1 ሳሙኤል 17:32-37
1 ሳሙኤል 17:32-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊትም ሳኦልን፥ “ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም ዳዊትን፥ “አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው፥ “እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፤ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር። ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ ገደልሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። እንግዲህ እገድለው ዘንድ፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቈላፍ ምንድን ነው?” ዳዊትም፥ “ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል” አለ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው።
1 ሳሙኤል 17:32-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳዊትም ሳኦልን፣ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ ባሪያህ ሄዶ ይዋጋዋል” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፣ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለ ሆነ፣ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፣ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፣ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጕረሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባሪያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም፣ “ሂድ፤ እግዚአብሔር ካንተ ጋራ ይሁን” አለው።
1 ሳሙኤል 17:32-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊትም ሳኦልን፦ ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፥ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው፦ እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፥ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፥ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ዳዊትም፦ ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን፦ ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው።
1 ሳሙኤል 17:32-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዳዊትም ሳኦልን “ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ ማንም ሰው መፍራት የለበትም! እኔ ያንተ አሽከር ሄጄ እርሱን እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ “አንተ ገና ልጅ ነህ፤ እርሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ስለ ሆነ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ ያንተ አሽከር የአባቴን በጎች የምጠብቅ እረኛ ነኝ፤ አንበሳም ሆነ ድብ መጥቶ ጠቦት በሚነጥቅበት ጊዜ፥ ተከትዬው ሄጄ አደጋ በመጣል የወሰደውን ጠቦት አስጥለው ነበር፤ አንበሳው ወይም ድቡ ወደ እኔ ተመልሶ በሚመጣበትም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ በመምታት እገድለው ነበር። እኔ ያንተ አሽከር አንበሳና ድብ ገድያለሁ፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለ ተፈታተነ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳና ድብ ያዳነኝ እግዚአብሔር ከዚህም ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም “መልካም ነው! እንግዲህ ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን!” ሲል መለሰለት።
1 ሳሙኤል 17:32-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳዊትም ሳኦልን፥ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ እኔ አገልጋይህ ሄጄ እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና ልጅ ነህ፥ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለሆነ፥ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፥ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፥ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባርያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ ጌታ አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሲል ዳዊት ተናገረ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ ጌታ ካንተ ጋር ይሁን!” አለው።