1 ቆሮንቶስ 9:14-17
1 ቆሮንቶስ 9:14-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችንም እንዲሁ ወንጌልን ለሚያስተምሩ ሰዎች ለሕይወታቸው መተዳደሪያ በዚያው ወንጌልን በማስተማር ይሆን ዘንድ አዘዘ። እኔ ግን ይህንም ቢሆን አልፈቀድሁትም፤ ይህን የጻፍሁም ይህን እንዳገኝ ብዬ አይደለም፤ እኔ ግን ምስጋናዬ ከሚቀርብኝ ሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ባስተምርም መመስገን አይገባኝም፤ ታዝዤ አድርጌዋለሁና፤ ወንጌልን ባላስተምር ደግሞ ወዮልኝ። ይህንስ በፈቃዴ አድርጌው ብሆን ዋጋዬን ባገኘሁ ነበር፤ በግድ ከሆነ ግን በተሰጠኝ መጋቢነት አገለገልሁ።
1 ቆሮንቶስ 9:14-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዝዟል። እኔ ግን ከእነዚህ መብቶች በአንዱ እንኳ አልተጠቀምሁም፤ አሁንም ይህን የምጽፍላችሁ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ በሚል ተስፋ አይደለም፤ ማንም ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ። በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል።
1 ቆሮንቶስ 9:14-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ። ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል።
1 ቆሮንቶስ 9:14-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንዲሁም ደግሞ ወንጌልን የሚያስተምሩ ቀለባቸውን ከዚሁ ሥራቸው እንዲያገኙ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን በእነዚህ መብቶች በአንዱም አልተጠቀምኩም፤ ይህንንም የጻፍኩት ይህ መብቴ ሳይከበርልኝ ለምን ቀረ? በማለት አይደለም። ሰው ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ይልቅ ብሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ማስተማር ግዴታዬ ስለ ሆነ የምመካበት ነገር አይደለም፤ እንዲያውም ወንጌልን ሳላስተምር ብቀር ወዮልኝ! የወንጌልን ቃል ያለ ግዴታ በፈቃዴ ባበሥር የድካም ዋጋ ይኖረኛል፤ በግዴታ ባደርገው ግን በዐደራ የተሰጠኝን ኀላፊነት ፈጸምኩ እንጂ ሌላ ያደረግኹት ነገር አለ ማለት አይደለም።
1 ቆሮንቶስ 9:14-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚያበስሩ ከወንጌል ቀለባቸውን እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ በአንዱም ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ብሰብክ እንኳ ግዴታዬ ነውና የምመካበት የለኝም፤ ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ! ይህን በፈቃዴ ባደርገው ዋጋ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል።