ከብንያም ነገድ ቂስ ተብሎ የሚጠራ ታዋቂነት ያለው አንድ ባለጸጋ ሰው ነበር፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጸሮር የልጅ ልጅ ሲሆን ከአፊሐ ጐሣ ወገን የበኮራት ቤተሰብ ነበር። ቂስም በመልከ ቀናነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሳኦል ተብሎ የሚጠራ ልጅ ነበረው፤ ሳኦልም ከትከሻው ዘለል፥ በቁመት ከሕዝቡ ሁሉ ይልቅ መለል ያለ ነበር፤ በመልከቀናነቱም ከሁሉ ይበልጥ ነበር። የሳኦል አባት ቂስ፥ አህዮቹ ጠፍተውበት ነበር፤ ስለዚህም ልጁን ሳኦልን “ከአገልጋዮች አንዱን ይዘህ ሂድና የጠፉትን አህዮች ፈልግ” ብሎ አዘዘው። ሳኦልና አገልጋዩም ተነሥተው በተራራማው የኤፍሬም አገርና በሻሊሻ ምድር በኩል አልፈው አህዮቹን መፈለግ ጀመሩ፤ ነገር ግን አህዮቹን ማግኘት አልቻሉም፤ ከዚያም በሻዕሊም ምድር በኩል አልፈው ሳያገኙአቸው ቀሩ፤ እንደገናም በብንያም ግዛት በኩል አለፉ፤ ይሁን እንጂ አሁንም አህዮቹን ማግኘት አልቻሉም። ወደ ጹፍ ምድር በደረሱ ጊዜ ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን አገልጋይ፦ “ከእንግዲህ ወዲህ አባቴ ስለ አህዮቹ ማሰቡ ቀርቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር አሁንስ ወደ ቤት እንመለስ” አለው። አገልጋዩም “ቈይ! እስቲ በዚህች ከተማ በጣም የተከበረ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱ የሚናገረው ቃል ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ ስለዚህም ወደ እርሱ እንሂድ፤ ምናልባትም አህዮቹን የት ማግኘት እንደምንችል እርሱ ሊነግረን ይችል ይሆናል” ሲል መለሰለት። ሳኦልም “መሄዱንስ እንሂድ፤ ነገር ግን ለዚያ ለእግዚአብሔር ሰው ምን ዐይነት ስጦታ ልናበረክትለት እንችላለን፤ ስንቃችንም እንኳ ከስልቻችን አልቆአል፤ ታዲያ ሌላ የምንሰጠው ነገር አለ እንዴ?” አለው። አገልጋዩም “እነሆ እኔ የአንድ ጥሬ ብር አንድ አራተኛው እጅ አለችኝ፤ እርስዋን እሰጠዋለሁ፤ እርሱም አህዮቹን የት ማግኘት እንደምንችል ይነግረናል” ሲል መለሰ። በቀድሞ ዘመን በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲፈልግ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ ይል ነበር፤ አሁን ነቢይ የሚባለው በዚያን ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበር። ሳኦልም አገልጋዩን “መልካም ነው እንሂድ!” አለው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው ወደ አለበት ከተማ ሄዱ። በዳገቱ አድርገው ወደ ከተማው ሲወጡ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው “ባለ ራእይ እዚህ አለን?” ብለው ጠየቁአቸው። ልጃገረዶቹም “አዎን! እነሆ፥ ሕዝቡ ዛሬ በኮረብታው ላይ መሥዋዕትን ስለሚያቀርብ ባለራእዩ ወደ ከተማይቱ መጥቶአልና ፈጥናችሁ ድረሱበት፤ ወደ ከተማው እንደ ገባችሁ ለመብላት ወደ ኮረብታው ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ፤ መሥዋዕቱን መባረክ ስላለበት ሕዝቡ እርሱ ከመምጣቱ በፊት አይበሉም፤ ከዚያም በኋላ ተጋባዦቹ ይበላሉ፤ ፈጥናችሁ ውጡ፤ አሁን ታገኙታላችሁ” አሉአቸው። ከዚያም በኋላ ሳኦልና አገልጋዩ ወደ ከተማይቱ ወጡ፤ ወደ ከተማይቱም በመግባት ላይ ሳሉ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ስፍራ ለማለፍ ወደ እነርሱ አቅጣጫ ሲመጣ አዩት። ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ለሳሙኤል እንዲህ ብሎ ገልጦለት ነበር፤ “ነገ በዚህ ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እልክልሃለሁ፤ ጩኸታቸው ወደ እኔ ስለ ደረሰ ወደ ሕዝቤ ተመልክቼአለሁና ከፍልስጥኤማውያን ጭቈና ሕዝቤን ስለሚያድን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ አድርገህ ቀባው።” ሳሙኤልም ሳኦልን ባየው ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሳሙኤልን “ያ የነገርኩህ ሰው እነሆ ይህ ነው፤ እርሱ ለሕዝቤ መሪ ይሆናል” አለው። ሳኦልም በቅጽሩ በር አጠገብ ወደነበረው ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ “የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ” አለው። ሳሙኤልም ሳኦልን፦ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ ከእኔ በፊት ወደ ማምለኪያው ቀድመህ ውጣ፤ ነገ ጧት በልብህ ያለውን ሁሉ ነግሬህ አሰናብትሃለሁ፤ ከሦስት ቀን በፊት የጠፉት አህዮችህ ተገኝተዋልና ስለ እነርሱ አትጨነቅ፤ ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ምኞት ማንን ለማግኘት ይመስልሃል? እነርሱ የሚፈልጉት አንተንና የአባትህን ቤተሰብ አይደለምን?” አለው። ሳኦልም “እኔ ከእስራኤል ነገዶች መካከል በተለይ ታናሽ የሆነው የብንያም ነገድ ተወላጅ ነኝ፤ በዚሁም ነገድ ውስጥ እንኳ የእኔ ቤተሰብ በጣም አነስተኛ ነው፤ ታዲያ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለእኔ ስለምን ትነግረኛለህ?” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ሳኦልንና አገልጋዩን እየመራ ወደ ታላቁ አዳራሽ አስገብቶ ብዛታቸው ሠላሳ የሚሆኑ እንግዶች በተቀመጡበት ገበታ ከሁሉ በላይ የሆነውን የክብር ቦታ ሰጣቸው። ሳሙኤልም የወጥ ቤቱን ሠራተኛ ጠርቶ “ለብቻው አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን ብልት ሥጋ አምጣ” አለው፤ ስለዚህም የወጥቤቱ ሠራተኛ ምርጥ የሆነውን የታናሽ ብልት ሥጋ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን “ተመልከት፤ ይህ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ምርጥ ሥጋ ነው፤ እኔ ከጋበዝኳቸው እንግዶች ጋር ሆነህ እንድትበላ ያስቀመጡልህ ስለ ሆነ እርሱን ተመገብ” አለው። ስለዚህም በዚያ ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር አብሮ ተመገበ፤ ከማምለኪያውም ስፍራ ወርደው ወደ ከተማይቱ በገቡ ጊዜ በሳሙኤል ቤት ሰገነት ላይ ለሳኦል አልጋ ተዘጋጀለት፤ እርሱም እዚያ ተኝቶ ዐደረ። በነጋም ጊዜ ማለዳ ሳሙኤል ከሰገነቱ ላይ ሳኦልን ጠርቶ “እንግዲህ ተነሥ፤ ላሰናብትህና መንገድህን ቀጥል” አለው፤ ሳኦልም ከመኝታው ተነሣ፤ እርሱና ሳሙኤልም አብረው ወደ መንገዱ ሄዱ፤ ወደ ከተማይቱም ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን “አገልጋይህ ቀድሞን ወደ ፊት እንዲሄድ ንገረው” አለው፤ አገልጋዩም ቀድሞ ከሄደ በኋላ ሳሙኤል ሳኦልን እንደገና “አንተ እዚህ ትንሽ ቈይ፤ እኔም እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos