1 ቆሮንቶስ 4:14-21
1 ቆሮንቶስ 4:14-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህን የምጽፍላችሁ እንደ ተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ብዬ አይደለም። ምንም እንኳ በዐሥር ሺሕ የሚቈጠሩ ሞግዚቶች በክርስቶስ ቢኖሯችሁም፣ ብዙ አባቶች ግን የሏችሁም፤ በወንጌል አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ ወልጄአችኋለሁና። ስለዚህ እኔን እንድትመስሉ እለምናችኋለሁ። እንግዲህ በጌታ የተወደደውንና የታመነውን ልጄን ጢሞቴዎስን የላክሁላችሁ በዚህ ምክንያት ነው፤ እርሱም በየስፍራው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከማስተምረው ትምህርት ጋራ የሚስማማውን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን የሕይወት አካሄዴን ያሳስባችኋል። ከእናንተ አንዳንዶቹ ወደ እናንተ የማልመጣ መስሏቸው ታብየዋል፤ ይሁን እንጂ የጌታ ፈቃድ ቢሆን ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ ከዚያም እነዚህ ትዕቢተኞች የሚናገሩትን ብቻ ሳይሆን፣ ምን ኀይል እንዳላቸውም ማየት እሻለሁ። ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት የወሬ ጕዳይ ሳይሆን የኀይል ጕዳይ ነው። ለመሆኑ የምትፈልጉት የቱን ነው? በትር ይዤ ልምጣ ወይስ በፍቅርና በገርነት መንፈስ?
1 ቆሮንቶስ 4:14-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም የጻፍሁላችሁ ላሳፍራችሁ አይደለም፤ ልጆችና ወዳጆች እንደ መሆናችሁ ልመክራችሁና ላስተምራችሁ ነው እንጂ፤ እኔ ለሁላችሁ ቤዛችሁ ነኝ፤ እናንተ ግን አላፈራችሁኝም። በክርስቶስ ብዙ መምህራን ቢኖሩአችሁም አባቶቻችሁ ብዙዎች አይደሉም፤ እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርት ወልጄአችኋለሁና። ወንድሞቻችን ሆይ! እኔን እንድትመስሉ እማልዳችኋለሁ፤ ስለዚህም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዳስተማርሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሄድሁበትን መንገድ ይገልጥላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር የታመነና ልጄ ወዳጄ የሆነ ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ። እነሆ፥ ወደ እናንተ ስላልመጣሁ ከእናንተ ወገን የታበዩ ሰዎች አሉ። እንኪያስ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ፈጥኜ እመጣለሁ፤ ነገር ግን የትዕቢተኞችን ነገር አልሻም፤ ኀይላቸውን እሻለሁ እንጂ። የእግዚአብሔር መንግሥት በኀይል እንጂ በቃል አይደለምና። እንዴት ሆኜ ወደ እናንተ ልመጣ ትወዳላችሁ? በበትር ነውን? ወይስ በፍቅርና በቅንነት መንፈስ?
1 ቆሮንቶስ 4:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። ስለዚህ የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፥ እኔም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደማስተምር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚሆነውን መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል። አንዳንዱ ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤ ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፥ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?
1 ቆሮንቶስ 4:14-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኔ ይህን የምጽፍላችሁ እንደ ተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ አስቤ ነው እንጂ ላሳፍራችሁ ብዬ አይደለም። ምንም እንኳ በክርስቶስ ብዙ መሪዎች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ወልጄአችኋለሁ። ስለዚህ የእኔን ምሳሌነት እንድትከተሉ እለምናችኋለሁ። በዚህ ምክንያት የተወደደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፤ በየቦታውና በየአብያተ ክርስቲያኑ እንደማስተምረው እርሱ እኔ በክርስቶስ ያገኘሁትን የአዲስ ሕይወት መመሪያ ያሳስባችኋል። ነገር ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ እኔ እናንተን ለመጐብኘት የማልመጣ መስሎአቸው በትዕቢት ተሞልተዋል። ይሁን እንጂ የጌታ ፈቃድ ቢሆን በቅርብ ጊዜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ የእነዚህን ትዕቢተኞች ንግግራቸውን ብቻ ሳይሆን ኀይላቸውንም ማወቅ እፈልጋለሁ። የእግዚአብሔር መንግሥት የንግግር ጉዳይ ሳይሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው። የምትፈልጉት ምንድን ነው? የመቅጫ በትር ይዤ ወደ እናንተ እንድመጣ ትፈልጋላችሁን? ወይስ በፍቅርና በትሕትና መንፈስ እንድመጣ ትፈልጋላችሁ?
1 ቆሮንቶስ 4:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። በክርስቶስ አእላፍ መሪዎች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። እንግዲህ “እኔን የምትመስሉ ሁኑ፤” ብዬ እለምናችኋለሁ። በዚህ ምክንያት የተወደደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፤ በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ እንደማስተምረው በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነው መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል። አንዳንዶች ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤ ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። ምን ትፈልጋላችሁ? በትር ይዤ ወደ እናንተ እንድመጣ? ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ?