የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 25:4-35

1 ሳሙኤል 25:4-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዳዊ​ትም በም​ድረ በዳ ሳለ፥ “ናባል በቀ​ር​ሜ​ሎስ በጎ​ቹን ይሸ​ል​ታል” የሚል ወሬ ሰማ። ዳዊ​ትም ዐሥር ብላ​ቴ​ኖ​ችን ላከ፤ ለብ​ላ​ቴ​ኖ​ቹም አለ፥ “ወደ ቀር​ሜ​ሎስ ወጥ​ታ​ችሁ ወደ ናባል ሂዱ፤ በስ​ሜም ሰላም በሉት፤ እን​ዲ​ህም በሉት፥ “ደኅ​ን​ነ​ትና ሰላም ለአ​ን​ተና ለቤ​ትህ፥ ለአ​ን​ተም ለሆ​ኑት ሁሉ ይሁን። አሁ​ንም በጎ​ችህ እን​ደ​ሚ​ሸ​ለቱ ከእኛ ጋር በም​ድረ በዳ ያሉ ሰዎች ነገ​ሩን፤ እኛም አል​ከ​ለ​ከ​ል​ና​ቸ​ውም፤ በቀ​ር​ሜ​ሎ​ስም በነ​በ​ሩ​በት ዘመን ሁሉ ከመ​ን​ጋ​ቸው ይሰ​ጡን ዘንድ አላ​ዘ​ዝ​ና​ቸ​ውም። ብላ​ቴ​ኖ​ች​ህን ጠይ​ቃ​ቸው፤ እነ​ር​ሱም ይነ​ግ​ሩ​ሃል፤ አሁ​ንም እን​ግ​ዲህ በመ​ል​ካም ቀን መጥ​ተ​ና​ልና ብላ​ቴ​ኖች በፊ​ትህ ሞገስ ያግኙ፤ በእ​ጅ​ህም ከተ​ገ​ኘው ለል​ጅህ ለዳ​ዊት እባ​ክህ፥ ላክ።” የዳ​ዊ​ትም ብላ​ቴ​ኖች መጡ፤ ይህ​ንም የላ​ካ​ቸ​ውን ቃል ሁሉ በዳ​ዊት ስም ለና​ባል ነገ​ሩት፤ ናባ​ልም ተነ​ሥቶ ለዳ​ዊት ብላ​ቴ​ኖች መለ​ሰ​ላ​ቸው እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ዳዊት ማን ነው? የእ​ሴ​ይስ ልጅ ማን ነው? እያ​ን​ዳ​ን​ዳ​ቸው ከጌ​ቶ​ቻ​ቸው የኰ​በ​ለሉ አገ​ል​ጋ​ዮች ዛሬ ብዙ ናቸው። እን​ጀ​ራ​ዬ​ንና የወ​ይን ጠጄን፥ ለሸ​ላ​ቾ​ቼም ያረ​ድ​ሁ​ትን ሥጋ ወስጄ ከወ​ዴት እንደ ሆኑ ለማ​ላ​ው​ቃ​ቸው ሰዎች እሰ​ጣ​ለ​ሁን?” የዳ​ዊ​ትም ብላ​ቴ​ኖች ዞረው በመ​ጡ​በት መን​ገድ ተመ​ለሱ፤ መጥ​ተ​ውም ይህን ነገር ሁሉ ለዳ​ዊት ነገ​ሩት። ዳዊ​ትም ሰዎ​ቹን፥ “ሁላ​ችሁ ሰይ​ፋ​ች​ሁን ታጠቁ” አላ​ቸው። ሁሉም ሰይ​ፋ​ቸ​ውን ታጠቁ፤ ዳዊ​ትም ሰይ​ፉን ታጠቀ፤ አራት መቶ ሰዎ​ችም ዳዊ​ትን ተከ​ት​ለው ወጡ፤ ሁለት መቶ​ውም በጓ​ዛ​ቸው ዘንድ ተቀ​መጡ። ከብ​ላ​ቴ​ኖ​ቹም አንዱ ለና​ባል ሚስት ለአ​ቤ​ግያ እን​ዲህ ብሎ ነገ​ራት፥ “እነሆ፥ ዳዊት በም​ድረ በዳ ሳለ ጌታ​ች​ንን ሰላም ሊሉት መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ እርሱ ግን ፊቱን አዞ​ረ​ባ​ቸው። እነ​ዚህ ሰዎች ግን በእኛ ዘንድ እጅግ ደጎች ነበሩ፤ የከ​ለ​ከ​ሉ​ንም የለም፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር በኖ​ር​ን​በት ዘመን ሁሉ በም​ድረ በዳ ሳለን ከመ​ን​ጋው እን​ሰ​ጣ​ቸው ዘንድ ያዘ​ዙን አን​ዳች ነገር የለም። ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ሆነን መን​ጋ​ውን በጠ​በ​ቅ​ን​በት ዘመን ሁሉ በም​ድረ በዳ ሌሊ​ትና ቀን አጥር ሆነ​ውን ነበር። ስለ​ዚ​ህም በጌ​ታ​ች​ንና በቤቱ ሁላ ክፉ ነገር እን​ዲ​መጣ ተቈ​ር​ጦ​አ​ልና፥ እርሱ ክፉ ሰው ስለ ሆነ ማንም ሊና​ገ​ረው አይ​ች​ል​ምና የም​ታ​ደ​ር​ጊ​ውን ተመ​ል​ከ​ቺና ዕወቂ።” አቤ​ግ​ያም ፈጥና፦ ሁለት መቶ እን​ጀራ፥ ሁለት አቁ​ማዳ የወ​ይን ጠጅ፥ አም​ስት የተ​ዘ​ጋጁ በጎች፥ አም​ስ​ትም መስ​ፈ​ሪያ በሶ፥ አንድ ጎሞር ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበ​ለስ ጥፍ​ጥፍ ወሰ​ደች፥ በአ​ህ​ዮ​ችም ላይ አስ​ጫ​ነች። ለአ​ገ​ል​ጋ​ዮ​ች​ዋም፥ “አስ​ቀ​ድ​ማ​ችሁ በፊቴ ሂዱ፤ እነ​ሆም እከ​ተ​ላ​ች​ኋ​ለሁ” አለች። ይህ​ንም ለባ​ልዋ ለና​ባል አል​ነ​ገ​ረ​ች​ውም። እር​ስ​ዋም በአ​ህ​ያዋ ላይ ተቀ​ምጣ በተ​ራ​ራው ላይ በተ​ሰ​ወረ ስፍራ በወ​ረ​ደች ጊዜ፥ እነሆ፥ ዳዊ​ትና ሰዎቹ ወደ እር​ስዋ ወር​ደው ተቀ​በ​ሏት፤ እር​ስ​ዋም ተገ​ና​ኘ​ቻ​ቸው። ዳዊ​ትም አለ፥ “ለዚህ ሰው ከሆ​ነው ሁሉ አንድ ነገር እን​ዳ​ይ​ጠ​ፋ​በት በእ​ው​ነት ከብ​ቱን ሁሉ በም​ድረ በዳ በከ​ንቱ ጠበ​ቅሁ፤ ከገ​ን​ዘቡ ሁሉ አን​ዳች ይወ​ስ​ዱ​በት ዘንድ ያዘ​ዝ​ነው የለም፤ እር​ሱም በበጎ ፋንታ ክፉ መለ​ሰ​ልኝ። ለና​ባ​ልም ከሆ​ነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አጥር ተጠ​ግቶ የሚ​ሸን አንድ ስንኳ ብን​ተው፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዳ​ዊት ላይ እን​ዲህ ያድ​ርግ፤ እን​ዲ​ህም ይጨ​ምር” ብሎ ነበር። አቤ​ግ​ያም ዳዊ​ትን ባየች ጊዜ ከአ​ህ​ያዋ ላይ ፈጥና ወረ​ደች፤ በዳ​ዊ​ትም ፊት በግ​ን​ባ​ርዋ ወደ​ቀች፤ ምድ​ርም ነክታ ሰገ​ደ​ች​ለት። በእ​ግ​ሩም ላይ ወደ​ቀች፤ እን​ዲ​ህም አለች፥ “ጌታዬ ሆይ! ይህ ኀጢ​ኣት በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪ​ያህ በጆ​ሮህ ልና​ገር፥ የባ​ሪ​ያ​ህ​ንም ቃል አድ​ምጥ። በዚህ ክፉ ሰው በና​ባል ላይ ጌታዬ ልቡን እን​ዳ​ይ​ጥል እለ​ም​ና​ለሁ፤ እንደ ስሙ እን​ዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፤ ስን​ፍ​ናም አድ​ሮ​በ​ታል፤ እኔ ባሪ​ያህ ግን አንተ የላ​ክ​ሃ​ቸ​ውን ብላ​ቴ​ኖ​ች​ህን አላ​የ​ሁም። አሁ​ንም ጌታዬ ሆይ! ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! በሕ​ያው ነፍ​ስህ እም​ላ​ለሁ! ወደ ንጹሕ ደም እን​ዳ​ት​ገ​ባና፥ እጅ​ህን እን​ድ​ታ​ድን የከ​ለ​ከ​ለህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነው፤ አሁ​ንም ጠላ​ቶ​ች​ህና በጌ​ታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። አሁ​ንም ባሪ​ያህ ወደ ጌታዬ ያመ​ጣ​ች​ውን ይህን መተ​ያያ ተቀ​በል፤ በጌ​ታ​ዬም ዘንድ ለሚ​ቆሙ ሰዎች ስጣ​ቸው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለጌ​ታዬ የታ​መነ ቤትን ይሠ​ራ​ለ​ታ​ልና፥ የጌ​ታ​ዬ​ንም ጦር​ነት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይዋ​ጋ​ለ​ታ​ልና የእ​ኔን የባ​ሪ​ያ​ህን ኀጢ​ኣት፥ እባ​ክህ፥ ይቅር በል፤ በዘ​መ​ን​ህም ሁሉ ክፋት አይ​ገ​ኝ​ብ​ህም። የሚ​ያ​ሳ​ድ​ድ​ህና ነፍ​ስ​ህን የሚሻ ሰው ቢነሣ፥ የጌ​ታዬ ነፍስ በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ በሕ​ይ​ወት ማሰ​ሪያ የታ​ሰ​ረች ትሆ​ና​ለች፤ የጠ​ላ​ቶ​ችህ ነፍስ ግን በወ​ን​ጭፍ እን​ደ​ሚ​ወ​ነ​ጨፍ ትሁን። እን​ዲ​ህም ይሆ​ናል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለጌ​ታዬ የተ​ና​ገ​ረ​ውን ቸር​ነት ሁሉ ያደ​ር​ግ​ል​ሃል፤ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ላይ አለቃ አድ​ርጎ ይሾ​ም​ሃል፤ ይህ ርኵ​ሰ​ትና የልብ በደል፥ በከ​ንቱ ንጹሕ ደም ማፍ​ሰ​ስም ለጌ​ታዬ አይ​ሁ​ኑ​በት፤ የጌ​ታ​ዬም እጁ ትዳን፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ለጌ​ታዬ በጎ ያድ​ር​ግ​ለት፤ በጎም ታደ​ር​ግ​ላት ዘንድ ባሪ​ያ​ህን አስብ።” ዳዊ​ትም አቤ​ግ​ያን አላት፥ “ዛሬ እኔን ለመ​ገ​ና​ኘት አን​ቺን የላከ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ስ​ገን። ጠባ​ይሽ የተ​ባ​ረከ ነው። ወደ ደም እን​ዳ​ል​ገባ፥ እጄ​ንም እን​ዳ​ድን ዛሬ የከ​ለ​ከ​ል​ሽኝ አን​ቺም የተ​ባ​ረ​ክሽ ነሽ። ነገር ግን ክፉ እን​ዳ​ላ​ደ​ር​ግ​ብሽ የከ​ለ​ከ​ለኝ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! እኔን ለመ​ገ​ና​ኘት ፈጥ​ነሽ ባል​መ​ጣሽ ኖሮ፥ እስ​ኪ​ነጋ ድረስ ለና​ባል አጥር ተጠ​ግቶ የሚ​ሸን አንድ ስንኳ ባል​ቀ​ረ​ውም ብዬ ነበር።” ዳዊ​ትም ያመ​ጣ​ች​ውን ከእ​ጅዋ ተቀ​ብሎ፥ “በሰ​ላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፥ ቃል​ሽን እንደ ሰማሁ፥ ፊት​ሽ​ንም እን​ዳ​ከ​በ​ርሁ ተመ​ል​ከቺ” አላት።

1 ሳሙኤል 25:4-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እንደሚሸልት ሰማ። እርሱም ዐሥር ወጣቶችን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ቀርሜሎስ ወደ ናባል ውጡ፤ በስሜም ሰላምታ አቅርቡለት። እንዲህም በሉት፤ ‘ዕድሜህ ይርዘም! ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ሰላም ለቤተ ሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን። “ ‘በዚህ ጊዜ በጎች እንደምትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ፣ ያደረስንባቸው ጕዳት የለም፤ ቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፣ የጠፋባቸው አንዳች ነገር አልነበረም። የገዛ አገልጋዮችህን ጠይቅ፤ እነርሱም ይነግሩሃል። ስለዚህ አመጣጣችን በጥሩ ቀን በመሆኑ፣ እነዚህ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። እባክህን ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የምትችለውን ያህል ስጥ።’ ” የዳዊት ሰዎች ከዚያ እንደ ደረሱም፣ በዳዊት ስም ይህንኑ መልእክት ለናባል ከተናገሩ በኋላ ምላሹን ይጠባበቁ ጀመር። ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለመሆኑ ይህ ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ ከጌቶቻቸው የሚኰበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። ታዲያ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደ መጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠውስ ለምንድን ነው?” የዳዊት ሰዎችም ወደ መጡበት ተመለሱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። ዳዊትም ሰዎቹን፣ “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም የራሱን ታጠቀ። አራት መቶ ያህል ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ መቶ ያህሉ ግን ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ። ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ዳዊት ሰላምታውን እንዲያቀርቡለት ከምድረ በዳ ወደ ጌታችን መልእክተኞች ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን የስድብ ናዳ አወረደባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን እጅግ መልካም ነበሩ፤ ጕዳትም አላደረሱብንም፤ በዱር አብረናቸው በነበርንበት ጊዜም ሁሉ፣ ምንም ነገር አልጠፋብንም። በጎቻችንን እየጠበቅን አብረናቸው ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ፣ ቀንም ሆነ ሌሊት በዙሪያችን ዐጥር ሆነውን ነበር። አሁንም በጌታችንና በመላው ቤተ ሰቡ ላይ መከራ እያንዣበበ ስለሆነ፣ አስቢበትና የምታደርጊውን አድርጊ፤ እርሱ እንደ ሆነ እንዲህ ያለ ባለጌ ሰው ስለሆነ፣ ደፍሮ የሚነግረው አንድም ሰው የለም።” አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፣ ሁለት አቍማዳ የወይን ጠጅ፣ አምስት የተሰናዱ በጎች፣ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰጠ እሸት፣ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፣ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች። ከዚያም አገልጋዮቿን፣ “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም። እርሷም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ወደ ሸለቆው በምትወርድበት ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፤ እርሷም አገኘቻቸው። ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ምንም ነገር እንዳይጠፋበት የዚህን ሰው ሀብት በምድረ በዳ ያን ያህል መጠበቄ ለካ በከንቱ ኖሯል፤ ደግ በሠራሁ ይኸው ክፉ መለሰልኝ። ነገ ጧት የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ባስቀር እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያድርግበት፣ ከዚህም የከፋ ይጨምርበት!” አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፣ በዳዊትም ፊት በግምባሯ ተደፍታ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ። ጌታዬ፣ ያን ባለጌ ሰው ናባልን ከቁም ነገር አይቍጠረው፤ ስሙ ራሱ ጅል ማለት ስለሆነ፣ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ጅልነትም አብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጕልማሶች አላየኋቸውም። ጌታዬ ሆይ፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤ አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። ጌታዬ የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለሚዋጋ እግዚአብሔርም ለጌታዬ ሥርወ መንግሥቱን በርግጥ ለዘላለም የሚያጸናለት በመሆኑ፣ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ። ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፣ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፣ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል። እግዚአብሔር ለጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት በጎውን ነገር ሁሉ ባደረገለትና በእስራኤልም ላይ ባነገሠው ጊዜ፣ ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርህም፤ በከንቱ ያፈሰስኸውም ደም ሆነ በገዛ እጅህ የተበቀልኸው የለምና። እግዚአብሔር በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜ እኔን አገልጋይህን ዐስበኝ።” ዳዊትም አቢግያን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። ጕዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፣ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።” ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፣ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት።

1 ሳሙኤል 25:4-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዳዊትም በምድረ በዳ ሳለ፦ ናባል በጎቹን ይሸልታል የሚል ወሬ ሰማ። ዳዊትም አሥር ጕልማሶች ላከ ለጕልማሶችም አለ፦ ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ወደ ናባል ሂዱ፥ በስሜም ስለ ሰላም ጠይቁት፥ እንዲህም በሉት፦ በደኅንነት ኑር፥ ለአንተና ለቤትህም ለአንተም ላሉት ሁሉ ሰላም ይሁን። አሁንም በጎችህን እንድትሸልት ሰምቻለሁ፥ እረኞችህም ከእኛ ጋር ነበሩ፥ ከቶ አልበደልናቸውም፥ በቀርሜሎስም በተቀመጡበት ዘመን ሁሉ ከመንጋው አንዳች አልጎደለባቸውም። ጕልማሶችህን ጠይቃቸው፥ እነርሱም ይነግሩሃል፥ አሁንም እንግዲህ በመልካም ቀን መጥተንብሃልና ጕልማሶች በፊትህ ሞገስ ያግኙ፥ በእጅህም ከተገኘው ለባሪያዎችህና ለልጅህ ለዳዊት፥ እባክህ፥ ስጥ። የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነግረው ዝም አሉ። ናባልም ለዳዊት ባሪያዎች፦ ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኮበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው። እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው። የዳዊትም ጕልማሶች ዞረው በመጡበት መንገድ ተመለሱ፥ መጥተውም ይህን ነገር ሁሉ ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ሰዎቹን፦ ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ አላቸው። ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፥ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፥ አራት መቶ ሰዎችም ዳዊትን ተከትለው ወጡ፥ ሁለት መቶውም በዕቃው ዘንድ ተቀመጡ። ከብላቴኖቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ ብሎ ነገራት፦ እነሆ፥ ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ጌታችንን ሊባርኩ መልእክተኞች ላከ፥ እርሱ ግን ሰደባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን በእኛ ዘንድ እጅግ መልካም ነበሩ፥ አልበደሉንምም፥ ከእነርሱም በሄድንበት ዘመን ሁሉ በምድረ በዳ ሳለን አንዳች አልጠፋብንም፥ ከእነርሱ ጋር ሆነን መንጋውን በጠበቅንበት ዘመን ሁሉ ሌሊትና ቀን አጥር ሆነውን ነበር። ስለዚህም በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ክፉ ነገር እንዲመጣ ተቆርጦአልና፥ እርሱ ምናምንቴ ሰው ስለ ሆነ ማንም ሊናገረው አይችልምና የምታደርጊውን ተመልከቺና እወቂ። አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስትም የተዘጋጁ በጎች፥ አምስትም መስፈሪያ ጥብስ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበለስ ጥፍጥፍ ወሰደች፥ በአህዮችም ላይ አስጫነች። ለብላቴኖችዋም፦ አስቀድማችሁ በፊቴ ሂዱ፥ እነሆም፥ እከተላችኋለሁ አለች። ይህንም ለባልዋ ለናባል አልነገረችውም። እርስዋም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ በተራራው ላይ በተሰወረ ስፍራ በወረደች ጊዜ፥ እነሆ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርስዋ ወረዱ፥ እርስዋም ተገናኘቻቸው። ዳዊትም፦ ለዚህ ሰው ከሆነው ሁሉ አንድ ነገር እንዳይጠፋበት በእውነት ከብቱን ሁሉ በምድረ በዳ በከንቱ ጠበቅሁ፥ እርሱም ስለ በጎነቴ ክፋት መለሰልኝ። ለእርሱም ከሆነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አንድ ወንድ ስንኳ ብተው እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያድርግ እንዲህም ይጨምር ብሎ ነበር። አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች፦ ጌታዬ ሆይ፥ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፥ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ። በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፥ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፥ ስሙ ናባል ነው፥ ስንፍናም አድሮበታል፥ እኔ ባሪያህ ግን ከአንተ የተላኩትን የጌታዬን ጕልማሶች አላየሁም። አሁንም፥ ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፥ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፥ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም። ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፥ የጠላቶችህንም ነፋስ ከወንጭፍ እንደሚጣል እንዲሁ ይጥላታል። እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥ አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተሳካልህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፥ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ። ዳዊትም አቢግያን አላት፦ ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ። ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ፥ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ ባልቀረውም ነበር። ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ፦ በደኅና ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እነሆ፥ ቃልሽን ሰማሁ፥ ፊትሽንም አከበርሁ አላት።

1 ሳሙኤል 25:4-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዳዊትም በበረሓ ሳለ ይህንኑ ወሬ ሰማ፤ ስለዚህም ዐሥር መልእክተኞችን መርጦ ወደ ቀርሜሎስ እንዲሄዱና ናባልን አግኝተው የእርሱን ሰላምታ እንዲያቀርቡለት አዘዛቸው፤ ለናባልም ይነግሩት ዘንድ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፦ “ሰላም ላንተ፥ ሰላም ለቤትህ፥ ሰላም ያንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን ብላችሁ ሰላምታ አቅርቡለት። በጎችህንም እንደምታሸልት ሰምቶአል፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜም ሁሉ ምንም ዐይነት ጒዳት እንዳላደረስንባቸው እንድታውቅ ይፈልጋል፤ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ከመንጋቸው አንድ እንኳ አልተወሰደባቸውም፤ እነርሱንም ብትጠይቃቸው ይህንኑ ይነግሩሃል፤ እነሆ ዛሬ እኛ የደስታ ግብዣ በሚደረግበት ቀን መጥተናል፤ እኛንም በመልካም ሁኔታ ትቀበለን ዘንድ ዳዊት ጠይቆአል፤ ስለዚህ ለእኛ ለአገልጋዮችህና ለወዳጅህ ለዳዊት ስትል የሚቻልህን ስጦታ አድርግልን።” የዳዊት ሰዎችም ይህንኑ መልእክት በዳዊት ስም ለናባል አስረክበው ይጠባበቁ ጀመር፤ ናባልም በመጨረሻ “ኧረ ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው? እኔ ስለ እርሱ ሰምቼም አላውቅም! እነሆ፥ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከጌቶቻቸው በኰበለሉ አገልጋዮች ተሞልታለች! ስለዚህ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም ለበጎች ሸላቾቼ ያረድኳቸውን እንስሶች አንሥቼ ከወዴት እንደ መጡ ለማላውቃቸው ሰዎች የምሰጥበት ምክንያት የለም!” አለ። መልእክተኞቹም ተመልሰው መጥተው ናባል ያለውን ሁሉ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም “በሉ ሰይፋችሁን ታጠቁ!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ ዳዊትም ራሱ ሰይፉን ታጠቀ፤ ጓዝ የሚጠብቁ ሁለት መቶ ሰዎች ወደ ኋላ ትቶ አራት መቶ ሰዎች በማስከተል ገሥግሦ ለመሄድ ተነሣ። ከናባል አገልጋዮች አንዱም የናባልን ሚስት አቢጌልን እንዲህ አላት፤ “ዳዊት ካለበት በረሓ መልእክተኞችን ከሰላምታ ጋር ወደ ጌታችን ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን በስድብ አዋረዳቸው፤ እነርሱ ግን ለእኛ በጎ አድራጊዎች ነበሩ፤ ምንም ችግር አልፈጠሩብንም፤ ከእነርሱ ጋር በዱር በነበርንበት ጊዜ ሁሉ ከእንስሶቻችን አንድ እንኳ ተሰርቆብን አያውቅም፤ መንጋዎቻችንን እየጠበቅን በቈየንበት ጊዜ ሁሉ በቀንም ሆነ በሌሊት እነርሱ ለእኛ አጥር ሆነውን ነበር። እባክሽን ይህን ጉዳይ አስቢበትና ማድረግ ስለሚገባሽ ነገር ወስኚ፤ አለበለዚያ ለጌታችንና ለቤተሰቡ ሁሉ አደገኛ ጥፋት ይሆናል፤ እርሱ እንደ ሆነ የማንንም ምክር የማይሰማ ደረቅ ሰው ነው!” አቢጌልም በፍጥነት ሁለት መቶ እንጀራ፥ ወይን ጠጅ የተሞላበት ሁለት የወይን አቁማዳ፥ አምስት የተጠበሱ በጎች፥ ዐሥራ ሰባት ኪሎ የተጠበሰ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ወይንና ሁለት መቶ የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ በአንድነት ሰብስባ በአህዮች ላይ ጫነች። ከዚህም በኋላ አገልጋዮቹን “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋላሁ” አለቻቸው፤ ለባልዋ ግን የነገረችው ቃል አልነበረም። እርስዋም በአህያ ላይ ተቀምጣ እየጋለበች በኮረብታው ጥግ በሚገኘው ጠመዝማዛ መንገድ ስትወርድ በድንገት ዳዊትና ተከታዮቹ ወደ እርስዋ ሲመጡ አገኘቻቸው፤ ዳዊትም በልቡ እንዲህ እያለ ያስብ ነበር፤ “የዚያን የማይረባ ሰው ሀብት በዚህ በረሓ ለምን ስጠብቅ ቈየሁ? የእርሱ ከሆነው ንብረት ምንም ነገር ተሰርቆበት አያውቅም፤ ታዲያ እኔ ስላደረግሁለት መልካም ነገር እርሱ የሚከፍለኝ ወሮታ ይህ ሆኖ ቀረ! ከመንጋቱ በፊት የእርሱ የሆኑትን ወንዶች ሁሉ አንድ እንኳ ሳላስቀር በሙሉ ሳልገድል ብቀር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!” አቢጌልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ በፍጥነት ከአህያዋ ወርዳ በዳዊት ጫማ አጠገብ መሬት ላይ ለጥ ብላ እጅ ነሣች፤ በጫማውም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ! እባክህ የእኔን የአገልጋይህን ቃል አድምጠኝ! በደሉን እኔ ልሸከም፤ የናባልን ጉዳይ ከቁም ነገር አታግባው! እርሱ ልክ እንድ አስሙ አጠራር ሞኝ ነው! ጌታዬ፥ የአንተ አገልጋዮች በመጡ ጊዜ እኔ በዚያ አልነበርኩም፤ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ጠላቶችህን እንዳትገድል የጠበቀህ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ እነሆ፥ እኔ አሁን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ጠላቶችህና አንተን ለመጒዳት የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ቅጣታቸውን ይቀበሉ፤ ጌታዬ ሆይ! እባክህ ይህ እኔ አገልጋይህ ያመጣሁልህን ስጦታ ተቀብለህ ለአገልጋዮችህ ይሁን። ጌታዬ፥ አንተ የእግዚአብሔርን ጦርነት እየተዋጋህ ነው፤ በምትኖርበትም ዘመን ሁሉ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር ማድረግን ስለማትፈልግ ስለ ፈጸምኩት በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ እግዚአብሔር አንተንና ዘሮችህን ለዘለዓለም ያነግሣል፤ ማንም ሰው በአንተ ላይ አደጋ ጥሎ ሊገድልህ ቢፈልግ አንድ ሰው ውድ የሆነ ሀብቱን እንደሚጠብቅ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን በሰላም ይጠብቅሃል፤ ስለ ጠላቶችህም የሆነ እንደ ሆነ አንድ ሰው ድንጋዩን ከወንጭፍ እንደሚያስፈነጥር እግዚአብሔር ራሱ አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል። እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥ ምንም ዐይነት ጸጸት ወይም የኅሊና ወቀሳ አይደርስብህም። ጌታዬ ሆይ፥ ያለ ምክንያት ወይም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ብለህ የገደልከው ሰው የለም፤ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር በሚባርክህ ጊዜ እኔንም አትርሳኝ።” ዳዊትም እንዲህ አላት፤ “ከእኔ ጋር እንድትገናኚ አንቺን ወደ እኔ የላከ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! በዛሬው ቀን ደም ከማፍሰስና በቀልንም ከመበቀል የጠበቀኝ መልካም አስተሳሰብሽ የተባረከ ይሁን፤ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። በአንቺ ላይ ጒዳት ከማድረስ እግዚአብሔር ጠብቆኛል፤ ፈጥነሽ ወደ እኔ ባትመጪ ኖሮ ግን፥ ከናባል ወንዶች አንድ እንኳ ሳላስተርፍ ከንጋት በፊት ሁሉንም ለመግደል በሕያው እግዚአብሔር ስም ምዬ ነበር።” ከዚያም በኋላ ዳዊት ያመጣችለትን ስጦታ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ተመልሰሽ ሂጂ፤ ልመናሽን ሰምቼአለሁ፤ የጠየቅሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አላት።

1 ሳሙኤል 25:4-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እንደሚሸልት ሰማ። እርሱም ዐሥር ወጣቶችን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ቀርሜሎስ ወደ ናባል ውጡ፤ በስሜም ሰላምታ አቅርቡለት። እንዲህም በሉት፤ ‘ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ሰላም ለቤተሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን። በዚህ ጊዜ በጎች እንደምትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ፥ ያደረስንባቸው ጉዳት የለም፤ ቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፥ የጠፋባቸው አንዳች ነገር አልነበረም። የገዛ አገልጋዮችህን ጠይቅ፤ እነርሱም ይነግሩሃል። ስለዚህ እነዚህ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። አመጣጣችን በግብዣ ቀን በመሆኑ እባክህን ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የምትችለውን ያህል ስጥ።’ ” የዳዊት ሰዎች ከዚያ እንደ ደረሱም፥ በዳዊት ስም ይህንኑ መልእክት ለናባል ከተናገሩ በኋላ ምላሹን ይጠባበቁ ጀመር። ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለመሆኑ ይህ ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ ከጌቶቻቸው የሚኰበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። ታዲያ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደመጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠውስ ለምንድን ነው?” የዳዊት ሰዎችም ወደመጡበት ተመለሱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። ዳዊትም ሰዎቹን፥ “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም የራሱን ታጠቀ። አራት መቶ ያህል ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ መቶ ያህሉ ግን ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ። ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢጌል እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ዳዊት ሰላምታውን እንዲያቀርቡለት ከምድረበዳ ወደ ጌታችን መልእክተኞች ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን በስድብ አዋረዳቸው። እነዚህ ሰዎች ግን እጅግ መልካም ነበሩ፤ ጉዳትም አላደረሱብንም፤ በዱር አብረናቸው በነበርንበት ጊዜም ሁሉ፥ ምንም ነገር አልጠፋብንም። በጎቻችንን እየጠበቅን አብረናቸው ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ፥ ቀንም ሆነ ሌሊት በዙሪያችን አጥር ሆነውን ነበር። አሁንም በጌታችንና በመላው ቤተሰቡ ላይ መከራ እያንዣበበ ስለሆነ፥ ምን እንደምታደርጊ አስቢበት፤ እርሱ እንደሆነ እንዲህ ያለ ባለጌ ሰው ስለሆነ፥ ማንም ደፍሮ የሚነግረው የለም።” አቢጌልም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስት የተሰናዱ በጎች፥ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰ እሸት፥ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፥ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች። ከዚያም አገልጋዮቹን፥ “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም። እርሷም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ወደ ሸለቆው በምትወርድበት ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፤ እርሷም አገኘቻቸው። ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ምንም ነገር እንዳይጠፋበት የዚህን ሰው ሀብት በምድረ በዳ ያን ያህል መጠበቄ ለካ በከንቱ ኖሯል፤ ደግ በሠራሁ ይኸው ክፉ መለሰልኝ። ነገ ጠዋት የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ባስቀር እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያድርግበት፥ ከዚህም የከፋ ይጨምርበት!” አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ተደፍታ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ። ጌታዬ፥ ያን ባለጌ ሰው ናባልን ከቁምነገር አይቁጠረው፤ ስሙ ራሱ ሞኝ ማለት ስለሆነ፥ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ሞኝነትም አብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጐልማሶች አላየኋቸውም። ጌታዬ ሆይ፤ በሕያው ጌታ፥ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ ጌታ ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤ አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጐልማሶች ይሰጥ። ጌታዬ የጌታን ጦርነት ስለሚዋጋ ጌታም ለጌታዬ የታመነ ቤት በእርግጥ ለዘለዓለም የሚያጸናለት በመሆኑ፥ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ። ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፥ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በጌታ ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፥ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል። ጌታም በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥ ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርብህም፤ ምክንያቱም በከንቱ ያፈሰስከው ደም ወይም በገዛ እጅህ የወሰድከው በቀል የለምና። ስለዚህ ጌታ ለጌታዬ በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜም፥ እኔንም አገልጋይህን አስበኝ።” ዳዊትም አቢጌልን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ የተመሰገነ ይሁን! ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። ጉዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው ጌታን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፥ እስኪ ነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።” ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፥ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት።