ሰሎሞንም የራሱን ቤት በዐሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፤ የቤቱንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ። የሊባኖስ ዱር ቤት የሚባል ቤትንም ሠራ፤ ርዝመቱንም መቶ ክንድ፥ ስፋቱንም አምሳ ክንድ፥ ቁመቱንም ሠላሳ ክንድ አደረገ፤ የዋንዛም እንጨት በሦስት ወገን በተሠሩ አዕማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአዕማዱም ላይ የዋንዛ እንጨት አግዳሚ ሰረገሎች ነበሩ። በአዕማዱም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዋንዛ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፤ አዕማዱም በአንዱ ወገን ዐሥራ አምስት፥ በአንዱ ወገን ዐሥራ አምስት የሆኑ አርባ አምስት ነበሩ። መስኮቶቹም በሦስት ወገን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ወገን ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር። ደጆቹ፥ መቃኖቹና የታችኛውና የላይኛው መድረኮች ሁሉ አራት ማዕዘን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ወገን ሆነው ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር። አዕማዱም ያሉበትን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ ታላቅ አዕማድና መድረክ ያሉበት ወለል ነበረ። የሚፈርድበትም የቤቱ ዙፋን በዚያ አለ። ለመፍረጃውም ቤትን ሠራ፤ ከላይ እስከ ታችም በዋንዛ እንጨት አያያዘው። ከፍርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌላውም አደባባይ ውስጥ የነበረውን የሚኖርበትን ቤት እንዲሁ ሠራ፤ እንደዚህም ቤት ያለ ቤትን ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ሠራ። ይህም ሁሉ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጕልላቱ ድረስ በከበረና በተጠረበ በውስጥና በውጭ በልክ በተከረከመ ድንጋይ ተሠርቶ ነበር፤ በውጭውም እስከ ታላቁ አደባባይ ድረስ እንዲሁ ነበረ። መሠረቱም ዐሥር ዐሥር ክንድና ስምንት ስምንት ክንድ በሆኑ በከበሩ በታላላቅ ድንጋዮች ተሠርቶ ነበር። በላዩም ልክ ሆኖ የተከረከመ ጥሩ ድንጋይና የዝግባ ሣንቃ ነበረ። በታላቁም አደባባይ ዙሪያ የነበረው ቅጥር እንደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ውስጠኛው አደባባይ ቅጥርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ወገን በተጠረበ ድንጋይ አንዱም ወገን በዝግባ ሳንቃ ተሠርቶ ነበር። ንጉሡም ሰሎሞን ልኮ ኪራምን ከጢሮስ አስመጣ። እርሱም ከንፍታሌም ወገን የነበረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፤ አባቱም የጢሮስ ሰው ናስ ሠራተኛ ነበረ፤ የናስንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥበብና በማስተዋል፥ በብልሃትም ተሞልቶ ነበር። ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን መጥቶ ሥራውን ሁሉ ሠራ። በቤቱ ውስጥ ላለው ወለል ሁለቱን የናስ አዕማድ ሠራ፤ የአንዱም ዓምድ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፤ የዙሪያውም መጠን ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዓምዱም ውፍረት አንድ ጋት ነበረ፤ ውስጠ ክፍትም ነበረ። ሁለተኛውም ዓምድ እንዲሁ ነበረ። በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ እንዲቀመጡ ከፈሰሰ ናስ ሁለት ጕልላትን ሠራ፤ የአንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ፥ የሁለተኛውም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ። በአዕማዱም ራስ ላይ የነበሩትን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መርበብ ሥራ አደረገ፤ አንዱም መርበብ ለአንዱ ጕልላት፥ ሁለተኛውም መርበብ ለሁለተኛው ጕልላት ነበረ። ሮማኖችንም ሠራ፤ በአንድ ጕልላት ዙሪያ በሁለት ተራ፥ በአንድም መርበብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እንዲሁም ለሁለተኛው ጕልላት አደረገ። በወለሉም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አራት ክንድ አድርጎ ቀረጸ። በሁለቱም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ በመርበቡ ሥራ አጠገብ ሮማኖቹን አደረገ። ሮማኖቹም በአንዱ ወገን ሁለት መቶ ነበሩ። የሁለተኛውም ጕልላት እንዲሁ ነበረ። አዕማዱንም በመቅደሱ ወለል አጠገብ አቆማቸው፤ የቀኙንም ዓምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግራውንም ዓምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው። በአዕማዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አደረገ። እንዲሁም የአዕማዱ ሥራ ተጨረሰ። ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኩሬ ሠራ። ከከንፈሩም በታች ለአንድ ክንድ ዐሥር፥ ለአንድ ክንድም ዐሥር ጕብጕቦች አዞረበት፤ ከንፈሮቹም እንደ ጽዋ ከንፈር ነበሩ። በውስጡም አበቦች በቅለውበት ነበር። ውፍረቱም ስንዝር ነበር። ኩሬውም በዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። ኩሬውም በላያቸው ነበረ፤ የሁሉም ጀርባቸው በስተውስጥ ነበረ። ውፍረቱም አንድ ጋት ነበረ። ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር ተሠርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበባዎች ሆኖ ተከርክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር። ዐሥርም የናስ መቀመጫዎችን ሠራ፤ የአንዱም መቀመጫ ርዝመት አራት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ ነበረ። መቀመጫዎችንም እንዲሁ ሠራ፤ እርስ በርሳቸውም አያይዞ ሰንበር ባለው ክፈፍ ሠራቸው። በክፈፎቹም መካከል በነበሩ ሰንበሮች ላይ አንበሳዎችና በሬዎች፥ ኪሩቤልም ነበሩ፤ እንዲሁም በክፈፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአንበሳዎቹና ከበሬዎቹ በታች ሻኩራ የሚመስል ተንጠልጥሎ ነበር። በየመቀመጫዎቹም ሁሉ አራት የናስ መንኰራኵሮች ነበሩባቸው፤ መንኰራኵሮቹም የሚዞሩበትን የናስ ወስከምት ሠራ፤ ከመታጠቢያውም ሰን በታች በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት በምስል የፈሰሱ እግሮች ነበሩ። በክፈፉም ውስጥ የነበረ አንገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አንገቱም ድቡልቡል ነበረ፤ ቁመቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአንገቱም ላይ ቅርጽ ነበረበት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕዘን ነበረ እንጂ ድቡልቡል አልነበረም። አራቱም መንኰራኵሮች ከሰንበሮቹ በታች ነበሩ፤ የመንኰራኵሮቹም ወስከምት በመቀመጫው ውስጥ ነበረ፤ የመንኰራኵሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ። የመንኰራኵሮቹም ሥራ እንደ ሰረገላ መንኰራኵር ሥራ ነበረ፤ ወስከምቶቹና የመንኰራኵሮቹ ክፈፍ፥ ቅትርቶቹም፥ ወስከምቱ የሚገባበት ቧምቧ ሁሉ በምስል የፈሰሰ ነበር። በየአንዳንዱም መቀመጫ በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት ደገፋዎች ነበሩ፤ ደገፋዎቹም ከመቀመጫው ጋር ተጋጥመው ነበር። በመቀመጫውም ራስ ላይ ስንዝር የሚሆን ድቡልቡል ነገር ነበረ፤ በመቀመጫውም ላይ የነበሩ መያዣዎችና ሰንበሮች ከእርሱ ጋር ይጋጠሙ ነበረ፤ ከላይም ክፍት ነበረ፤ በክፈፎቻቸውም ኪሩቤልና አንበሶች የዘንባባ ዛፎችም ነበሩ፤ እያንዳንዱም ፊት ለፊት በስተውስጥና በዙሪያው ተያይዞ ነበር። እንዲሁም ዐሥሩን መቀመጫዎች ሠራ፤ ሁሉም በመጠን፥ በንድፍም ትክክሎች ነበሩ። ዐሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በዐሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር። አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኩሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ ፊት ለፊት በስተምሥራቅ አኖረው።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 7 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 7:1-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos