2 ቆሮንቶስ 11:1-15
2 ቆሮንቶስ 11:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በስንፍናዬ እናገር ዘንድ ጥቂት ልትታገሡኝ ይገባ ነበር፤ ቢሆንም በርግጥ ታገሡኝ፤ ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁና። ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ከክርስቶስ የዋህነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። ወደ እናንተ የመጣና እኛ ወደ አላስተማርናችሁ ወደ ሌላ ኢየሱስ የጠራችሁ ቢኖር፥ ወይም ያልተቀበላችሁት ሌላ መንፈስ ቢኖር፥ ወይም ያልተማራችሁት ሌላ ወንጌል ቢኖር ልትጠብቁን ይገባል። እኔ ግን ሌሎች ሐዋርያት ከአስተማሩት ያጐደልሁባችሁ የለም ይመስለኛል። እኔ በአነጋገሬ አላዋቂ ብሆንም በዕውቀት ግን እንዲሁ አይደለሁም፤ ነገር ግን ሁሉን በሁሉ እገልጥላችኋለሁ። ወይስ ራሴን በሁሉ ያዋረድሁ በደልሁ ይሆን? እናንተ ከፍ ከፍ ትሉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ አስተምሬአችኋለሁና። እናንተን አገለግል ዘንድ፥ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተቀብዬ፥ ለምግቤ ያህል ወሰድሁ፤ ከእናንተ ዘንድ በነበርሁበት ጊዜም፥ ስቸገር ገንዘባችሁን አልተመኘሁም። ባልበቃኝም ጊዜ ወንድሞቻችን ከመቄዶንያ መጥተው አሙአሉልኝ፤ በእናንተም ላይ እንዳልከብድባችሁ በሁሉ ተጠነቀቅሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ። የክርስቶስ ዕውነት አብሮኝ ይኖራልና፥ ይህቺ ደስታዬ በአካይያ አውራጃ አልተከለከለችብኝም። ስለምን ነው? አልወዳችሁምና ነውን? እንደምወድዳችሁስ እግዚአብሔር ያውቃል። ነገር ግን ያደረግሁትም ቢሆን፥ የማደርገውም ቢሆን፥ እነርሱ እንደ እኛ የሚመኩበትን ያገኙ ዘንድ፥ ምክንያት የሚሹትን ምክንያት አሳጣቸው ዘንድ ነው። የሚተነኰሉ፥ ራሳቸውን የክርስቶስን ሐዋርያት የሚያስመስሉ፥ ዐመፅንም የሚያደርጉ ሐሰተኞች ሐዋርያት አሉና። ይህም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ ተለውጦ እንደ ብርሃን መልአክ ይመስላልና። መልእክተኞቹም የጽድቅ መላእክትን ቢመስሉ፥ ይህ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜያቸው ግን እንደ ሥራቸው ነው።
2 ቆሮንቶስ 11:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በርግጥም እየታገሣችሁኝ ነው። በእግዚአብሔር ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ እናንተን እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ባል ዐጭቻችኋለሁና። ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰል እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ልቡና ተበላሽቶ ለክርስቶስ ካላችሁ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትወሰዱ እሠጋለሁ። ምክንያቱም አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ ከሰበክንላችሁ ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ፣ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ፣ ወይም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ብትቀበሉ፣ ነገሩን በዝምታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው። እኔ ግን “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም የማንስ አይመስለኝም። የንግግር ችሎታ ባይኖረኝም እንኳ፣ ዕውቀት ግን አለኝ፤ ይህንም በሁሉ መንገድ በሚገባ ግልጽ አድርገንላችኋል። እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ ለእናንተ መስበኬ እንደ ኀጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን? እናንተን ለማገልገል ስል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ። ከእናንተም ጋር ሳለሁ አንዳች ባስፈለገኝ ጊዜ፣ ከመቄዶንያ የመጡ ወንድሞች የሚያስፈልገኝን ስለ ሰጡኝ ለማንም ሸክም አልሆንሁም። በእናንተ ላይ በምንም ነገር ሸክም እንዳልሆን ተጠንቅቄአለሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ። የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ፣ በአካይያ አውራጃ ይህን ትምክሕቴን ማንም ሊገታው አይችልም። ይህን የምለው ለምንድን ነው? ስለማልወድዳችሁ ነውን? እንደምወድዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል። ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን በሥራቸው እየተመኩ ቀን የሚጠብቁትን ሰዎች ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደ ፊትም አደርጋለሁ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው። ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል። እንግዲህ የእርሱ አገልጋዮች፣ የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ የሚያስገርም አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
2 ቆሮንቶስ 11:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም። በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል በነገር ሁሉ ተገልጠንላችኋል። ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን? እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ። ከእናንተም ጋር ሳለሁ በጎደለኝ ጊዜ፥ በማንም አልከበድሁበትም፤ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ሰጥተዋልና፤ በነገርም ሁሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ። የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህት በእኔ ዘንድ በአካይያ አገር አይከለከልም። ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል። ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
2 ቆሮንቶስ 11:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እባካችሁ ታገሡኝ። እንደ አንዲት ንጽሕት ልጃገረድ በድንግልናዋ ለአንድ ባል እንደምትታጭ እኔም እናንተን ለክርስቶስ ስላአጨኋችሁ ስለ እናንተ መንፈሳዊ ቅናት እቀናለሁ። እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ሐሳብ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ያላችሁን ቅንና ንጹሕ የሆነ ታማኝነት ትተዋላችሁ ብዬ እፈራለሁ። አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ የሰበክነውን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም እናንተ የተቀበላችሁትን መንፈስ ሳይሆን ሌላ መንፈስ ብትቀበሉ፥ ወይም የተቀበላችሁትን ወንጌል ሳይሆን ሌላ ወንጌል ብትቀበሉ፥ ዝም ብላችሁ ተሸነፋችሁ ማለት ነው። ነገር ግን እኔ ከነዚህ ታላላቅ ሐዋርያት በምንም ነገር የማንስ አይመስለኝም። በአነጋገር ፈሊጥ ምሁር ባልሆንም እንኳ ዕውቀት አይጐድለኝም፤ ይህንንም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ በግልጥ አስረድተናችኋል። እኔ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ለእናንተ መስበኬና እናንተን ከፍ ለማድረግ ራሴን ማዋረዴ ምናልባት እንደ ኃጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን? እናንተን ለማገልገል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያን ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ። ከእናንተ ጋር ሳለሁ ችግር በደረሰብኝ ጊዜ ከመቄዶንያ የመጡ ወንድሞች በሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ይረዱኝ ስለ ነበር በማንም ሸክም አልሆንኩም፤ እስከ አሁን በእናንተ ላይ በምንም ነገር ሸክም አልሆንኩም፤ ለወደፊትም ሸክም አልሆንባችሁም። የክርስቶስ እውነት በእኔ ውስጥ በመኖሩ እንዳልመካ የሚያደርገኝ በአካይያ አገሮች ማንም የለም። ምክንያቱስ ምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነውን? እንደምወዳችሁስ እግዚአብሔር ያውቃል። እነዚያ ሌሎች ሐዋርያት “እኛም እንደ እነርሱ እንሠራለን” እያሉ የሚመኩበትን ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደፊትም ደግሞ አደርጋለሁ። እንደእነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው። ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ሰይጣን እንኳ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለውጣል። ስለዚህ እነዚህ የሰይጣን አገልጋዮች የጽድቅ አገልጋዮችን ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ አያስደንቅም፤ በመጨረሻ የሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ።
2 ቆሮንቶስ 11:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሞኝነቴን በጥቂቱ ብትታገሡኝ በወደድኩ ነበር፤ ስለሆነም በእርግጥ ታገሡኝ። እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር ቅንዐት እቀናላችኋለሁና። ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ሊኖራችሁ ከሚገባ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትርቁ ብዬ እፈራለሁ። ምክንያቱም አንዱ መጥቶ እኛ ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ሆኖ ብታገኙት፥ በመልካምነታችሁ ትታገሡታላችሁ። ራሴን ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደማንስ አድርጌ አልቆጥርም። በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል ይህንን ግልጽ አድርገንላችኋል። እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ ለእናንተ መስበኬ እንደ ኃጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን? እናንተን ለማገልገል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ እየተቀበልሁ ዘረፍሁ። ከእናንተም ጋር እያለሁ በሚጎድለኝ ጊዜ፥ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ስላሟሉልኝ፥ በማንም ላይ ሸክም አልሆንኩም፤ በማንኛውም መንገድ በእናንተ ላይ ሸክም እንዳልሆን ተጠንቅቄአለሁ፤ እጠነቀቅማለሁ። የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህቴ በአካይያም አገር ዝም የሚያሰኘኝ አይደለም። ስለምን? ስለማልወዳችሁ ይመስላችኋል? እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል። ነገር ግን በሚመኩበት ሥራ ከእኛ እኩል በአቻነት ለመቆጠር የሚፈልጉ ሰዎችን ምክንያት ለማሳጣት፥ አሁን የማደርገውን ወደፊትም እገፋበታለሁ። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡም፥ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አጭበርባሪ ሠራተኞች ናቸው። ይህም አያስገርምም! ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ መስሎ ራሱን ለውጦ ይቀርባል። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች በመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።