የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ነገሥት 7:1-39

1 ነገሥት 7:1-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሰሎ​ሞ​ንም የራ​ሱን ቤት በዐ​ሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፤ የቤ​ቱ​ንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ። የሊ​ባ​ኖስ ዱር ቤት የሚ​ባል ቤት​ንም ሠራ፤ ርዝ​መ​ቱ​ንም መቶ ክንድ፥ ስፋ​ቱ​ንም አምሳ ክንድ፥ ቁመ​ቱ​ንም ሠላሳ ክንድ አደ​ረገ፤ የዋ​ን​ዛም እን​ጨት በሦ​ስት ወገን በተ​ሠሩ አዕ​ማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአ​ዕ​ማ​ዱም ላይ የዋ​ንዛ እን​ጨት አግ​ዳሚ ሰረ​ገ​ሎች ነበሩ። በአ​ዕ​ማ​ዱም ላይ በነ​በሩ አግ​ዳ​ሚ​ዎች ቤቱ በዋ​ንዛ ሳንቃ ተሸ​ፍኖ ነበር፤ አዕ​ማ​ዱም በአ​ንዱ ወገን ዐሥራ አም​ስት፥ በአ​ንዱ ወገን ዐሥራ አም​ስት የሆኑ አርባ አም​ስት ነበሩ። መስ​ኮ​ቶ​ቹም በሦ​ስት ወገን ነበሩ፤ መስ​ኮ​ቶ​ቹም በሦ​ስት ወገን ፊት ለፊት ይተ​ያዩ ነበር። ደጆቹ፥ መቃ​ኖ​ቹና የታ​ች​ኛ​ውና የላ​ይ​ኛው መድ​ረ​ኮች ሁሉ አራት ማዕ​ዘን ነበሩ፤ መስ​ኮ​ቶ​ቹም በሦ​ስት ወገን ሆነው ፊት ለፊት ይተ​ያዩ ነበር። አዕ​ማ​ዱም ያሉ​በ​ትን ቤት ሠራ፤ ርዝ​መ​ቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋ​ቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእ​ር​ሱም ፊት ደግሞ ታላቅ አዕ​ማ​ድና መድ​ረክ ያሉ​በት ወለል ነበረ። የሚ​ፈ​ር​ድ​በ​ትም የቤቱ ዙፋን በዚያ አለ። ለመ​ፍ​ረ​ጃ​ውም ቤትን ሠራ፤ ከላይ እስከ ታችም በዋ​ንዛ እን​ጨት አያ​ያ​ዘው። ከፍ​ርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌ​ላ​ውም አደ​ባ​ባይ ውስጥ የነ​በ​ረ​ውን የሚ​ኖ​ር​በ​ትን ቤት እን​ዲሁ ሠራ፤ እን​ደ​ዚ​ህም ቤት ያለ ቤትን ሰሎ​ሞን ላገ​ባት ለፈ​ር​ዖን ልጅ ሠራ። ይህም ሁሉ ከመ​ሠ​ረቱ ጀምሮ እስከ ጕል​ላቱ ድረስ በከ​በ​ረና በተ​ጠ​ረበ በው​ስ​ጥና በውጭ በልክ በተ​ከ​ረ​ከመ ድን​ጋይ ተሠ​ርቶ ነበር፤ በው​ጭ​ውም እስከ ታላቁ አደ​ባ​ባይ ድረስ እን​ዲሁ ነበረ። መሠ​ረ​ቱም ዐሥር ዐሥር ክን​ድና ስም​ንት ስም​ንት ክንድ በሆኑ በከ​በሩ በታ​ላ​ላቅ ድን​ጋ​ዮች ተሠ​ርቶ ነበር። በላ​ዩም ልክ ሆኖ የተ​ከ​ረ​ከመ ጥሩ ድን​ጋ​ይና የዝ​ግባ ሣንቃ ነበረ። በታ​ላ​ቁም አደ​ባ​ባይ ዙሪያ የነ​በ​ረው ቅጥር እንደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት እንደ ውስ​ጠ​ኛው አደ​ባ​ባይ ቅጥ​ርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ወገን በተ​ጠ​ረበ ድን​ጋይ አን​ዱም ወገን በዝ​ግባ ሳንቃ ተሠ​ርቶ ነበር። ንጉ​ሡም ሰሎ​ሞን ልኮ ኪራ​ምን ከጢ​ሮስ አስ​መጣ። እር​ሱም ከን​ፍ​ታ​ሌም ወገን የነ​በ​ረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፤ አባ​ቱም የጢ​ሮስ ሰው ናስ ሠራ​ተኛ ነበረ፤ የና​ስ​ንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥ​በ​ብና በማ​ስ​ተ​ዋል፥ በብ​ል​ሃ​ትም ተሞ​ልቶ ነበር። ወደ ንጉ​ሡም ወደ ሰሎ​ሞን መጥቶ ሥራ​ውን ሁሉ ሠራ። በቤቱ ውስጥ ላለው ወለል ሁለ​ቱን የናስ አዕ​ማድ ሠራ፤ የአ​ን​ዱም ዓምድ ቁመት ዐሥራ ስም​ንት ክንድ ነበረ፤ የዙ​ሪ​ያ​ውም መጠን ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዓ​ም​ዱም ውፍ​ረት አንድ ጋት ነበረ፤ ውስጠ ክፍ​ትም ነበረ። ሁለ​ተ​ኛ​ውም ዓምድ እን​ዲሁ ነበረ። በሁ​ለ​ቱም አዕ​ማድ ራስ ላይ እን​ዲ​ቀ​መጡ ከፈ​ሰሰ ናስ ሁለት ጕል​ላ​ትን ሠራ፤ የአ​ን​ዱም ጕል​ላት ቁመት አም​ስት ክንድ፥ የሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም ጕል​ላት ቁመት አም​ስት ክንድ ነበረ። በአ​ዕ​ማ​ዱም ራስ ላይ የነ​በ​ሩ​ትን ጕል​ላ​ቶች ይሸ​ፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መር​በብ ሥራ አደ​ረገ፤ አን​ዱም መር​በብ ለአ​ንዱ ጕል​ላት፥ ሁለ​ተ​ኛ​ውም መር​በብ ለሁ​ለ​ተ​ኛው ጕል​ላት ነበረ። ሮማ​ኖ​ች​ንም ሠራ፤ በአ​ንድ ጕል​ላት ዙሪያ በሁ​ለት ተራ፥ በአ​ን​ድም መር​በብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እን​ዲ​ሁም ለሁ​ለ​ተ​ኛው ጕል​ላት አደ​ረገ። በወ​ለ​ሉም አዕ​ማድ በነ​በ​ሩት ጕል​ላ​ቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚ​መ​ስል ሥራ አራት ክንድ አድ​ርጎ ቀረጸ። በሁ​ለ​ቱም አዕ​ማድ በነ​በ​ሩት ጕል​ላ​ቶች ላይ በመ​ር​በቡ ሥራ አጠ​ገብ ሮማ​ኖ​ቹን አደ​ረገ። ሮማ​ኖ​ቹም በአ​ንዱ ወገን ሁለት መቶ ነበሩ። የሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም ጕል​ላት እን​ዲሁ ነበረ። አዕ​ማ​ዱ​ንም በመ​ቅ​ደሱ ወለል አጠ​ገብ አቆ​ማ​ቸው፤ የቀ​ኙ​ንም ዓምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግ​ራ​ው​ንም ዓምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው። በአ​ዕ​ማ​ዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚ​መ​ስል ሥራ አደ​ረገ። እን​ዲ​ሁም የአ​ዕ​ማዱ ሥራ ተጨ​ረሰ። ከፈ​ሰ​ሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመ​ቱም አም​ስት ክንድ፥ በዙ​ሪ​ያ​ውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኩሬ ሠራ። ከከ​ን​ፈ​ሩም በታች ለአ​ንድ ክንድ ዐሥር፥ ለአ​ንድ ክን​ድም ዐሥር ጕብ​ጕ​ቦች አዞ​ረ​በት፤ ከን​ፈ​ሮ​ቹም እንደ ጽዋ ከን​ፈር ነበሩ። በው​ስ​ጡም አበ​ቦች በቅ​ለ​ው​በት ነበር። ውፍ​ረ​ቱም ስን​ዝር ነበር። ኩሬ​ውም በዐ​ሥራ ሁለት በሬ​ዎች ምስል ላይ ተቀ​ምጦ ነበር፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስ​ቱም ወደ ምዕ​ራብ፥ ሦስ​ቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስ​ቱም ወደ ምሥ​ራቅ ይመ​ለ​ከቱ ነበር። ኩሬ​ውም በላ​ያ​ቸው ነበረ፤ የሁ​ሉም ጀር​ባ​ቸው በስ​ተ​ው​ስጥ ነበረ። ውፍ​ረ​ቱም አንድ ጋት ነበረ። ከን​ፈ​ሩም እንደ ጽዋ ከን​ፈር ተሠ​ርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበ​ባ​ዎች ሆኖ ተከ​ር​ክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባ​ዶስ መስ​ፈ​ሪያ ይይዝ ነበር። ዐሥ​ርም የናስ መቀ​መ​ጫ​ዎ​ችን ሠራ፤ የአ​ን​ዱም መቀ​መጫ ርዝ​መት አራት ክንድ፥ ወር​ዱም አራት ክንድ፥ ቁመ​ቱም ሦስት ክንድ ነበረ። መቀ​መ​ጫ​ዎ​ች​ንም እን​ዲሁ ሠራ፤ እርስ በር​ሳ​ቸ​ውም አያ​ይዞ ሰን​በር ባለው ክፈፍ ሠራ​ቸው። በክ​ፈ​ፎ​ቹም መካ​ከል በነ​በሩ ሰን​በ​ሮች ላይ አን​በ​ሳ​ዎ​ችና በሬ​ዎች፥ ኪሩ​ቤ​ልም ነበሩ፤ እን​ዲ​ሁም በክ​ፈ​ፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአ​ን​በ​ሳ​ዎ​ቹና ከበ​ሬ​ዎቹ በታች ሻኩራ የሚ​መ​ስል ተን​ጠ​ል​ጥሎ ነበር። በየ​መ​ቀ​መ​ጫ​ዎ​ቹም ሁሉ አራት የናስ መን​ኰ​ራ​ኵ​ሮች ነበ​ሩ​ባ​ቸው፤ መን​ኰ​ራ​ኵ​ሮ​ቹም የሚ​ዞ​ሩ​በ​ትን የናስ ወስ​ከ​ምት ሠራ፤ ከመ​ታ​ጠ​ቢ​ያ​ውም ሰን በታች በአ​ራቱ ማዕ​ዘን በኩል አራት በም​ስል የፈ​ሰሱ እግ​ሮች ነበሩ። በክ​ፈ​ፉም ውስጥ የነ​በረ አን​ገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አን​ገ​ቱም ድቡ​ል​ቡል ነበረ፤ ቁመ​ቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአ​ን​ገ​ቱም ላይ ቅርጽ ነበ​ረ​በት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕ​ዘን ነበረ እንጂ ድቡ​ል​ቡል አል​ነ​በ​ረም። አራ​ቱም መን​ኰ​ራ​ኵ​ሮች ከሰ​ን​በ​ሮቹ በታች ነበሩ፤ የመ​ን​ኰ​ራ​ኵ​ሮ​ቹም ወስ​ከ​ምት በመ​ቀ​መ​ጫው ውስጥ ነበረ፤ የመ​ን​ኰ​ራ​ኵ​ሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ። የመ​ን​ኰ​ራ​ኵ​ሮ​ቹም ሥራ እንደ ሰረ​ገላ መን​ኰ​ራ​ኵር ሥራ ነበረ፤ ወስ​ከ​ም​ቶ​ቹና የመ​ን​ኰ​ራ​ኵ​ሮቹ ክፈፍ፥ ቅት​ር​ቶ​ቹም፥ ወስ​ከ​ምቱ የሚ​ገ​ባ​በት ቧምቧ ሁሉ በም​ስል የፈ​ሰሰ ነበር። በየ​አ​ን​ዳ​ን​ዱም መቀ​መጫ በአ​ራቱ ማዕ​ዘን በኩል አራት ደገ​ፋ​ዎች ነበሩ፤ ደገ​ፋ​ዎ​ቹም ከመ​ቀ​መ​ጫው ጋር ተጋ​ጥ​መው ነበር። በመ​ቀ​መ​ጫ​ውም ራስ ላይ ስን​ዝር የሚ​ሆን ድቡ​ል​ቡል ነገር ነበረ፤ በመ​ቀ​መ​ጫ​ውም ላይ የነ​በሩ መያ​ዣ​ዎ​ችና ሰን​በ​ሮች ከእ​ርሱ ጋር ይጋ​ጠሙ ነበረ፤ ከላ​ይም ክፍት ነበረ፤ በክ​ፈ​ፎ​ቻ​ቸ​ውም ኪሩ​ቤ​ልና አን​በ​ሶች የዘ​ን​ባባ ዛፎ​ችም ነበሩ፤ እያ​ን​ዳ​ን​ዱም ፊት ለፊት በስ​ተ​ው​ስ​ጥና በዙ​ሪ​ያው ተያ​ይዞ ነበር። እን​ዲ​ሁም ዐሥ​ሩን መቀ​መ​ጫ​ዎች ሠራ፤ ሁሉም በመ​ጠን፥ በን​ድ​ፍም ትክ​ክ​ሎች ነበሩ። ዐሥ​ሩ​ንም የናስ መታ​ጠ​ቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታ​ጠ​ቢያ ሰን አርባ የባ​ዶስ መስ​ፈ​ሪያ ያነሣ ነበር፤ እያ​ን​ዳ​ን​ዱም መታ​ጠ​ቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በዐ​ሥ​ሩም መቀ​መ​ጫ​ዎች ላይ በእ​ያ​ን​ዳ​ንዱ አንድ አንድ መታ​ጠ​ቢያ ሰን ይቀ​መጥ ነበር። አም​ስ​ቱ​ንም መቀ​መ​ጫ​ዎች በቤቱ ቀኝ፥ አም​ስ​ቱ​ንም በቤቱ ግራ አኖ​ራ​ቸው፤ ኩሬ​ው​ንም በቤቱ ቀኝ በአ​ዜብ ፊት ለፊት በስ​ተ​ም​ሥ​ራቅ አኖ​ረው።

1 ነገሥት 7:1-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሰሎሞን የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ ለመጨረስ ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት። የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፣ ወርዱ አምሳ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፣ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት። ቤቱ ከምሰሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ አምስት፣ በድምሩ አርባ አምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር። መስኮቶቹም ከፍ ብለው የተሠሩ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ። በሮቹ በሙሉ ባለ አራት ማእዘን መቃኖች ያሏቸው፣ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ። ሰሎሞን፣ “ባለ ብዙ ምሰሶ አዳራሽ” የተባለ ቤት ሠራ፤ የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሠላሳ ክንድ፣ ነበር፤ በስተ ፊት በኩልም ጣራ ያለውና በአዕማድ የተደገፈ መመላለሻ ነበረው። ዳኝነት የሚያይበትንም የዙፋን ችሎት አዳራሽ ሠራ፤ ይኸውም የፍትሕ አዳራሽ የተባለው ነው፤ ይህንም ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ሸፈነው። ከአዳራሹ በስተ ጀርባ ባለው አደባባይ መኖሪያው እንዲሆን የተሠራው ቤተ መንግሥትም የዚሁ ተመሳሳይ ነበር። ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ይህንኑ ቤተ መንግሥት የመሰለ አዳራሽ ሠራ። ከውጭ አንሥቶ እስከ ትልቁ አደባባይ፣ ከመሠረቱ አንሥቶ እስከ ድምድማቱ ያለው የሕንጻ ሥራ በሙሉ፣ በውስጥም በውጭም በልክ በልኩ በተቈረጠና አምሮ በተስተካከለ ምርጥ ድንጋይ የተሠራ ነበር። መሠረቱም ዐሥርና ስምንት ክንድ ርዝመት ባላቸውና ምርጥ በሆኑ ታላላቅ ድንጋዮች የተሠራ ነበር። በላዩም ላይ ምርጥ የሆኑ፣ በልክ በልኩ የተቈረጡ ድንጋዮችና የዝግባ ሳንቃዎች ነበሩ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ከመመላለሻ በረንዳው ጭምር እንደ ትልቁ አደባባይ አምሮ በተጠረበ ሦስት ረድፍ ድንጋይና ተስተካክሎ በተከረከመ በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ የታጠረ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞንም መልእክተኛ ልኮ ኪራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ አስመጣ፤ የኪራም እናት ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን፣ የናስ ሥራ ባለሙያ ነበር። ኪራም በማናቸውም የናስ ሥራ ጥበብን፣ ማስተዋልንና ዕውቀትን የተሞላ ሰው ነበር፤ እርሱም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጥቶ የተመደበለትን ሥራ ሁሉ አከናወነ። ኪራም የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ፣ ዙሪያው ዐሥራ ሁለት ክንድ የሆነ፣ ሁለት የናስ ምሰሶዎች ሠራ። እንዲሁም በምሰሶዎቹ ዐናት ላይ የሚሆኑ፣ ሁለት ጕልላት ከቀለጠ ናስ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበር። በምሰሶዎቹ ዐናት ላይ ላሉት ጕልላቶችም ጌጥ እንዲሆኑ፣ ለእያንዳንዳቸው ሰባት የመረብ ሰንሰለት አበጀ፤ ደግሞም በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን ጕልላቶች ለማስጌጥ የእያንዳንዱን መረብ ዙሪያ የሚከብቡ ሮማኖች በሁለት ረድፍ ሠራ፤ ለሁለቱም ጕልላቶች ያደረገው ተመሳሳይ ነበር። በመመላለሻው ምሰሶዎች ዐናት ላይ ያሉት ጕልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን፣ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። በሁለቱም የምሰሶ ጕልላቶችና ከመርበቡ ቀጥሎ ባለው የክብ ቅርጽ ላይ ዙሪያውን በሙሉ ሁለት መቶ ሮማኖች በተርታ ነበሩ። ምሰሶዎቹንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ላይ አቆመ፤ በስተ ደቡብ ያቆመውን ምሰሶ ያኪን፣ በስተ ሰሜን በኩል ያለውንም ቦዔዝ ብሎ ጠራው። ዐናቱ ላይ ያሉት ጕልላቶች የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ። ቅርጹ ክብ፣ ስፋቱ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፣ ቁመቱ አምስት ክንድ የሆነ ክብ ገንዳ ከቀለጠ ብረት ሠራ፤ ዙሪያውም ሲለካ ሠላሳ ክንድ ሆነ። ከከንፈሩም ዝቅ ብሎ፣ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ እንደ ቅል ያሉ ዐሥር ቅርጾች ዙሪያውን በሁለት ረድፍ ከብበውታል፤ እነዚህም ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ተሠርተው ነበር። ገንዳውም፣ ሦስቱ ፊታቸውን ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ባዞሩ የዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ገንዳው በላያቸው ሆኖ የሁሉም የኋላ አካል በመካከል ላይ የገጠመ ነበር። የገንዳው ውፍረት አንድ ጋት ሲሆን፣ የከንፈሩ ጠርዝ ደግሞ እንደ አበባ ቅርጽ ሆኖ፣ የጽዋ ከንፈር የመሰለ ነው፤ ይህም አርባ ሁለት ሺሕ ሊትር ያህል ውሃ የሚይዝ ነበር። እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዐሥር ባለ መንኰራኵር የዕቃ ማስቀመጫዎች ከመዳብ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ርዝመት አራት ክንድ፣ ወርድ አራት ክንድ፣ ቁመትም ሦስት ክንድ ነበር። የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ባለ አራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው። ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኮርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኮርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጕንጕን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጕንጕን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው። በዕቃ ማስቀመጫዎቹም ውስጥ ጥልቀቱ አንድ ክንድ የሆነ ባለ ክብ ክፍተት ነበር፤ ይህም ክፍተት ድቡልቡል ሆኖ ከታች ከመቆሚያው በኩል ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ወርድ ሲኖረው፣ በክፍተቱም ዙሪያ ቅርጾች ነበሩ፤ ክፈፎቹ ግን ባለ አራት ማእዘን እንጂ ክብ አልነበሩም። አራቱ መንኰራኵሮች በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ናስ ሥር ሲሆኑ፣ የመንኰራኵሮቹ ወስከምቶች ደግሞ ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር የተያያዙ ነበሩ፤ የእያንዳንዱም መንኰራኵር ስፋት አንድ ክንድ ተኩል ነበር። መንኰራኵሮቹ የሠረገላ መንኰራኵር መሰል ሲሆኑ፣ ወስከምቶቹ የመንኰራኵሮቹ ክፈፎችና ዐቃፊዎቻቸው እንዲሁም ወስከምቶቹ የሚገቡባቸው ቧምቧዎች በሙሉ ከቀለጠ ብረት የተሠሩ ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ወጣ ያለ እጀታ ነበረው። በዕቃ ማስቀመጫው ጫፍ ላይ ግማሽ ክንድ የሆነ ዙሪያ ክብ ነበረበት፤ ድጋፎቹና ጠፍጣፋ ናሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ዐናት ጋር የተያያዙ ነበሩ። እርሱም በድጋፎቹና በጠፍጣፋ ናሶቹ ላይ ባለው ቦታ ሁሉ፣ ዙሪያውን የአበባ ጕንጕን እያደረገ ኪሩቤልን፣ አንበሶችንና የዘንባባ ዛፎችን ቀረጸ። ዐሥሩም የዕቃ ተሸካሚዎች የተሠሩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ሁሉም ከአንድ ቅርጽ ቀልጠው የወጡ ስለሆነ፣ በመጠንና በቅርጽ ፍጹም ተመሳሳይ ነበሩ። ከዚያም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ የሚሆን፣ እያንዳንዱ ስምንት መቶ ሰማንያ ሊትር የሚይዝ ዐሥር የናስ መታጠቢያ ገንዳ ሠራ፤ ስፋቱም አራት ክንድ ነበር። ከዕቃ ማስቀመጫዎቹም አምስቱን ከመቅደሱ በስተ ደቡብ፣ አምስቱን በስተ ሰሜን በኩል አኖረ፤ ገንዳውንም ከቤተ መቅደሱ በደቡብ ምሥራቅ ጫፍ ላይ በስተ ደቡብ አኖረው።

1 ነገሥት 7:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሰሎሞንም የራሱን ቤት በዐሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፤ የቤቱንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ። የሊባኖስ ዱር ቤት የሚባል ቤትን ሠራ፤ ርዝመቱንም መቶ ክንድ፥ ስፋቱንም አምሳ ክንድ፥ ቁመቱንም ሠላሳ ክንድ አደረገ፤ የዝግባም እንጨት በሦስት ተራ በተሠሩ አዕማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአዕማዱም ላይ የዝግባ እንጨት አግዳሚ ሰረገሎች ነበሩ። በአዕማዱም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዝግባ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፤ አዕማዱም በአንዱ ተራ ዐሥራ አምስት፥ በአንዱ ተራ ዐሥራ አምስት እየሆኑ አርባ አምስት ነበሩ። መስኮቶቹም በሦስት ተራ ነበሩ፤ መስኮቶቹም ፊት ለፊት ይተያዩ ነበሩ። ደጆቹና መስኮቶቹም ሁሉ አራት ማዕዘን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ሆነው ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር። አዕማዱም ያሉበትን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ አዕማድና መድረክ ያሉበት ወለል ነበረ። ደግሞም የሚፈርድበት ዙፋን ያለበትን የፍርድ ቤት አደረገ። ከወለሉም አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ እንጨት ተሸፍኖ ነበር። ከፍርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌላውም አደባባይ ውስጥ የነበረውን መኖሪያ ቤት እንዲሁ ሠራ። እንደዚሁም ያለ ቤት ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ቤት ሠራ። እነዚህም ሁሉ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጉልላቱ ድረስ በጥሩ በተጠረበና በውስጥና በውጭ በልክ በተከረከመ ድንጋይ ተሠርተው ነበር፤ በውጭውም እስከ ታላቁ አደባባይ ድረስ እንዲሁ ነበረ። መሠረቱም ዐሥር ወይም ስምንት ክንድ በሆነ በጥሩና በታላቅ ድንጋይ ተሠርቶ ነበር። በላዩም ልክ ሆኖ የተከረከመ ጥሩ ድንጋይና የዝግባ ሳንቃ ነበረ። በታላቁም አደባባይ ዙሪያ የነበረው ቅጥር እንደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ውስጠኛው አደባባይ ቅጥርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ተራ በተጠረበ ድንጋይ አንዱም ተራ በዝግባ ሳንቃ ተሠርቶ ነበር። ንጉሡም ሰሎሞን ልኮ ኪራምን ከጢሮስ አስመጣ። እርሱም ከንፍታሌም ወገን የነበረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፤ አባቱም የጢሮስ ሰው ናስ ሠራተኛ ነበረ፤ የናስንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥበብ በማስተዋል በብልሃትም ተሞልቶ ነበር። ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን መጥቶ ሥራውን ሁሉ ሠራ። ሁለቱን የናስ አዕማድ አደረገ፤ የአንዱም ዐምድ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፤ የዙሪያውም መጠን ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዐምዱም ውፍረት አንድ ጋት ነበረ፤ ውስጠ ክፍትም ነበረ። ሁለተኛውም ዐምድ እንዲሁ ነበረ። በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ እንዲቀመጡ ከፈሰሰ ናስ ሁለት ጕልላት ሠራ፤ የአንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ፥ የሁለተኛውም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ። በአዕማዱም ራስ ላይ የነበሩትን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መርበብ ሥራ አደረገ፤ አንዱም መርበብ ለአንዱ ጕልላት ሁለተኛውም መርበብ ለሁለተኛው ጕልላት ነበረ። ሮማኖችንም ሠራ፤ በአንድ ጕልላት ዙሪያ በተራ ሁለት መቶ ሮማኖች ነበሩ፤ በአንድም መርበብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እንዲሁም ለሁለተኛው ጕልላት አደረገ። በወለሉም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አራት ክንድ አድርጎ ቀረጸ። በሁለቱም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ በመርበቡ ሥራ አጠገብ ሮማኖቹን አደረገ። አዕማዱንም በመቅደሱ ወለል አጠገብ አቆማቸው፤ የቀኙንም ዐምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግራውንም ዐምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው። በአዕማዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ ነበር፤ እንዲሁም የአዕማዱ ሥራ ተጨረሰ። ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ። ከከንፈሩም በታች ለአንድ ክንድ ዐሥር ለአንድ ክንድም ዐሥር ጉብጉቦች አዞረበት፤ እርሱም በቀለጠ ጊዜ ጉብጉቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። ኵሬውም በዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። ኵሬውም በላያቸው ነበረ፤ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። ውፍረቱም አንድ ጋት ነበረ፤ ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር ተሠርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበባዎች ሆኖ ተከርክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር። ዐሥርም የናስ መቀመጫዎች ሠራ፤ የአንዱም መቀመጫ ርዝመት አራት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ ነበረ። የመቀመጫውም ሥራ እንዲህ ነበረ፤ በክፈፎችም መካከል ያለው ሰንበር ይመስል ነበር። በክፈፎቹም መካከል በነበሩ ሰንበሮች ላይ አንበሳዎችና በሬዎች ኪሩቤልም ነበሩ፤ እንዲሁም በክፈፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአንበሳዎቹና ከበሬዎቹ በታች ሻኵራ የሚመስል ተንጠልጥሎ ነበር። በየመቀመጫዎቹም ሁሉ አራት የናስ መኰራኵሮች ነበሩባቸ፤ መንኰራኵሮቹም የሚዞሩበትን የናስ ወስከምት ሠራ፤ ከመታጠቢያውም ሰን በታች በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት በምስል የፈሰሱ እግሮች ነበሩ። በክፈፉም ውስጥ የነበረ አንገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አንገቱም ድቡልቡል ነበረ፤ ቁመቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአንገቱም ላይ ቅርጽ ነበረበት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕዘን ነበረ እንጂ ድቡልቡል አልነበረም። አራቱም መንኰራኵሮች ከሰንበሮቹ በታች ነበሩ፤ የመንኰራኵሮቹም ወስከምት በመቀመጫው ውስጥ ነበረ፤ የመኰራኵሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ። የመንኰራኵሮቹም ሥራ እንደ ሠረገላ መንኰራኵር ነበረ፤ ወስከምቶቹና የመንኰራኵሮቹ ክፈፍ ቅትርቶቹም ወስከምቱም የሚገባበት ቧምቧ ሁሉ በምስል የፈሰሰ ነበረ። በእያንዳንዱም መቀመጫ በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት ደገፋዎች ነበሩ፤ ደገፋዎቹም ከመቀመጫው ጋር ተገጥመው ነበር። በመቀመጫውም ላይ ስንዝር የሚሆን ድቡልቡል ነገር ነበረ፤ በመቀመጫውም ላይ የነበሩ መያዣዎችና ሰንበሮች ከእርሱ ጋር ይጋጠሙ ነበር። በመያዣውና በሰንበሮቹ ላይ ኪሩቤልንና አንበሳዎችን የዘንባባውንም ዛፍ እንደ መጠናችው ቀረጸ፤ በዙሪያውም ሻኵራ አደረገ። እንዲሁ ዐሥሩን መቀመጫዎች ሠራ፤ ሁሉም በምስልና በመጠን በንድፍም ትክክሎች ነበሩ። ዐሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በዐሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር። አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።

1 ነገሥት 7:1-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሰሎሞን ለራሱ የሚሆን ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ቤተ መንግሥቱንም ለመሥራት ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት፤ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ አርባ አራት ሜትር፥ ወርዱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ አዳራሹም በእያንዳንዱ ረድፍ ዐሥራ አምስት ሆነው በሦስት ረድፍ የቆሙ አርባ አምስት ምሰሶዎች ነበሩት፤ በምሰሶዎቹም ላይ የተጋደሙ፥ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ ሠረገሎችና በየመካከላቸው የገቡ ሳንቃዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም በላይ በምሰሶዎቹ የተደገፉ ዕቃ ቤቶች ነበሩ፤ የእነዚህም ዕቃ ቤቶች ጣራ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር፤ ትይዩ የሆኑት የሕንጻው ሁለት ግንቦች እያንዳንዳቸው በመደዳ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩአቸው። በሮቹና መስኮቶቹ ሁሉ ባለአራት ማእዘን መቃኖች ነበሩአቸው፤ ለእያንዳንዱ ግንብ በረድፍ የተሠሩ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ግንብ መስኮቶች ከሌላው ግንብ መስኮቶች ጋር ትይዩ ነበሩ። “ባለ ብዙ ምሰሶዎች” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ወርዱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ በብዙ ምሰሶዎች የተደገፈና ጣራ የተሠራለት መመላለሻ ታዛም ነበረው። ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበትም የዙፋን አዳራሽ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። ከችሎቱም አዳራሽ በስተ ኋላ በሚገኘው ሌላ አደባባይ ሰሎሞን የሚኖርበትን ሕንጻ እንደ ሌሎቹ ሕንጻዎች አድርጎ አሠራ፤ የግብጽ ንጉሥ ልጅ ለነበረችው ሚስቱም ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት አሠራላት። እነዚህ ሁሉ ሕንጻዎችና ታላቁ አደባባይ ጭምር ከመሠረታቸው እስከ ድምድማቸው በጥሩ ታላላቅ ድንጋዮች አጊጠው የተሠሩ ነበሩ፤ ድንጋዮቹ በዚያም በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ በፊትም በኋላም በልክ ተጠርበውና ተከርክመው የመጡ ነበሩ። መሠረቱም የተሠራው በዚያው በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ ተዘጋጅተው በመጡ ታላላቅ ድንጋዮች ነበር፤ ከታላላቆቹም ድንጋዮች ውስጥ የአንዳንዱ ጥርብ ድንጋይ ርዝመት ሦስት ሦስት ሜትር ተኩል ሲሆን፥ የሌሎቹ ደግሞ አራት ሜትር ነበር። በእነዚህም ታላላቅ ድንጋዮች ላይ በልክ የተሠሩ ሌሎች ድንጋዮችና ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ አግዳሚ ሠረገሎች ነበሩ። የቤተ መንግሥቱ አደባባይ፥ የቤተ መቅደሱ ውስጣዊ አደባባይና ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባው በር በእያንዳንዱ ባለ ሦስት ረድፍ የጥርብ ድንጋይ ሕንጻ ላይ አንዳንድ ረድፍ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሠረገላ የተጋደመባቸው ግንቦች ነበሩ። ሰሎሞንም ሑራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ ከተማ አስጠራ፤ ሑራም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ ቀደም ብሎ የሞተው የሑራም አባትም የጢሮስ ተወላጅ ሲሆን እርሱም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ የሑራም እናት የንፍታሌም ነገድ ተወላጅ ነበረች፤ ሑራም በእጅ ጥበብ ብዙ ልምድ ያለው ብልህ ሰው ነበር፤ ከንጉሥ ሰሎሞን በተደረገለት ጥሪ መሠረት መጥቶ የተመደበለትን የነሐስ ሥራ ሁሉ ሠራ። ሑራም የእያንዳንዳቸው ቁመት ስምንት ሜትር፥ የዙሪያ ስፋታቸው አምስት ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ውስጡ ክፍት የሆነ አራት ጣት ውፍረት ካለው ነሐስ ሁለት ምሰሶዎችን ሠራ። እንዲሁም በምሰሶዎቹ ላይ የሚቆሙ የእያንዳንዳቸው ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት የነሐስ ጒልላቶችን ሠራ። በምሰሶዎቹም ራስ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ያስጌጡ ዘንድ በሰባት ረድፍ የተሠሩ መረቦችን ሠራ፤ አንዱን መረብ ለአንድ ጉልላት፥ ሁለተኛውን መረብ ለሁለተኛው ጉልላት አደረገ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉትን ጉልላቶች ለማስጌጥ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ። ለየአንዳንዱም ጉልላት እንዲሁ አደረገ። በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጒልላቶች ቁመታቸው አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን የአሸንድዬ አበባን በሚመስል ሥራ ተጊጠው ነበር፤ እነርሱም ከመረቡ በላይ ባለው ክብ ስፍራ እንዲቆሙ ተደረገ፤ በእያንዳንዱም ጒልላት ዙሪያ በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ሁለት መቶ የሮማን ቅርጾች ነበሩ። ሑራም ከነሐስ የተሠሩትን ሁለት ምሰሶዎች በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ፊት ለፊት አቆማቸው፤ ከቤተ መቅደሱ መግቢያ በር በስተ ደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ ተጠራ፤ በስተ ሰሜን በኩል የቆመው ምሰሶ ደግሞ ቦዔዝ ተባለ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ የአሸንድዬ አበባ የሚመስሉ ከነሐስ የተሠሩ ጉልላቶች ነበሩ። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ዐይነት ተፈጸመ። ሑራም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ጥልቀት፥ አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የክብ ማእከል ርዝመት፤ ዐሥራ ሦስት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ዙሪያ ያለው አንድ ክብ ገንዳ ከነሐስ ሠራ። የገንዳው አፍ ውጫዊ ክፈፍ ሁሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በቅል አምሳል ከነሐስ የተሠሩና በሁለት ረድፍ የተደረደሩ፥ ቅርጾች ነበሩት። ገንዳውም ከነሐስ በተሠሩ ዐሥራ ሁለት የበሬዎች ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀመጠ፤ ኰርማዎቹም በየአቅጣጫው ፊታቸውን ወደ ውጪ መልሰው ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ሦስቱ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ይመስሉ ነበር። የገንዳው ጐኖች ውፍረት አንድ መዳፍ ነበር፤ የጽዋ ቅርጽ ያለው አበባ የሚመስል የአፉ ክፈፍ የአሸንድዬ አበባ ቅርጽ ነበረው፤ ይህም ገንዳ አርባ ሺህ ሊትር ያኽል ውሃ የሚይዝ ነበር። ሑራም የእያንዳንዱ ርዝመት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ወርዱ አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ ዐሥር ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችን ከነሐስ ሠራ። የዕቃ መቀመጫዎቹም የተሠሩት በክንፎቹ መካከል ልሙጥ በሆነ ነገር ነበር። ልሙጥ በሆነው ነገርም ላይ በአንበሶች፥ በበሬዎችና በኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ፤ ከአንበሶቹ፥ ከበሬዎቹና ከኪሩቤሉ ቅርጾች ራስጌና ግርጌ የአበባ ጒንጒን የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ፤ እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ከነሐስ የተሠሩ አራት መንኰራኲሮችና መንኰራኲሮቹ የሚሽከረከሩበት የነሐስ ወስከምቶች ነበራቸው፤ እንዲሁም በአራቱ ማእዘኖች የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበሩ፤ መደገፊያዎቹም የአበባ ጒንጒን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። የመታጠቢያ ገንዳውም አንገት ዐሥራ ስምንት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ እርሱም ክብ ነበር፤ ቁመቱም አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በአንገቱም ላይ ማስጌጫ ቅርጽ ነበረበት፤ የገንዳው ተሸካሚ ግን አራት ማእዘን ነበር እንጂ ክብ አልነበረም። የመንኰራኲሮቹም ቁመት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ መንኰራኲሮቹም በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ነሐስ ሥር ነበሩ፤ የመንኰራኲሮችም ወስከምቶች ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፤ መንኰራኲሮቹም የሠረገላ መንኰራኲሮችን ይመስሉ ነበር፤ ወስከምቶቻቸው፥ ቅትርቶቻቸውና ዐቃፊዎቻቸው ሁሉም ከነሐስ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ። የእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ማእዘኖች በየግርጌአቸው ከእነርሱው ጋር አንድ ወጥ ሆነው ከነሐስ የተሠሩ አራት መደገፊያዎች ነበሩአቸው። በእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ጫፍ ዙሪያ ክፈፍ ላይ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ክብ ቅርጽ ነበር፤ መደገፊያዎቹና ጠፍጣፋ ነሐሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። በእነዚሁ መደገፊያዎችና ጠፍጣፋ ነሐሶች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ በኪሩቤል፥ በአንበሶችና በዘንባባ ዛፎች አምሳል በተሠሩ ቅርጾች አጊጠው ነበር፤ እንዲሁም ዙሪያቸው የአበባ ጒንጒን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። እንግዲህ ዐሥሩ ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች የተሠሩት በዚህ ዐይነት ነበር። መጠናቸውና ቅርጻቸው እኩል ስለ ሆነ ሁሉም ተመሳሳይ ነበሩ። ሑራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎች ሠራ፤ እያንዳንዱ ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ያኽል ሲሆን፥ ስምንት መቶ ሊትር ያኽል ውሃ ይይዝ ነበር፤ ሑራምም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ፥ የቀሩትንም አምስቱን በቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን በኩል አቆመ፤ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው።

1 ነገሥት 7:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሰሎሞን ለራሱ የሚሆን ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ቤተ መንግሥቱንም ለመሥራት ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት። የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፥ ወርዱ አምሳ ክንድ፥ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፥ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት። ቤቱ ከምሰ ሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ አምስት፥ በድምሩ አርባ አምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፥ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር። ትይዩ የሆኑት የሕንጻው ሁለት ግንቦች እያንዳንዳቸው በመደዳ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩአቸው። በሮቹና መስኮቶቹ ሁሉ ባለ አራት ማእዘን መቃኖች ነበሩአቸው፤ ለእያንዳንዱ ግንብ በረድፍ የተሠሩ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ግንብ መስኮቶች ከሌላው ግንብ መስኮቶች ጋር ትይዩ ነበሩ። “ባለ ብዙ ምሰሶዎች” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ወርዱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ በብዙ ምሰሶዎች የተደገፈና ጣራ የተሠራለት መመላለሻ ታዛም ነበረው። ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበትም የዙፋን አዳራሽ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። ከችሎቱም አዳራሽ በስተ ኋላ በሚገኘው ሌላ አደባባይ ሰሎሞን የሚኖርበትን ሕንጻ እንደ ሌሎቹ ሕንጻዎች አድርጎ አሠራ፤ የግብጽ ንጉሥ ልጅ ለነበረችው ሚስቱም ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት አሠራላት። እነዚህ ሁሉ ሕንጻዎችና ታላቁ አደባባይ ጭምር ከመሠረታቸው እስከ ድምድማቸው በጥሩ ታላላቅ ድንጋዮች አጊጠው የተሠሩ ነበሩ፤ ድንጋዮቹ በዚያም በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ በፊትም በኋላም በልክ ተጠርበውና ተከርክመው የመጡ ነበሩ። መሠረቱም የተሠራው በዚያው በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ ተዘጋጅተው በመጡ ታላላቅ ድንጋዮች ነበር፤ ከታላላቆቹም ድንጋዮች ውስጥ የአንዳንዱ ጥርብ ድንጋይ ርዝመት ሦስት ሦስት ሜትር ተኩል ሲሆን፥ የሌሎቹ ደግሞ አራት ሜትር ነበር። በእነዚህም ታላላቅ ድንጋዮች ላይ በልክ የተሠሩ ሌሎች ድንጋዮችና ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ አግዳሚ ሠረገሎች ነበሩ። የቤተ መንግሥቱ አደባባይ፥ የጌታ ቤት ውስጣዊ አደባባይና ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባው በር በእያንዳንዱ ባለ ሦስት ረድፍ የጥርብ ድንጋይ ሕንጻ ላይ አንዳንድ ረድፍ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሠረገላ የተጋደመባቸው ግንቦች ነበሩ። ሰሎሞንም ሑራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ ከተማ አስጠራ። ሑራም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ ቀደም ብሎ የሞተው የሑራም አባትም የጢሮስ ተወላጅ ሲሆን እርሱም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ የሑራም እናት የንፍታሌም ነገድ ተወላጅ ነበረች፤ ሑራም በእጅ ጥበብ ብዙ ልምድ ያለው ብልህ ሰው ነበር፤ ከንጉሥ ሰሎሞን በተደረገለት ጥሪ መሠረት መጥቶ የተመደበለትን የነሐስ ሥራ ሁሉ ሠራ። ሑራም የእያንዳንዳቸው ቁመት ስምንት ሜትር፥ የዙሪያ ስፋታቸው አምስት ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ውስጡ ክፍት የሆነ አራት ጣት ውፍረት ካለው ነሐስ ሁለት ምሰሶዎችን ሠራ። እንዲሁም በምሰሶዎቹ ላይ የሚቆሙ የእያንዳንዳቸው ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት የነሐስ ጉልላቶችን ሠራ። በምሰሶዎቹም ራስ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ያስጌጡ ዘንድ በሰባት ረድፍ የተሠሩ መረቦችን ሠራ፤ አንዱን መረብ ለአንድ ጉልላት፥ ሁለተኛውን መረብ ለሁለተኛው ጉልላት አደረገ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉትን ጉልላቶች ለማስጌጥ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ። ለየአንዳንዱም ጉልላት እንዲሁ አደረገ። በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጉልላቶች ቁመታቸው አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን የአሸንድዬ አበባን በሚመስል ሥራ ተጊጠው ነበር። እነርሱም ከመረቡ በላይ ባለው ክብ ስፍራ እንዲቆሙ ተደረገ፤ በእያንዳንዱም ጉልላት ዙሪያ በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ሁለት መቶ የሮማን ቅርጾች ነበሩ። ሑራም ከነሐስ የተሠሩትን ሁለት ምሰሶዎች በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ፊት ለፊት አቆማቸው፤ ከቤተ መቅደሱ መግቢያ በር በስተ ደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ ተጠራ፤ በስተ ሰሜን በኩል የቆመው ምሰሶ ደግሞ ቦዔዝ ተባለ። በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ የአሸንድዬ አበባ የሚመስሉ ከነሐስ የተሠሩ ጉልላቶች ነበሩ። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ዓይነት ተፈጸመ። ሑራም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ጥልቀት፥ አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የክብ ማእከል ርዝመት፤ ዐሥራ ሦስት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ዙሪያ ያለው አንድ ክብ ገንዳ ከነሐስ ሠራ። የገንዳው አፍ ውጫዊ ክፈፍ ሁሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በቅል አምሳል ከነሐስ የተሠሩና በሁለት ረድፍ የተደረደሩ፥ ቅርጾች ነበሩት። ገንዳውም ከነሐስ በተሠሩ ዐሥራ ሁለት የበሬዎች ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀመጠ፤ ኰርማዎቹም በየአቅጣጫው ፊታቸውን ወደ ውጪ መልሰው ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ሦስቱ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ይመስሉ ነበር። የገንዳው ጐኖች ውፍረት አንድ መዳፍ ነበር፤ የጽዋ ቅርጽ ያለው አበባ የሚመስል የአፉ ክፈፍ የአሸንድዬ አበባ ቅርጽ ነበረው፤ ይህም ገንዳ አርባ ሺህ ሊትር ያኽል ውሃ የሚይዝ ነበር። ሑራም የእያንዳንዱ ርዝመት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ወርዱ አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ ዐሥር ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችን ከነሐስ ሠራ። የዕቃ መቀመጫዎቹም የተሠሩት በክንፎቹ መካከል ልሙጥ በሆነ ነገር ነበር። ልሙጥ በሆነው ነገርም ላይ በአንበሶች፥ በበሬዎችና በኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ፤ ከአንበሶቹ፥ ከበሬዎቹና ከኪሩቤሉ ቅርጾች ራስጌና ግርጌ የአበባ ጉንጉን የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ከነሐስ የተሠሩ አራት መንኰራኲሮችና መንኰራኲሮቹ የሚሽከረከሩበት የነሐስ ወስከምቶች ነበራቸው፤ እንዲሁም በአራቱ ማእዘኖች የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበሩ፤ መደገፊያዎቹም የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። የመታጠቢያ ገንዳውም አንገት ዐሥራ ስምንት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ እርሱም ክብ ነበር፤ ቁመቱም አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በአንገቱም ላይ ማስጌጫ ቅርጽ ነበረበት፤ የገንዳው ተሸካሚ ግን አራት ማእዘን ነበር እንጂ ክብ አልነበረም። የመንኰራኲሮቹም ቁመት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ መንኰራኲሮቹም በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ነሐስ ሥር ነበሩ፤ የመንኰራኲሮችም ወስከምቶች ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፤ መንኰራኲሮቹም የሠረገላ መንኰራኲሮችን ይመስሉ ነበር፤ ወስከምቶቻቸው፥ ቅትርቶቻቸውና ዐቃፊዎቻቸው ሁሉም ከነሐስ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ። የእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ማእዘኖች በየግርጌአቸው ከእነርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ከነሐስ የተሠሩ አራት መደገፊያዎች ነበሩአቸው። በእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ጫፍ ዙሪያ ክፈፍ ላይ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ክብ ቅርጽ ነበር፤ መደገፊያዎቹና ጠፍጣፋ ነሐሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። በእነዚሁ መደገፊያዎችና ጠፍጣፋ ነሐሶች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ በኪሩቤል፥ በአንበሶችና በዘንባባ ዛፎች አምሳል በተሠሩ ቅርጾች አጊጠው ነበር፤ እንዲሁም ዙሪያቸው የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። እንግዲህ ዐሥሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች የተሠሩት በዚህ ዓይነት ነበር። መጠናቸውና ቅርጻቸው እኩል ስለ ሆነ ሁሉም ተመሳሳይ ነበሩ። ሑራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎችን ሠራ፤ እያንዳንዱም ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ያኽል ሲሆን፥ ስምንት መቶ ሊትር ያኽል ውሃ ይይዝ ነበር። ሑራምም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ፥ የቀሩትንም አምስቱን በቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን በኩል አቆመ፤ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው።