የሚሆን ማን ነው? እኛ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ንግድ ዕቃ እንደሚቸረችሩት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ ቅን መልእክተኞች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ በጌታ በሩ ተከፍቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንፈሴ ማረፍ አልቻለም፤ ምክንያቱም እዚያ ወንድሜን ቲቶን አላገኘሁትም። ስለዚህ ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን፥ በእኛም በሁሉም ስፍራ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ፥ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነን፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፥ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚነግዱ እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።