1 ጢሞቴዎስ 1:12-19

1 ጢሞቴዎስ 1:12-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኀይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ፤ አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ፤ የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ። “ኀጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ፤” የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኀጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምህረትን አገኘሁ። ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፤ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤

1 ጢሞቴዎስ 1:12-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ የቈጠረኝን፣ ብርታትም የሰጠኝን ጌታችንን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ። ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ የነበርሁ ብሆንም፣ ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረት ተደርጎልኛል፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑት እምነትና ፍቅር ጋራም የጌታችን ጸጋ ተትረፈረፈልኝ። “ክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል እውነተኛና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኀጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ። ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ። እንግዲህ ዘላለማዊ ለሆነው፣ ለማይሞተው፣ ለማይታየውና ብቻውን አምላክ ለሆነው ንጉሥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ምስጋና ይሁን። አሜን። ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ፤ አስቀድሞ ስለ አንተ በተነገረው ትንቢት መሠረት ይህን ትእዛዝ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም እርሱን በመከተል መልካሙን ገድል እንድትጋደል ነው። እምነትና በጎ ኅሊናም ይኑርህ፤ አንዳንዶች ኅሊናቸውን ጥለው ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደሚጠፋ መርከብ እምነታቸውን አጥፍተዋል።

1 ጢሞቴዎስ 1:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቍኦጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ፤ አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ፥ የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ። ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ። ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤

1 ጢሞቴዎስ 1:12-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እኔን ለአገልግሎት በመሾም ታማኝ አድርጎ የቈጠረኝንና የሰጠኝን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግናለሁ። ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን የሰደብኩና ያሳደድኩ፥ ያዋረድኩም ብሆን፤ እርሱ ምሕረት አደረገልኝ፤ እርሱም ይህን ምሕረት ያደረገልኝ እኔ ይህን ሁሉ ያደረግኹት ባለማወቅና ባለማመን ስለ ነበረ ነው። የአምላካችን ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ የእኛ ከሆነው እምነትና ፍቅር ጋር ተትረፍርፎ ተሰጠኝ። “ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል እውነተኛና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ሁሉ የባስሁ ኃጢአተኛ እኔ ነኝ። ነገር ግን ምሕረት ተደረገልኝ፤ ምሕረት የተደረገልኝም ኢየሱስ ክርስቶስ ወሰን የሌለውን ትዕግሥቱን ከሁሉ የባስሁ ኀጢአተኛ በሆንኩት በእኔ ላይ በማሳየቱ በእርሱ ለሚያምኑና የዘለዓለም ሕይወት ለሚያገኙ ምሳሌ እንድሆን ነው። ስለዚህ ለዘለዓለማዊው ንጉሥ፥ ለማይሞተው፥ ለማይታየው፥ ለአንዱ አምላክ ክብርና ምስጋና ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን። ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! ከዚህ ቀደም ስለ አንተ በትንቢት በተነገረው መሠረት የሚከተለውን ትእዛዝ በዐደራ እሰጥሃለሁ፤ ትንቢቱን በመከተል መልካም ጦርነትን ተዋጋ፤ እምነትና መልካም ኅሊና ይኑርህ። አንዳንድ ሰዎች ኅሊናቸውን በመጣላቸው መርከብ በማዕበል እንደሚጠፋ እምነታቸውን አጥፍተዋል።

1 ጢሞቴዎስ 1:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ብርታት የሰጠኝን ጌታችንን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፤ ይሁንና ከዚህ ቀደም ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም የነበርኩ ብሆንም እንኳ ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ፤ የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑት ከእምነትና ከፍቅር ጋር እጅጉን በዛልኝ። “ኀጢአተኞችን ለማዳን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ፤” የሚለው ቃል የታመነና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኀጢአተኞችም ዋነኛው እኔ ነኝ፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ዋነኛ በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ በማሳየት፥ በእርሱ አምነው የዘለዓለም ሕይወትን ለሚያገኙ ምሳሌ እንድሆን አደረገኝ፥ በእዚህም ምክንያት ምሕረትን አገኘሁ። ለዘመናትም ንጉሥ፥ ለማይሞተው፥ ለማይታየው፥ ብቻውን አምላክ ለሆነው መፈራትና ክብር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን። ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! አስቀድሞ ስለ አንተ የተነገረውን ትንቢት ሁሉ መሠረት በማድረግ፥ በእነርሱ መልካም ውጊያን እንድትዋጋ ይህችን ትእዛዝ በአደራ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህን በምታደርግበት ጊዜ ግን እምነትንና በጎ ኅሊናን ይዘህ ይሁን፤ አንዳንዶች ሕሊናን ወደ ጎን በማድረግ፥ በእምነት ረገድ በማዕበል እንደተሰባበረች መርከብ ጠፍተዋል፤