1 ሳሙኤል 21:1-6
1 ሳሙኤል 21:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊትም ወደ ካህኑ ወደ አቤሜሌክ ወደ ኖብ መጣ፤ አቤሜሌክም እርሱን በተገናኘው ጊዜ ደነገጠ፥ “ስለምን አንተ ብቻህን ነህ? ከአንተስ ጋር ስለምን ማንም የለም?” አለው። ዳዊትም ካህኑን አቤሜሌክን፥ “የተላክህበትን ነገርና የሰጠሁህን ትእዛዝ ማንም አይወቅ ብሎ ንጉሡ አንድ ነገር አዝዞኛል፤ ስለዚህም ‘ብላቴኖቼን በእግዚአብሔር መታመን’ በሚባለው እንዲህ ባለው ስፍራ እንዲሆኑ አዝዣቸዋለሁ። አሁንም አምስት እንጀራ በእጅህ ካለ፥ ወይም በእጅህ ያለውን ስጠኝ” አለው። ካህኑም ለዳዊት መልሶ፥ “ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን የተቀደሰ እንጀራ አለ፤ ብላቴኖቹ ከሴቶች ንጹሓን እንደ ሆኑ መብላት ይችላሉ” አለው። ዳዊትም ለካህኑ መልሶ፥ “ከሴቶች ተለይተን ወደ መንገድ ከወጣን ዛሬ ሦስተኛ ቀናችን ነው። እኔም ብላቴኖቼም ንጹሓን ነን። ነገር ግን ዛሬ ሰውነቴ ንጽሕት ስለ ሆነች ነው እንጂ ይህች መንገድ የነጻች አይደለችም” አለው። ካህኑ አቤሜሌክም በእርሱ ፋንታ ትኩስ እንጀራ ይደረግ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ከአለው ኅብስት በቀር ሌላ እንጀራ አልነበረምና የቍርባኑን ኅብስት ሰጠው።
1 ሳሙኤል 21:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳዊትም ካህኑ አቢሜሌክ ወዳለበት ወደ ኖብ ሄደ። አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፣ “ምነው ብቻህን? ሰውስ ለምን ዐብሮህ የለም?” ሲል ጠየቀው። ዳዊት፣ ካህኑን አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ፣ ‘ስለ ላክሁህ ነገርና ስለ ሰጠሁህ መመሪያ ማንም ሰው ምንም ነገር አይወቅ’ ብሎ አዞኛል። ሰዎቼንም የት እንደምንገናኝ ነግሬያቸዋለሁ። ታዲያ አሁን በእጅህ ምን አለ? ዐምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።” ካህኑም ዳዊትን፣ “ሰው ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን ሰዎቹ በቅርቡ ከሴት የተጠበቁ ከሆነ፣ የተቀደሰ እንጀራ በዚህ አለ” አለው። ዳዊትም “እንደተለመደው ሁሉ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ከእኛ ተጠብቀዋል፤ ባልተቀደሰ ተልእኮ ውስጥ እንኳ የሰዎቹ ዕቃዎች የተቀደሱ ናቸው፤ ታዲያ ዛሬማ እንዴት!” ሲል ለካህኑ መለሰ። ስለዚህ ካህኑ የተቀደሰውን እንጀራ ለዳዊት ሰጠው፤ ከእግዚአብሔር ፊት ተነሥቶ በትኵስ እንጀራ ከተተካው ከገጸ ኅብስቱ በቀር በዚያ ሌላ እንጀራ አልነበረምና።
1 ሳሙኤል 21:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊትም ወደ ካህኑ ወደ አቢሜሌክ ወደ ኖብ መጣ፥ አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፦ ስለ ምን አንተ ብቻህን ነህ? ከአንተስ ጋር ስለምን ማንም የለም? አለው። ዳዊትም ካህኑን አቢሜሌክን፦ የተላክህበትን ነገርና የሰጠሁህን ትእዛዝ ማንም አይወቅ ብሎ ንጉሡ አንድ ነገር አዝዞኛል፥ ስለዚህም ብላቴኖቹን እንዲህ ባለ ስፍራ ተውኋቸው። አሁንስ በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን በእጄ ስጠኝ አለው። ካህኑም ለዳዊት መልሶ፦ ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፥ ነገር ግን የተቀደስ እንጀራ አለ፥ ብላቴኖቹ ከሴቶቹ ንጹሐን እንደ ሆኑ መብላት ይቻላል አለው። ዳዊትም ለካህኑ መልሶ፦ በእውነት ከወጣን ጀምረን እኛ ሰውነታችንን ከሴቶች ሦስት ቀን ጠብቀናል፥ የብላቴኖችም ዕቃ የተቀደሰች ናት፥ ስለዚህ ዛሬ እቃቸው የተቀደሰች በመሆንዋ እንጀራው እንደሚበላ እንጀራ ይሆናል አለው። ካህኑም በእርሱ ፋንታ ትኩስ እንጀራ ይደረግ ዘንድ ከእግዚአብሔር ፊት ከተነሣው ከገጹ ኅብስት በቀር ሌላ እንጀራ አልነበረምና የተቀደሰውን እንጀራ ሰጠው።
1 ሳሙኤል 21:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዳዊት በኖብ ወደሚገኘው ወደ ካህኑ አቤሜሌክ ዘንድ ሄደ፤ አቤሜሌክም በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ሊቀበለው ወጥቶ “ማንም ሰው ሳይከተልህ ብቻህን ስለምን ወደዚህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ዳዊትም ለካህኑ ለአቢሜሌክ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ እዚህ የመጣሁት የንጉሥ ሳኦልን ተልእኮ ለመፈጸም ነው፤ እኔ ወደዚህ የተላክሁበትን ጉዳይ ለማንም ሰው እንዳልገልጥ ንጉሡ አዞኛል፤ ተከታዮቼንም በአንድ ቦታ እንድንገናኝ አዝዣቸዋለሁ፤ ታዲያ አሁን ምን ምግብ ትሰጠኛለህ? አምስት እንጀራ ወይም ያለህን ሌላ ነገር ስጠኝ።” ካህኑም “ከተቀደሰው ኅብስት በቀር ሕዝብ የሚመገበው እንጀራ የለኝም፤ ተከታዮችህ በቅርቡ ከሴቶች ጋር ሳይገናኙ ተቈጥበው በንጽሕና የቈዩ ከሆኑ፥ ይህን ኅብስት መብላት ይችላሉ” ሲል መለሰለት። ዳዊትም ለካህኑ መልሶ “ከብላቴኖቼ ጋር ወደ ተልእኮ በምሄድበት ጊዜ ሁሉ ከሴቶች እንርቃለን፤ ተራ ተልእኮ እንኳ በምናደርግበት ጊዜ ብላቴኖቼ ንጽሕናቸውን ይጠብቃሉ። ዛሬማ ምንኛ የበለጠ ቅዱሳን መሆን ይገባቸዋል?” ስለዚህም ካህኑ የተቀደሰውን ኅብስት አንሥቶ ለዳዊት ሰጠው፤ ካህኑ ያለው ምግብ ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የቀረበው ኅብስት ብቻ ነበር፤ ይህም ኅብስት ከተቀደሰው ጠረጴዛ ላይ ተነሥቶ በሌላ አዲስ ኅብስት የተተካ ነበር።
1 ሳሙኤል 21:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳዊትም ካህኑ አቢሜሌክ ወዳለበት ወደ ኖብ ሄደ። አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፥ “ምነው ብቻህን? ሰውስ ለምን አብሮህ የለም?” ሲል ጠየቀው። ዳዊት፥ ካህኑን አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ፥ ‘ስለ ላክሁህ ነገርና ስለ ሰጠሁህ መመሪያ ማንም ሰው ምንም ነገር አይወቅ’ ብሎ አዞኛል። ሰዎቼንም የት እንደምንገናኝ ነግሬያቸዋለሁ። ታዲያ አሁን በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።” ካህኑም፥ “ሰው ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን ሰዎቹ በቅርቡ ከሴት የተጠበቁ ከሆነ፥ የተቀደሰ እንጀራ በዚህ አለ” አለው። ዳዊትም “እንደተለመደው ሁሉ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ከእኛ ተጠብቀዋል፤ በተራ ተልእኮ ውስጥ እንኳ የሰዎቹ ዕቃዎች የተቀደሱ ናቸው፤ ዛሬማ ምንኛ የበለጠ ቅዱሳን መሆን ይገባቸዋል?” ሲል መለሰ። ስለዚህ ካህኑ የተቀደሰውን እንጀራ ለዳዊት ሰጠው፤ ከጌታ ፊት ተነሥቶ በትኩስ እንጀራ ከተተካው ከኅብስት በስተቀር በዚያ ሌላ እንጀራ አልነበረምና።