2 ቆሮንቶስ 11:23-33

2 ቆሮንቶስ 11:23-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እነ​ርሱ የክ​ር​ስ​ቶስ አገ​ል​ጋ​ዮች ቢሆ​ኑም እኔም እንደ ሰነፍ ለራሴ እና​ገ​ራ​ለሁ፤ እኔ እበ​ል​ጣ​ለሁ፤ እጅ​ግም ደከ​ምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገ​ረ​ፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰ​ርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘ​ጋ​ጀሁ። አይ​ሁድ አን​ዲት ስት​ቀር አም​ስት ጊዜ አርባ አርባ ገረ​ፉኝ። ሦስት ጊዜ በበ​ትር ደበ​ደ​ቡኝ፤ አንድ ጊዜ በድ​ን​ጋይ መቱኝ፤ መር​ከቤ ሦስት ጊዜ ተሰ​በ​ረች፤ በጥ​ልቁ ባሕር ውስጥ ስዋኝ አድሬ፥ ስዋኝ ዋልሁ። በመ​ን​ገድ ዘወ​ትር መከራ እቀ​በል ነበር፤ በወ​ን​ዝም መከራ ተቀ​በ​ልሁ፤ ወን​በ​ዴ​ዎ​ችም አሠ​ቃ​ዩኝ፤ ዘመ​ዶ​ችም አስ​ጨ​ነ​ቁኝ፤ አሕ​ዛብ መከራ አጸ​ኑ​ብኝ፤ በከ​ተማ መከራ ተቀ​በ​ልሁ፤ በበ​ረ​ሃም መከራ ተቀ​በ​ልሁ፤ በባ​ሕ​ርም መከራ ተቀ​በ​ልሁ፤ ሐሰ​ተ​ኞች መም​ህ​ራን መከራ አጸ​ኑ​ብኝ። በድ​ካ​ምና በጥ​ረት፥ ብዙ ጊዜም ዕን​ቅ​ልፍ በማ​ጣት፥ በመ​ራ​ብና በመ​ጠ​ማት፥ አብ​ዝ​ቶም በመ​ጾም፥ በብ​ር​ድና በመ​ራ​ቆት ተቸ​ገ​ርሁ። የቀ​ረ​ው​ንም ነገር ሳል​ቈ​ጥር ዕለት ዕለት የሚ​ከ​ብ​ድ​ብኝ የአ​ብ​ያተ ክር​ስ​ቲ​ያ​ናት ሁሉ አሳብ ነው። ታሞ እኔ የማ​ላ​ዝ​ን​ለት ማን ነው? በድ​ሎስ እኔ የማ​ል​ደ​ነ​ግ​ጥ​ለት ማን ነው? መመ​ካት የሚ​ገባ ከሆ​ነስ እኔም በመ​ከ​ራዬ እመ​ካ​ለሁ። ለዘ​ለ​ዓ​ለም ቡሩክ አም​ላክ የሆነ የጌ​ታ​ችን የኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ አባት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሐሰት እን​ደ​ማ​ል​ና​ገር ያው​ቃል። በደ​ማ​ስቆ ከተማ ከን​ጉሥ አር​ስ​ጣ​ስ​ዮስ በታች የሆነ የአ​ሕ​ዛብ አለቃ ሊይ​ዘኝ ወድዶ የደ​ማ​ስ​ቆን ከተማ ያስ​ጠ​ብቅ ነበር። በቅ​ር​ጫ​ትም አድ​ር​ገው በመ​ስ​ኮቱ በኩል በአ​ጥሩ ላይ አወ​ረ​ዱኝ፤ ከእ​ጁም አመ​ለ​ጥሁ።

2 ቆሮንቶስ 11:23-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? አእምሮውን እንደ ጣለ ሰው ልናገርና እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ ደግሞም ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት ተቃርቤአለሁ። አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው ዐምስት ጊዜ ገርፈውኛል። ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፤ አንድ ሌሊትና ቀን በባሕር ላይ ዐድሬአለሁ፤ ብዙ ጊዜ በጕዞ ተንከራትቻለሁ፤ ደግሞም ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋ፣ ለገዛ ወገኖቼ አደጋ፣ ለአሕዛብ አደጋ፣ ለከተማ አደጋ፣ ለገጠር አደጋ፣ ለባሕር አደጋ እንዲሁም ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ ተጋልጬ ነበር። ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ጊዜ ምግብ ሳልቀምስ ኖሬአለሁ፤ በብርድና በዕራቍትነት ተቈራምጃለሁ። ሌላውን ነገር ሳልቈጥር፣ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው። ደካማ ማን ነው? እኔስ አብሬ አልደክምምን? በኀጢአት የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልቈጭምን? መመካት ካለብኝ፣ ደካማነቴን በሚያሳዩ ነገሮች እመካለሁ። ለዘላለም የተመሰገነው የጌታ የኢየሱስ አምላክና አባት እንደማልዋሽ ያውቃል። ደማስቆ ሳለሁ ከንጉሥ አርስጦስዮስ በታች የሆነው ገዥ ሊያስይዘኝ ፈልጎ፣ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር። ነገር ግን በግንቡ መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ ከእጁ አመለጥሁ።

2 ቆሮንቶስ 11:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን? ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ። ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል። በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥ በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።

2 ቆሮንቶስ 11:23-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? እኔ ከእነርሱ ይበልጥ የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ፤ ይህንንም ስል እንደ እብድ ሆኜ ነው የምናገረው፤ ከእነርሱ ይበልጥ ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት አደጋ ደርሼአለሁ፤ ሠላሳ ዘጠኝ፥ ሠላሳ ዘጠኝ ጅራፍ አምስት ጊዜ በአይሁድ ተገርፌአለሁ፤ ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፤ አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በባሕር ላይ ነበርኩ፤ በጒዞዬ ብዛት የወንዝና የጐርፍ፥ የሽፍቶችም አደጋ ደርሶብኛል፤ ከአይሁድ ወገኖቼና ከአሕዛብ አደጋ ደርሶብኛል፤ በከተማና በበረሓ በባሕርም አደጋ ደርሶብኛል፤ እንዲሁም ከሐሰተኞች አማኞች አደጋ ደርሶብኛል። ብዙ ሥራና ድካም ነበረብኝ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ በራብና በውሃ ጥም ተጨንቄአለሁ፤ ብዙ ጊዜም የምግብ እጦት ደርሶብኛል፤ ብርድና መራቆትም ደርሶብኛል። ሌላውንም ሁሉ ነገር ሳልቈጥር ስለ አብያተ ክርስቲያን ሁሉ በየቀኑ በማሰብ እጨነቅ ነበር። አንድ ሰው ሲደክም እኔ አብሬው ያልደከምኩት መቼ ነው? አንድ ሰው በኃጢአት ሲሰናከል እኔም ያልተናደድኩት መቼ ነው? መመካት የሚያስፈልግ ቢሆን እኔ የምመካው ደካማነቴን በሚያሳዩ ነገሮች ነው። ለዘለዓለም የተመሰገነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር እንደማልዋሽ ያውቃል። በደማስቆ ከተማ በነበርኩበት ጊዜ ከንጉሡ ከአሬታስ በታች የነበረው አገረ ገዥ እኔን ለመያዝ ፈልጎ የከተማውን በሮች በዘበኞች ያስጠብቅ ነበር። ነገር ግን ሰዎች በቅጥሩ መስኮት በኩል በቅርጫት አድርገው አወረዱኝና ከእጁ አመለጥኩ።

2 ቆሮንቶስ 11:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንደ እብድ ሰው እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ በሥራ ብዙ ደክሜአለሁ፥ ብዙ ጊዜ ታስሬለሁ፥ ብዙ ግርፋት ደርሶብኛል፥ ብዙ ጊዜ እስከ መሞት ደርሻለሁ። አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው አምስት ጊዜ ገርፈውኛል። ሦስት ጊዜ በበትር ተመትቻለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬለሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰባብሯል፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖሬለሁ። ብዙ ጊዜ በጉዞ ተንከራትቼአለሁ፤ በወንዝ አደጋ፥ በወንበዴዎች አደጋ፥ በወገኔ በኩል ከሚመጣ አደጋ፥ በአሕዛብ በኩል ያለ አደጋ፥ በከተማ አደጋ፥ በምድረ በዳ አደጋ፥ በባሕር አደጋ፥ በሐሰተኛ ወንድሞች በኩል አደጋ ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት፥ በእንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፥ በራብና በጥም፥ ብዙ ጊዜም በመራብ፥ በብርድና በመታረዝ አሳልፌለሁ። ሌላው ሳይቆጠር፥ በየዕለቱ የሚከብድብኝ ለአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መጨነቄ ነው። የሚደክም ማን ነው? እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልናደድምን? ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ መድከሜን በሚያሳይ ነገር እመካለሁ። ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እንዳልዋሸሁ ያውቃል። በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ ፈልጎ የደማስቆ ሰዎችን በከተማው አሰማርቶ ነበር፤ ነገር ግን በግንቡ ላይ በሚገኝ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።