የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 9:1-27

1 ሳሙኤል 9:1-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከብ​ን​ያም ልጆች ስሙ ቂስ የተ​ባለ አንድ ሰው ነበረ፥ እር​ሱም የአ​ብ​ሔል ልጅ፥ የያ​ሬድ ልጅ፥ የባ​ሔር ልጅ፥ የብ​ን​ያም ሰው፥ የአ​ፌቅ ልጅ፥ ጽኑዕ ኀያል ሰው ነበረ። ለእ​ር​ሱም ሳኦል የሚ​ባል የተ​መ​ረጠ መል​ካም ልጅ ነበ​ረው፤ በም​ድር ሁሉ ላይ ከእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ከእ​ርሱ ይልቅ መል​ካም የሆነ ሰው አል​ነ​በ​ረም፤ ከሕ​ዝ​ቡም ሁሉ ይልቅ ከት​ከ​ሻ​ውና ከዚ​ያም በላይ ቁመቱ ዘለግ ያለ ነበረ። የሳ​ኦ​ልም አባት የቂስ አህ​ዮች ጠፍ​ተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦ​ልን፥ “ከብ​ላ​ቴ​ኖቹ አን​ዱን ወስ​ደህ ተነ​ሡና ሄዳ​ችሁ አህ​ዮ​ችን ፈልጉ” አለው። ወደ ተራ​ራ​ማ​ውም ወደ ኤፍ​ሬም ሀገር ሄዱ፤ በሲ​ልካ ምድ​ርም አለፉ፤ አላ​ገ​ኙ​አ​ቸ​ው​ምም፤ በፋ​ስ​ቂም ምድር አለፉ፤ በዚ​ያም አል​ነ​በ​ሩም፤ በኢ​ያ​ሚ​ንም ምድር አለፉ፤ አላ​ገ​ኙ​አ​ቸ​ው​ምም። ወደ መሴፋ ምድ​ርም በደ​ረሱ ጊዜ ሳኦል ከእ​ርሱ ጋር የነ​በ​ረ​ውን ብላ​ቴና፥ “አባቴ ስለ አህ​ዮች ማሰ​ብን ትቶ ስለ እኛ እን​ዳ​ይ​ጨ​ነቅ፥ ና፤ እን​መ​ለስ” አለው። ብላ​ቴ​ና​ውም፥ “እነሆ፥ አንድ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው በዚ​ህች ከተማ አለ፤ እር​ሱም የተ​ከ​በረ ሰው ነው፤ የሚ​ና​ገ​ረው ሁሉ በእ​ው​ነት ይፈ​ጸ​ማል፤ አሁ​ንም ወደ​ዚያ እን​ሂድ፤ ምና​ል​ባት የም​ን​ሄ​ድ​በ​ትን መን​ገድ ይነ​ግ​ረ​ና​ልና” አለው። ሳኦ​ልም አብ​ሮት ያለ​ውን ብላ​ቴና፥ “እነሆ! እን​ሄ​ዳ​ለን፤ ነገር ግን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው ምን እን​ወ​ስ​ድ​ለ​ታ​ለን? እን​ጀራ ከከ​ረ​ጢ​ታ​ችን አል​ቆ​አ​ልና፤ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው የም​ን​ወ​ስ​ድ​ለት ምንም የለ​ንም” አለው። ብላ​ቴ​ናው ደግሞ ለሳ​ኦል መልሶ፥ “እነሆ፥ በእጄ የብር ሰቅል ሩብ አለኝ፤ እር​ሱ​ንም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው ትሰ​ጠ​ዋ​ለህ፤ የም​ን​ሄ​ድ​በ​ትን መን​ገ​ድም ይነ​ግ​ረ​ናል። ቀድሞ ነቢ​ዩን ባለ ራእይ ይሉት ነበ​ርና አስ​ቀ​ድሞ በእ​ስ​ራ​ኤል ዘንድ ሰው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ለመ​ጠ​የቅ ሲሄድ፦ ኑ፤ ወደ ባለ ራእይ እን​ሂድ ይል ነበር።” ሳኦ​ልም ብላ​ቴ​ና​ውን፥ “የተ​ና​ገ​ር​ኸው ነገር መል​ካም ነው፤ ና፤ እን​ሂድ” አለ​ውና የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው ወዳ​ለ​በት ከተማ ሄዱ። በከ​ተ​ማ​ዪ​ቱም ዳገት በወጡ ጊዜ ቈነ​ጃ​ጅት ውኃ ሊቀዱ ሲወጡ አገ​ኙና፥ “ባለ ራእይ በዚህ አለ ወይ?” አሉ​አ​ቸው። ቈነ​ጃ​ጅ​ቱም፥ “አዎን እነሆ፥ በፊ​ታ​ችሁ ነው። ዛሬ ወደ ከተ​ማ​ዪቱ መጥ​ቶ​አ​ልና፥ ዛሬም ሕዝቡ በባማ ኮረ​ብታ ላይ መሥ​ዋ​ዕት ማቅ​ረብ አለ​ባ​ቸ​ውና። ወደ ከተ​ማ​ዪ​ቱም በገ​ባ​ችሁ ጊዜ ለመ​ብ​ላት ወደ ባማ ኮረ​ብታ ሳይ​ወጣ በከ​ተ​ማው ውስጥ ታገ​ኙ​ታ​ላ​ችሁ፤ መሥ​ዋ​ዕ​ታ​ቸ​ውን እርሱ የሚ​ባ​ርክ ስለ​ሆነ እርሱ ሳይ​ወጣ ሕዝቡ ምንም አይ​ቀ​ም​ሱ​ምና፥ ከዚ​ያም በኋላ እን​ግ​ዶች ይበ​ላ​ሉና፤ በዚ​ህም ጊዜ ታገ​ኙ​ታ​ላ​ች​ሁና አሁን ውጡ” አሉ​አ​ቸው። ወደ ከተ​ማ​ዪ​ቱም ወጡ፤ በከ​ተ​ማ​ዪ​ቱም መካ​ከል በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ሳሙ​ኤል ወደ ባማ ኮረ​ብታ ለመ​ው​ጣት ወደ እነ​ርሱ መጣ። ገናም ሳኦል ሳይ​መጣ ከአ​ንድ ቀን በፊት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለሳ​ሙ​ኤል ጆሮ​ውን ከፈ​ተ​ለት፥ እን​ዲ​ህም አለው፥ “ነገ በዚ​ህች ሰዓት ከብ​ን​ያም ሀገር አንድ ሰው እል​ክ​ል​ሃ​ለሁ፤ ልቅ​ሶ​አ​ቸው ወደ እኔ ስለ ደረሰ የሕ​ዝ​ቤን ሥቃ​ያ​ቸ​ውን ተመ​ል​ክ​ች​አ​ለ​ሁና ለሕ​ዝቤ ለእ​ስ​ራ​ኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀ​ባ​ዋ​ለህ፤ ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም እጅ ሕዝ​ቤን ያድ​ናል።” ሳሙ​ኤ​ልም ሳኦ​ልን ባየ ጊዜ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ “ያ የነ​ገ​ር​ሁህ ሰው እነሆ፤ እር​ሱም በሕ​ዝቤ ላይ ይነ​ግ​ሣል” አለው። ሳኦ​ልም በበሩ ወደ ሳሙ​ኤል ቀርቦ፥ “የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ፥ እባ​ክህ፥ ንገ​ረኝ” አለው። ሳሙ​ኤ​ልም መልሶ ሳኦ​ልን፥ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬም ከእኔ ጋር ወደ ባማ ኮረ​ብታ በፊቴ ውጣና ምሳ ብላ፤ ነገም በጥ​ዋት አሰ​ና​ብ​ት​ሃ​ለሁ፤ በል​ብ​ህም ያለ​ውን ነገር ሁሉ እነ​ግ​ር​ሃ​ለሁ፤ ከሦ​ስት ቀንም በፊት የጠፉ አህ​ዮ​ችህ ተገ​ኝ​ተ​ዋ​ልና ልብ​ህን አታ​ስ​ጨ​ን​ቀው። የእ​ስ​ራ​ኤል መል​ካም ምኞት ለማን ነው? ለአ​ን​ተና ለአ​ባ​ትህ ቤት አይ​ደ​ለ​ምን?” አለው። ሳኦ​ልም መልሶ፥ “እኔ ከእ​ስ​ራ​ኤል ነገ​ዶች ከሚ​ያ​ንስ ወገን የሆ​ንሁ ብን​ያ​ማዊ ሰው አይ​ደ​ለ​ሁ​ምን? ወገ​ኔስ ከብ​ን​ያም ነገድ ወገ​ኖች ሁሉ የሚ​ያ​ንስ አይ​ደ​ለ​ምን? እን​ዲ​ህስ ያለ​ውን ነገር ለምን ነገ​ር​ኸኝ?” አለ። ሳሙ​ኤ​ልም ሳኦ​ል​ንና ብላ​ቴ​ና​ውን ወስዶ ወደ አዳ​ራሽ አገ​ባ​ቸው፥ ሰባ ሰዎ​ችም ምሳ በሚ​በ​ሉ​በት በም​ር​ፋቁ ራስ አስ​ቀ​መ​ጣ​ቸው፤ ሳሙ​ኤ​ልም ወጥ ቤቱን፥ “በአ​ንተ ዘንድ አኑ​ረው ብዬ የሰ​ጠ​ሁ​ህን እድል ፋንታ አምጣ” አለው። ወጥ​ቤ​ቱም ወር​ቹን አም​ጥቶ በሳ​ኦል ፊት አኖ​ረው። ሳሙ​ኤ​ልም፥ “ሳኦ​ልን ለም​ስ​ክር ከባ​ል​ን​ጀ​ራህ ተለ​ይቶ ቀር​ቦ​ል​ሃ​ልና እነሆ፥ በል​ተህ የተ​ረ​ፈ​ህን በፊ​ትህ አኑር” አለው። በዚ​ያም ቀን ሳኦል ከሳ​ሙ​ኤል ጋር በላ። ከባማ ኮረ​ብ​ታም ወደ ከተ​ማ​ዪቱ ወረዱ፤ ሳሙ​ኤ​ልም ለሳ​ኦል በሰ​ገ​ነቱ ላይ መኝታ አዘ​ጋ​ጀ​ለት፤ እር​ሱም ተኛ። ማል​ደ​ውም ተነሡ፤ በነ​ጋም ጊዜ ሳሙ​ኤል ሳኦ​ልን፥ “ከሰ​ገ​ነቱ ላይ ጠርቶ፦ ተነ​ሣና ላሰ​ና​ብ​ትህ” አለው። ሳኦ​ልም ተነሣ፤ እር​ሱና ሳሙ​ኤ​ልም ሁለቱ ወደ ሜዳ ወጡ። እነ​ር​ሱም በከ​ተ​ማ​ዪቱ ዳር ሲወ​ርዱ ሳሙ​ኤል ሳኦ​ልን፥ “ብላ​ቴ​ናው ወደ ፊታ​ችን እን​ዲ​ያ​ልፍ እዘ​ዘው፤ አንተ ግን ከእኔ ጋር ከዚህ ቁምና የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል ስማ” አለው። ብላ​ቴ​ና​ውም አለፈ።

1 ሳሙኤል 9:1-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቂስ የተባለ አንድ ታዋቂ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፣ የጽሮር ልጅ፣ የብኮራት ልጅ፣ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ ነበር። ቂስም ከእስራኤል ልጆች መካከል በመልከ ቀናነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት፣ ቁመቱም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ፣ ሳኦል የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው። በዚያም ጊዜ የሳኦል አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን፣ “ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱን ይዘህ ሂድና አህዮቹን ፈልግ” አለው። ስለዚህ በኰረብታማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አካባቢ ባለው ስፍራ ሁሉ ተዘዋወረ፤ ሆኖም አህዮቹን አላገኙም። ወደ ሻዕሊምም ግዛት ዘልቀው ገቡ፤ አህዮቹ ግን በዚያም አልነበሩም። እንዲሁም በብንያም ግዛት በኩል ዐለፈ፤ ሆኖም አላገኟቸውም። ወደ ጹፍ ግዛት በደረሱ ጊዜ ሳኦል አብሮት የነበረውን አገልጋይ፣ “አባቴ ይህን ጊዜ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር፣ ና እንመለስ” አለው። አገልጋዩ ግን፣ “እነሆ፤ በዚህች ከተማ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱም በጣም የተከበረ ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረን ይሆናልና ወደዚያ እንሂድ” ሲል መለሰለት። ሳኦልም አገልጋዩን፣ “መሄዱን እንሂድ፤ ነገር ግን ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ ዐልቋል። ለእግዚአብሔር ሰው የምናበረክተውም ስጦታ የለንም፤ ታዲያ ምን አለን?” አለው። አገልጋዩ፣ “እኔ የአንድ ሰቅል ጥሬ ብር ሩብ አለኝ፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረን ዘንድ ገንዘቡን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጠዋለሁ” ሲል በድጋሚ መለሰለት። ቀደም ሲል በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፣ “ኑ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ” ይል ነበር፤ ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበርና። ሳኦልም፣ “መልካም፤ ና እንሂድ” አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። በከተማዪቱ መዳረሻ ያለውን ኰረብታ በመውጣት ላይ ሳሉ፣ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው፣ “ባለ ራእዩ እዚህ ነውን?” ሲሉ ጠየቁ። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “አዎን አለ፤ እነሆ፤ ከፊታችሁ ነው፤ ፈጠን በሉ፤ ሕዝቡ በማምለኪያው ኰረብታ ላይ መሥዋዕት ስለሚያቀርብ፣ ወደ ከተማችን ገና ዛሬ መምጣቱ ነው፤ ወደ ከተማዪቱም በገባችሁ ጊዜ፣ ለመብላት ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን እርሱ መባረክ ስላለበት፣ እርሱ እስኪመጣ ድረስ ሕዝቡ መብላት አይጀምርም፤ ከዚያ በኋላ የተጋበዘው ሕዝብ ይበላል፤ አሁኑኑ ውጡ፤ ወዲያው ታገኙታላችሁ።” እነርሱም ወደ ከተማዪቱ ወጡ፤ ወደ ከተማዪቱም በመግባት ላይ ሳሉ፣ እነሆ፤ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ለመውጣት እነርሱ ወዳሉበት አቅጣጫ መጣ። ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ለሳሙኤል ይህን እንዲህ ሲል ገልጦለት ነበር፤ “ነገ በዚህ ጊዜ ከብንያም ምድር አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንዲሆን ቅባው፤ እርሱም ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል። እነሆ፤ ሕዝቤን ከላይ ተመልክቻለሁ፤ ጩኸቱ ከእኔ ዘንድ ደርሷልና።” ሳሙኤል ሳኦልን ባየው ጊዜ እግዚአብሔር፣ “ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፤ እርሱም ሕዝቤን ይገዛል” አለው። ሳኦልም በቅጥሩ በር ላይ ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ፣ “የባለ ራእዩ ቤት የት እንደ ሆነ ትነግረኛለህ?” ሲል ጠየቀው። ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ ከፊቴ ቀድማችሁ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ውጡ፤ ነገ ጧት አሰናብትሃለሁ፤ በልብህ ያለውንም እነግርሃለሁ። ከሦስት ቀን በፊት ስለ ጠፉብህ አህዮች አትጨነቅ፤ ተገኝተዋልና። የእስራኤል ምኞት ሁሉ ያዘነበለው ወደ አንተና ወደ አባትህ ቤተ ሰብ ሁሉ አይደለምን?” ሳኦልም፣ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ወገን አይደለሁምን? ጐሣዬስ ከብንያም ነገድ ጐሣዎች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? ታዲያ እንዲህ ያለውን ነገር ስለ ምን ትነግረኛለህ?” ብሎ መለሰለት። ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ አዳራሹ አመጣ፤ ከተጋበዙትም ሠላሳ ያህል ሰዎች ሁሉ በላይ አስቀመጣቸው። ሳሙኤልም ወጥ ቤቱን፣ “ለይተህ አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን የሥጋ ብልት አምጣው” አለው። ወጥ ቤቱም የጭኑን ሥጋ እንዳለ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠው። ሳሙኤልም፣ “ይህ፣ ‘እንግዶችን ጋብዣለሁ’ ካልሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ስለሆነ ብላው” አለው። ሳኦልም በዚያች ዕለት ከሳሙኤል ጋር አብሮ በላ። ከማምለኪያው ኰረብታ ወደ ከተማዪቱ ከወረዱ በኋላ ሳሙኤል በቤቱ ሰገነት ላይ ከሳኦል ጋር ተነጋገረ። በማለዳ ተነሡ፤ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፣ “ላሰናብትህ ስለሆነ ተዘጋጅ” አለው። ሳኦልም ተዘጋጅቶ እንዳበቃ፣ ከሳሙኤል ጋር ተያይዘው ወደ ውጭ ወጡ። ወደ ከተማዪቱ ዳርቻ እየወረዱ ሳለ፣ ሳሙኤል ሳኦልን፣ “አገልጋይህ ወደ ፊት ቀድሞን እንዲሄድ ንገረው” አለው፤ አገልጋዩም እንደ ተነገረው አደረገ፤ ከዚህ በኋላ ሳሙኤል፣ “አንተ ግን ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት እነግርህ ዘንድ ለጥቂት ጊዜ እዚህ ቈይ” አለው።

1 ሳሙኤል 9:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፥ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጽሮር ልጅ፥ የብኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ፥ ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ። ለእርሱም ሳኦል የሚባል የተመረጠ መልካም ልጅ ነበረው፥ ከእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ይልቅ መልካም የሆነ ሰው አልነበረም፥ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻውና ከዚያም በላይ ቁመቱ ዘለግ ያለ ነበረ። የሳኦልም አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፥ ቂስም ልጁን ሳኦልን፦ ከብላቴኖቹ አንዱን ወስደህ ተነሣ፥ አህዮችንም ለመሻት ሂድ አለው። በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አለፉ፥ አላገኙአቸውምም፥ በሻዕሊም ምድርም አለፉ፥ በዚያም አልነበሩም፥ በብንያም ምድርም አለፉ፥ አላገኙአቸውምም። ወደ ጹፍ ምድር በመጡ ጊዜም ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን ብላቴና፦ አባቴ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ ስለ እኛ እንዳይጨነቅ፥ ና፥ እንመለስ አለው። እርሱም፦ እነሆ፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለ፥ እርሱም የተከበረ ሰው ነው፥ የሚናገረውም ሁሉ በእውነት ይፈጸማል፥ አሁን ወደዚያ እንሂድ፥ ምናልባት የምንሄድበትን መንገድ ይነግረናል አለው። ሳኦልም ብላቴናውን፦ እነሆ፥ እንሄዳለን፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሰው ምን እናመጣለታለን? እንጀራ ከከረጢታችን አልቆአልና፥ እጅ መንሻም የለንምና ለእግዚአብሔር ሰው የምናመጣለት ምን አለን? አለው። ብላቴናው ደግሞ ለሳኦል መልሶ፦ እነሆ፥ በእጄ የሰቅል ብር ሩቡ አለኝ፥ እርሱንም መንገዳችንን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጣለሁ አለ። ዛሬ ነቢይ የሚባለው ቀድሞ ባለ ራእይ ይባል ነበርና አስቀድሞ በእስራኤል ዘንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፦ ኑ፥ ወደ ባለ ራእይ እንሂድ ይል ነበር። ሳኦልም ብላቴናውን፦ የተናገረኸው ነገር መልካም ነው፥ ና፥ እንሂድ አለውና የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። በከተማይቱም ዳገት በወጡ ጊዜ ቆነጃጅት ውኃውን ሊቀዱ ሲወጡ አገኙና፦ ባለ ራእይ በዚህ አለ ወይ? አሉአቸው። እነርሱም፦ አዎን፥ እነሆ፥ በፊታችሁ ነው፥ ዛሬ ወደ ከተማይቱ መጥቶአልና፥ ዛሬም ሕዝቡ በኮረብታው ላይ ባለው መስገጃ መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸውና ፈጥናችሁ ውጡ። ወደ ከተማይቱም በገባችሁ ጊዜ መሥዋዕቱን እርሱ የሚባርክ ስለ ሆነ እርሱ ሳይወጣ ሕዝቡ ምንም አይቀምሱምና፥ ከዚያም በኋላ የተጠሩት ይበላሉና ለመብላት ወደ ኮረብታው መስገጃ ሳይወጣ ታገኙታላችሁ፥ በዚህም ጊዜ ታገኙታላችሁና አሁን ውጡ አሉአቸው። ወደ ከተማይቱም ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ሳሙኤል ወደ ኮረብታው መስገጃ ለመውጣት ወደ እነርሱ መጣ። ገናም ሳኦል ሳይመጣ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ ብሎ ገልጦለት ነበር፦ ነገ በዚህች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድድልሃለሁ፥ ልቅሶአቸው ወደ እኔ የደረስ ሕዝቤን ተመልክቻለሁና ለሕዝቤ ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ፥ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ሕዝቤን ያድናል። ሳሙኤልም ሳኦልን ባየ ጊዜ እግዚአብሔር፦ ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፥ እርሱም በሕዝቤ ላይ ይሠለጥናል አለው። ሳኦልም በበሩ ወደ ሳሙኤል ቀርቦ፦ የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው። ሳሙኤልም መልሶ ሳኦልን፦ ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከእኔ ጋር ትበላላችሁና በፊቴ ወደ ኮረብታው መስገጃ ውጡ፥ ነገም አሰናብትሃለሁ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ እነግርሃለሁ፥ ከሦስት ቀንም በፊት የጠፉ አህዮችህ ተገኝተዋልና ልብህን አትጣልባቸው። የእስራኤልም ምኞት ለማን ነው? ለአንተና ለአባትህ ቤት አይደለምን? አለው። ሳኦልም መልሶ፦ እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ? አለ። ሳሙኤልም ሳኦልንና ብላቴናውን ወስዶ ወደ አዳራሽ አገባቸው፥ በመርፈቂያውም ራስ አስቀመጣቸው፥ የተጠሩትም ሠላሳ ሰዎች ያህል ነበሩ። ሳሙኤልም ወጥቤቱን፦ በአንተ ዘንድ አኑረው ብዬ የሰጠሁህን እድል ፈንታ አምጣ አለው። ወጥቤቱም ጭኑንና በእርሱ ላይ የነበረውን አምጥቶ በሳኦል ፊት አኖረው። ሳሙኤልም፦ ሕዝቡን ከጠራሁ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተጠብቆአልና እነሆ፥ የተቀመጠልህን በፊትህ አኑረህ ብላው አለ። በዚያም ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር በላ። ከኮረብታውም መስገጃ ወደ ከተማይቱ ወረዱ፥ ሳሙኤልም ለሳኦል በሰገነቱ ላይ መኝታ አዘጋጀለት፥ እርሱም ተኛ። ማልዶም ተነሡ፥ በነጋም ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፦ ተነሣና ላስናብትህ አለው። ሳኦልም ተነሣ፥ እርሱና ሳሙኤልም ሁለቱ ወደ ሜዳ ወጡ። እነርሱም በከተማይቱ ዳር ሲወርዱ ሳሙኤል ሳኦልን፦ ብላቴናውን ወደ ፊታችን እንዲያልፍ እዘዘው፥ አንተ ግን የእግዚአብሔርን ቃል አሰማህ ዘንድ በዚህ ቁም አለው። ብላቴናውም አለፈ።

1 ሳሙኤል 9:1-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከብንያም ነገድ ቂስ ተብሎ የሚጠራ ታዋቂነት ያለው አንድ ባለጸጋ ሰው ነበር፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጸሮር የልጅ ልጅ ሲሆን ከአፊሐ ጐሣ ወገን የበኮራት ቤተሰብ ነበር። ቂስም በመልከ ቀናነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሳኦል ተብሎ የሚጠራ ልጅ ነበረው፤ ሳኦልም ከትከሻው ዘለል፥ በቁመት ከሕዝቡ ሁሉ ይልቅ መለል ያለ ነበር፤ በመልከቀናነቱም ከሁሉ ይበልጥ ነበር። የሳኦል አባት ቂስ፥ አህዮቹ ጠፍተውበት ነበር፤ ስለዚህም ልጁን ሳኦልን “ከአገልጋዮች አንዱን ይዘህ ሂድና የጠፉትን አህዮች ፈልግ” ብሎ አዘዘው። ሳኦልና አገልጋዩም ተነሥተው በተራራማው የኤፍሬም አገርና በሻሊሻ ምድር በኩል አልፈው አህዮቹን መፈለግ ጀመሩ፤ ነገር ግን አህዮቹን ማግኘት አልቻሉም፤ ከዚያም በሻዕሊም ምድር በኩል አልፈው ሳያገኙአቸው ቀሩ፤ እንደገናም በብንያም ግዛት በኩል አለፉ፤ ይሁን እንጂ አሁንም አህዮቹን ማግኘት አልቻሉም። ወደ ጹፍ ምድር በደረሱ ጊዜ ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን አገልጋይ፦ “ከእንግዲህ ወዲህ አባቴ ስለ አህዮቹ ማሰቡ ቀርቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር አሁንስ ወደ ቤት እንመለስ” አለው። አገልጋዩም “ቈይ! እስቲ በዚህች ከተማ በጣም የተከበረ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱ የሚናገረው ቃል ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ ስለዚህም ወደ እርሱ እንሂድ፤ ምናልባትም አህዮቹን የት ማግኘት እንደምንችል እርሱ ሊነግረን ይችል ይሆናል” ሲል መለሰለት። ሳኦልም “መሄዱንስ እንሂድ፤ ነገር ግን ለዚያ ለእግዚአብሔር ሰው ምን ዐይነት ስጦታ ልናበረክትለት እንችላለን፤ ስንቃችንም እንኳ ከስልቻችን አልቆአል፤ ታዲያ ሌላ የምንሰጠው ነገር አለ እንዴ?” አለው። አገልጋዩም “እነሆ እኔ የአንድ ጥሬ ብር አንድ አራተኛው እጅ አለችኝ፤ እርስዋን እሰጠዋለሁ፤ እርሱም አህዮቹን የት ማግኘት እንደምንችል ይነግረናል” ሲል መለሰ። በቀድሞ ዘመን በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲፈልግ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ ይል ነበር፤ አሁን ነቢይ የሚባለው በዚያን ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበር። ሳኦልም አገልጋዩን “መልካም ነው እንሂድ!” አለው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው ወደ አለበት ከተማ ሄዱ። በዳገቱ አድርገው ወደ ከተማው ሲወጡ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው “ባለ ራእይ እዚህ አለን?” ብለው ጠየቁአቸው። ልጃገረዶቹም “አዎን! እነሆ፥ ሕዝቡ ዛሬ በኮረብታው ላይ መሥዋዕትን ስለሚያቀርብ ባለራእዩ ወደ ከተማይቱ መጥቶአልና ፈጥናችሁ ድረሱበት፤ ወደ ከተማው እንደ ገባችሁ ለመብላት ወደ ኮረብታው ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ፤ መሥዋዕቱን መባረክ ስላለበት ሕዝቡ እርሱ ከመምጣቱ በፊት አይበሉም፤ ከዚያም በኋላ ተጋባዦቹ ይበላሉ፤ ፈጥናችሁ ውጡ፤ አሁን ታገኙታላችሁ” አሉአቸው። ከዚያም በኋላ ሳኦልና አገልጋዩ ወደ ከተማይቱ ወጡ፤ ወደ ከተማይቱም በመግባት ላይ ሳሉ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ስፍራ ለማለፍ ወደ እነርሱ አቅጣጫ ሲመጣ አዩት። ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ለሳሙኤል እንዲህ ብሎ ገልጦለት ነበር፤ “ነገ በዚህ ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እልክልሃለሁ፤ ጩኸታቸው ወደ እኔ ስለ ደረሰ ወደ ሕዝቤ ተመልክቼአለሁና ከፍልስጥኤማውያን ጭቈና ሕዝቤን ስለሚያድን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ አድርገህ ቀባው።” ሳሙኤልም ሳኦልን ባየው ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሳሙኤልን “ያ የነገርኩህ ሰው እነሆ ይህ ነው፤ እርሱ ለሕዝቤ መሪ ይሆናል” አለው። ሳኦልም በቅጽሩ በር አጠገብ ወደነበረው ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ “የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ” አለው። ሳሙኤልም ሳኦልን፦ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ ከእኔ በፊት ወደ ማምለኪያው ቀድመህ ውጣ፤ ነገ ጧት በልብህ ያለውን ሁሉ ነግሬህ አሰናብትሃለሁ፤ ከሦስት ቀን በፊት የጠፉት አህዮችህ ተገኝተዋልና ስለ እነርሱ አትጨነቅ፤ ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ምኞት ማንን ለማግኘት ይመስልሃል? እነርሱ የሚፈልጉት አንተንና የአባትህን ቤተሰብ አይደለምን?” አለው። ሳኦልም “እኔ ከእስራኤል ነገዶች መካከል በተለይ ታናሽ የሆነው የብንያም ነገድ ተወላጅ ነኝ፤ በዚሁም ነገድ ውስጥ እንኳ የእኔ ቤተሰብ በጣም አነስተኛ ነው፤ ታዲያ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለእኔ ስለምን ትነግረኛለህ?” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ሳኦልንና አገልጋዩን እየመራ ወደ ታላቁ አዳራሽ አስገብቶ ብዛታቸው ሠላሳ የሚሆኑ እንግዶች በተቀመጡበት ገበታ ከሁሉ በላይ የሆነውን የክብር ቦታ ሰጣቸው። ሳሙኤልም የወጥ ቤቱን ሠራተኛ ጠርቶ “ለብቻው አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን ብልት ሥጋ አምጣ” አለው፤ ስለዚህም የወጥቤቱ ሠራተኛ ምርጥ የሆነውን የታናሽ ብልት ሥጋ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን “ተመልከት፤ ይህ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ምርጥ ሥጋ ነው፤ እኔ ከጋበዝኳቸው እንግዶች ጋር ሆነህ እንድትበላ ያስቀመጡልህ ስለ ሆነ እርሱን ተመገብ” አለው። ስለዚህም በዚያ ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር አብሮ ተመገበ፤ ከማምለኪያውም ስፍራ ወርደው ወደ ከተማይቱ በገቡ ጊዜ በሳሙኤል ቤት ሰገነት ላይ ለሳኦል አልጋ ተዘጋጀለት፤ እርሱም እዚያ ተኝቶ ዐደረ። በነጋም ጊዜ ማለዳ ሳሙኤል ከሰገነቱ ላይ ሳኦልን ጠርቶ “እንግዲህ ተነሥ፤ ላሰናብትህና መንገድህን ቀጥል” አለው፤ ሳኦልም ከመኝታው ተነሣ፤ እርሱና ሳሙኤልም አብረው ወደ መንገዱ ሄዱ፤ ወደ ከተማይቱም ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን “አገልጋይህ ቀድሞን ወደ ፊት እንዲሄድ ንገረው” አለው፤ አገልጋዩም ቀድሞ ከሄደ በኋላ ሳሙኤል ሳኦልን እንደገና “አንተ እዚህ ትንሽ ቈይ፤ እኔም እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው።

1 ሳሙኤል 9:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጸሮር ልጅ፥ የበኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፊሐ ልጅ ነበር። ቂስም ከእስራኤል ልጆች መካከል በመልከ ቀናነት ተወዳዳሪ የማይገኝለት፥ ቁመቱም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ፥ ሳኦል የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው። በዚያም ጊዜ የሳኦል አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን፥ “ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱን ይዘህ ሂድና አህዮቹን ፈልግ” አለው። ስለዚህ በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አካባቢ ባለው ስፍራ ሁሉ ተዘዋወረ፤ ሆኖም አህዮቹን አላገኘም። ወደ ሻዕሊምም ግዛት ዘልቀው ገቡ፤ አህዮቹ ግን በዚያም አልነበሩም። ከዚያም በብንያም ምድር በኩል አለፉ፤ ሆኖም አላገኟቸውም። ወደ ጹፍ ምድር በደረሱ ጊዜ ሳኦል አብሮት የነበረውን አገልጋይ፥ “አባቴ ይህን ጊዜ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር፥ ና እንመለስ” አለው። አገልጋዩ ግን፥ “እነሆ፤ በዚህች ከተማ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱም በጣም የተከበረ ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ሊነግረን ይችል ይሆናልና ወደዚያ እንሂድ” ሲል መለሰለት። ሳኦልም አገልጋዩን፥ “ብንሄድስ ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ አልቋአል፤ ለዚያ የእግዚአብሔር ሰው የምንሰጠው ስጦታ የለንም፤ ምን አለን?” አለው። አገልጋዩ፦ “እነሆ፥ እኔ የአንድ ጥሬ ብር አንድ አራተኛው እጅ አለኝ፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጠዋለሁ” ሲል በድጋሚ ለሳኦል መለሰለት። ቀደም ሲል በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፥ “ኑ፥ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ” ይል ነበር፤ ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበርና። ሳኦልም፥ “መልካም፤ ና እንሂድ” አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። በከተማዪቱ መዳረሻ ያለውን ኰረብታ በመውጣት ላይ ሳሉ፥ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው፥ “ባለ ራእዩ እዚህ አለን?” ሲሉ ጠየቋቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “አዎን አለ፤ እነሆ፤ ከፊታችሁ ነው፤ ፈጠን በሉ፤ ሕዝቡ በማምለኪያው ኰረብታ ላይ መሥዋዕት ስለሚያቀርብ፥ ወደ ከተማችን ገና ዛሬ መምጣቱ ነው፤ ወደ ከተማዪቱም በገባችሁ ጊዜ፥ ለመብላት ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን እርሱ መባረክ ስላለበት ሕዝቡ እርሱ ከመምጣቱ በፊት አይበላም፤ ከዚያ በኋላ የተጋበዘው ሕዝብ ይበላል፤ አሁኑኑ ውጡ፤ ወዲያው ታገኙታላችሁ።” እነርሱም ወደ ከተማይቱ ወጡ፤ ወደ ከተማይቱም በመግባት ላይ ሳሉ፥ እነሆ፤ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ለመውጣት እነርሱ ወዳሉበት አቅጣጫ መጣ። ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት ጌታ ለሳሙኤል እንዲህ ሲል ገልጦለት ነበር፤ “ነገ በዚህ ጊዜ ከብንያም ምድር አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንዲሆን ቀባው፤ እርሱም ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል። እነሆ፤ ሕዝቤን ከላይ ተመልክቻለሁ፤ የስቃይ ጩኸቱ ከእኔ ዘንድ ደርሷልና።” ሳሙኤል ሳኦልን ባየው ጊዜ ጌታ፥ “ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ! እርሱም ሕዝቤን ይገዛል” አለው። ሳኦልም በቅጥሩ በር ላይ ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ፥ “የባለ ራእዩ ቤት የት እንደሆነ ትነግረኛለህ?” ሲል ጠየቀው። ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ፤ ከፊቴ ቀድማችሁ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ውጡ፤ ነገ ጠዋት አሰናብትሃለሁ፤ በልብህ ያለውንም እነግርሃለሁ። ተገኝተዋልና፥ ከሦስት ቀን በፊት ስለ ጠፉብህ አህዮች አትጨነቅ። የእስራኤል ምኞት ሁሉ ያዘነበለው ወደ ማን ነው? ወደ አንተና ወደ አባትህ ቤተሰብ ሁሉ አይደለምን?” ሳኦልም፥ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ወገን አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? ታዲያ እንዲህ ያለውን ነገር ስለምን ትነግረኛለህ?” ብሎ መለሰለት። ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ አዳራሹ አመጣ፤ ከተጋበዙትም ሠላሳ ያህል ሰዎች ሁሉ በላይ አስቀመጣቸው። ሳሙኤልም ወጥ ቤቱን፥ “ለይተህ አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን የሥጋ ብልት አምጣው” አለው። ወጥ ቤቱም የጭኑን ሥጋ እንዳለ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠው። ሳሙኤልም፥ “ይህ፥ እንግዶችን ጋብዣለሁ ካልሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ፥ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ስለሆነ ብላው” አለው። ሳኦልም በዚያች ዕለት ከሳሙኤል ጋር አብሮ በላ። ከማምለኪያው ኰረብታ ወደ ከተማዪቱ ከወረዱ በኋላ ሳሙኤል በቤቱ ሰገነት ላይ ከሳኦል ጋር ተነጋገረ። በነጋም ጊዜ በማለዳ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፥ “ላሰናብትህ ስለሆነ ተዘጋጅ” አለው። ሳኦልም ተዘጋጅቶ እንዳበቃ፥ ከሳሙኤል ጋር ተያይዘው ወደ ውጭ ወጡ። ወደ ከተማዪቱ ዳርቻ እየወረዱ ሳለ፥ ሳሙኤል ሳኦልን፥ “አገልጋይህ ወደ ፊት ቀድሞን እንዲሄድ ንገረው፤ አገልጋይህም እንዳለፈ፥ አንተ ግን ከጌታ የተላከ መልእክት እንድነግርህ ለጥቂት ጊዜ እዚህ ቆይ” አለው።