ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 11
11
ለእግዚአብሔር ስለሚደረግ ቅንዐት
1በስንፍናዬ እናገር ዘንድ ጥቂት ልትታገሡኝ ይገባ ነበር፤ ቢሆንም በርግጥ ታገሡኝ፤ 2ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁና።#ግሪኩ “እናንተን ለአንድ ሙሽራ ለክርስቶስ ንጽሕት ድንግል አድርጌ አጭቻችኋለሁና” ይላል። 3#ዘፍ. 3፥1-5፤ 13። ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ከክርስቶስ የዋህነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 4ወደ እናንተ የመጣና እኛ ወደ አላስተማርናችሁ ወደ ሌላ ኢየሱስ የጠራችሁ ቢኖር፥ ወይም ያልተቀበላችሁት ሌላ መንፈስ ቢኖር፥ ወይም ያልተማራችሁት ሌላ ወንጌል ቢኖር ልትጠብቁን ይገባል። 5እኔ ግን ሌሎች ሐዋርያት ከአስተማሩት ያጐደልሁባችሁ የለም ይመስለኛል። #ግሪኩ “ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደማንስ ራሴን አልቈጥርም” ይላል።
ወንጌልን ያለ ዋጋ ስለ ማስተማር
6እኔ በአነጋገሬ አላዋቂ ብሆንም በዕውቀት ግን እንዲሁ አይደለሁም፤ ነገር ግን ሁሉን በሁሉ እገልጥላችኋለሁ። 7ወይስ ራሴን በሁሉ ያዋረድሁ በደልሁ ይሆን? እናንተ ከፍ ከፍ ትሉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ አስተምሬአችኋለሁና። 8እናንተን አገለግል ዘንድ፥ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተቀብዬ፥ ለምግቤ ያህል ወሰድሁ፤ 9#ፊል. 4፥15-18። ከእናንተ ዘንድ በነበርሁበት ጊዜም፥ ስቸገር ገንዘባችሁን አልተመኘሁም።#ግሪኩ “በማንም አልከበድሁም” ይላል። ባልበቃኝም ጊዜ ወንድሞቻችን ከመቄዶንያ መጥተው አሙአሉልኝ፤ በእናንተም ላይ እንዳልከብድባችሁ በሁሉ ተጠነቀቅሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ። 10የክርስቶስ ዕውነት አብሮኝ ይኖራልና፥ ይህቺ ደስታዬ#ግሪኩ “ትምክሕቴ” ይላል። በአካይያ አውራጃ አልተከለከለችብኝም። 11ስለምን ነው? አልወዳችሁምና ነውን? እንደምወድዳችሁስ እግዚአብሔር ያውቃል።
12ነገር ግን ያደረግሁትም ቢሆን፥ የማደርገውም ቢሆን፥ እነርሱ እንደ እኛ የሚመኩበትን ያገኙ ዘንድ፥ ምክንያት የሚሹትን ምክንያት አሳጣቸው ዘንድ ነው። 13የሚተነኰሉ፥ ራሳቸውን የክርስቶስን ሐዋርያት የሚያስመስሉ፥ ዐመፅንም የሚያደርጉ ሐሰተኞች ሐዋርያት አሉና። 14ይህም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ ተለውጦ እንደ ብርሃን መልአክ ይመስላልና። 15መልእክተኞቹም የጽድቅ መላእክትን ቢመስሉ፥ ይህ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜያቸው ግን እንደ ሥራቸው ነው።
ስለ መንፈሳዊ ትምክሕት
16ደግሞም እንዲህ እላለሁ፦ ሰነፍ የሚያደርገኝ አይኑር፤ ያውም ብሆን እኔ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሰነፍ እንኳ ብሆን ተቀበሉኝ። 17ይህም ቢሆን የምናገረው ለእግዚአብሔር የሚገባ አይደለም፤ ነገር ግን ስለዚህች ትምክሕቴ እንደ ሰነፍ እናገራለሁ። 18በሥጋዊ ሥርዐት የሚመኩ ብዙዎች ናቸውና እኔ ደግሞ እመካለሁ። 19እናንተ ልባሞች ስትሆኑ ሰነፎችን መስማት ደስ ያሰኛችኋልና። 20የሚገዙአችሁንና የሚቀሙአችሁን፥ መባያ የሚያደርጓችሁንና የሚታበዩባችሁን፥ ፊታችሁንም በጥፊ የሚመትዋችሁን ትታገሡአቸዋላችሁና። 21እኛ እንደ ደካሞች መስለን እንደ ነበርን፥ ይህን በውርደት እናገራለሁ፤ ነገር ግን ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍራለሁ። 22እነርሱ ዕብራውያን ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ፤ እነርሱ እስራኤላውያን ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ፤ እነርሱ የአብርሃም ልጆች ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ። 23#የሐዋ. 16፥23። እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ቢሆኑም እኔም እንደ ሰነፍ ለራሴ እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ እጅግም ደከምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ። 24#ዘዳ. 25፥3። አይሁድ አንዲት ስትቀር አምስት ጊዜ አርባ አርባ ገረፉኝ። 25#የሐዋ. 16፥22፤ 14፥19። ሦስት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ መቱኝ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ስዋኝ አድሬ፥ ስዋኝ ዋልሁ። 26#የሐዋ. 9፥23፤ 14፥15። በመንገድ ዘወትር መከራ እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከራ ተቀበልሁ፤ ወንበዴዎችም አሠቃዩኝ፤ ዘመዶችም አስጨነቁኝ፤ አሕዛብ መከራ አጸኑብኝ፤ በከተማ መከራ ተቀበልሁ፤ በበረሃም መከራ ተቀበልሁ፤ በባሕርም መከራ ተቀበልሁ፤ ሐሰተኞች መምህራን መከራ አጸኑብኝ። 27በድካምና በጥረት፥ ብዙ ጊዜም ዕንቅልፍ በማጣት፥ በመራብና በመጠማት፥ አብዝቶም በመጾም፥ በብርድና በመራቆት ተቸገርሁ። 28የቀረውንም ነገር ሳልቈጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 29ታሞ እኔ የማላዝንለት ማን ነው? በድሎስ እኔ የማልደነግጥለት ማን ነው?
30መመካት የሚገባ ከሆነስ እኔም በመከራዬ እመካለሁ። 31ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ሐሰት እንደማልናገር ያውቃል። 32#የሐዋ. 9፥23-25። በደማስቆ ከተማ ከንጉሥ አርስጣስዮስ በታች የሆነ የአሕዛብ አለቃ ሊይዘኝ ወድዶ የደማስቆን ከተማ ያስጠብቅ ነበር። 33በቅርጫትም አድርገው በመስኮቱ በኩል በአጥሩ ላይ አወረዱኝ፤ ከእጁም አመለጥሁ።
Currently Selected:
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ