1 ሳሙኤል 10:25-27
1 ሳሙኤል 10:25-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሳሙኤልም የንጉሡን ሥርዐት ነገራቸው፤ በመጽሐፍም ጻፈው፤ በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው። ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እየቤታቸው አሰናበታቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እየቤታቸው ሄዱ። ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ገባዖን ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካው ኀያላንም ከሳኦል ጋር ሄዱ። ክፉዎች ሰዎች ግን፥ “ያድነን ዘንድ ይህ ሰው ማን ነው?” ብለው ናቁት፤ እጅ መንሻም አላመጡለትም።
1 ሳሙኤል 10:25-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሳሙኤልም ለንጉሥ የሚገባውን ወግና ሥርዐት ለሕዝቡ ገልጦ ካስረዳ በኋላ በመጽሐፍ ጽፎ በእግዚአብሔር ፊት አኖረው። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱን ሰው ወደየቤቱ አሰናበተ። ሳኦልም ጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ፤ እግዚአብሔርም ልባቸውን የነካው ኀያላን ሰዎች አብረውት ሄዱ። አንዳንድ ምናምንቴ ሰዎች ግን፣ “እንዲህ ያለ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” በማለት ናቁት፤ ስጦታም አላመጡለትም። ሳኦል ግን ዝም አለ።
1 ሳሙኤል 10:25-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሳሙኤልም የመንግሥቱን ወግ ነገረ፥ በመጽሐፍም ጻፈው በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው። ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እየቤታቸው አሰናበታቸው። ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ሄደ፥ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካ ኃያላንም ከእርሱ ጋር ሄዱ። ምናምንቴዎች ሰዎች ግን፦ ይህ ሰው እንዴት ያድነናል? ብለው ናቁት፥ እጅ መንሻም አላመጡለትም።
1 ሳሙኤል 10:25-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሳሙኤልም ለሕዝቡ፥ ለአንድ ንጉሥ ሊደረግለት የሚገባውን ሥርዓት አስረዳቸው፤ ያንንም በመጽሐፍ ጽፎ በእግዚአብሔር ፊት አስቀመጠው፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ ወደየቤቱ አሰናበተ፤ ሳኦልም በጊብዓ ወደሚገኘው ቤቱ ተመልሶ ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን ያነሣሣው ኀያላንም ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ ነገር ግን አንዳንድ ሥርዓተ አልባዎች “አሁን ይህ ሰው እኛን ለማዳን ይችላል?” ተባባሉ፤ እርሱንም በመናቅ ምንም ዐይነት ገጸ በረከት ሳያመጡለት ቀሩ። ሳኦል ግን ዝም አለ።
1 ሳሙኤል 10:25-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሳሙኤልም ለንጉሥ የሚገባውን ተግባርና ሥርዓት ለሕዝቡ ገልጦ ካስረዳ በኋላ በመጽሐፍ ጽፎ በጌታ ፊት አኖረው። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱን ሰው ወደየቤቱ አሰናበተ። ሳኦልም ጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ፤ እግዚአብሔርም ልባቸውን የነካው ኀያላን ሰዎች አብረውት ሄዱ። አንዳንድ ሥርዓተ አልባዎች ግን፥ “እንዲህ ያለ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” በማለት ናቁት፤ ስጦታም አላመጡለትም። ሳኦል ግን ዝም አለ።