ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 4
4
ስለ ሐዋርያዊ አገልግሎት
1እኛ የክርስቶስ አገልጋዮችና የእግዚአብሔር የምሥጢሩ መጋቢዎች እንደ ሆን ሰው ስለ እኛ እንዲህ ያስብ። 2እንግዲህ በዚህ ከመጋቢዎች እያንዳንዱ ቸርና ታማኝ ሆኖ እንዲገኝ ይፈለጋል። 3ለእኔስ በእናንተ ዘንድ መመስገን ውርደት ነው፤ ጻድቅ ብትሉኝ፥ በመዋቲ ሰው ዘንድም ቸር ብላችሁ ብታከብሩኝ እኔ ለራሴ አልፈርድም።#ምዕ. 4 ቍ. 3 በግሪኩ “ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ቢፈረድብኝ ለእኔ ምንም አይደለም እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም” ይላል። 4የሚያጠራጥረኝና ትዝ የሚለኝ ነገር የለም፤ በዚህም ራሴን አላመጻድቅም፤ እግዚአብሔር ይመረምረኛልና። 5ጊዜው ሳይደርስ ዛሬ ለምን ትመረምራላቸሁ? በጨለማ ውስጥ የተሰወረውንም የሚያበራ፥ የልብን አሳብም የሚገልጥ ጌታችን ይመጣል፤ ያንጊዜ ሁሉም ዋጋውን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።
6ወንድሞቻችን ሆይ! እኔም፥ አጵሎስም ብንሆን መከራ የተቀበልነው ስለ እናንተ ነው፤ እናንተ እንድትማሩ፥ ከመጻሕፍት ቃልም ወጥታችሁ በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳትታበዩ ነው። 7ማን ይመረምርሃል?#ግሪኩ “አንተን ከሌላው ልዩ ያደረገህ ማን ነው” ይላል። የምትታበይስ በምንድን ነው? ከሌላ ያላገኘኸው አለህን? ያለህንም ከሌላ ካገኘህ እንዳላገኘ ለምን ትኮራለህ?
8እናንተ አሁን ጠግባችኋል፤ በልጽጋችኋልም፤ ያለእኛም ፈጽማችሁ ነግሣችኋል፤ እኛም ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ አግባብ በሆነ ነበር። 9እኔስ ለሞት ዝግጁዎች እንደ መሆናችን እኛን ሐዋርያቱን እግዚአብሔር የኋለኞች ያደረገን ይመስለኛል፤ እኛ ለሰዎችም፥ ለአለቆችም፥ ለዓለምም መዘባበቻ ሆነናልና። 10እኛስ ስለ ክርስቶስ ብለን አላዋቂዎች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጠቢባን ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ ክቡራን ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን። 11እኛ እስከዚች ቀን ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንሰደዳለን፤ ማረፊያም የለንም፤ እንደበደባለንም። 12#የሐዋ. 18፥3። በእጃችን ሥራ እያገለገልን እንደክማለን፤ ይረግሙናል፤ እኛ ግን እንመርቃቸዋለን፤ ያሳድዱናል፤ እኛ ግን እንጸልይላቸዋለን፤ እንታገሣቸዋለንም። 13ይሰድቡናል፥ እንማልዳቸዋለን፤ በዓለም እንደ ጊጤ ሆን፤ በሁሉም ዘንድ የተናቅን ሆን።
14ይህንም የጻፍሁላችሁ ላሳፍራችሁ አይደለም፤ ልጆችና ወዳጆች እንደ መሆናችሁ ልመክራችሁና ላስተምራችሁ ነው እንጂ፤ እኔ ለሁላችሁ ቤዛችሁ ነኝ፤ እናንተ ግን አላፈራችሁኝም።#“እኔ ለሁላችሁ ቤዛችሁ ነኝ እናንተ ግን አላፈራችሁኝም” የሚለው በግሪኩ የለም። 15በክርስቶስ ብዙ መምህራን ቢኖሩአችሁም አባቶቻችሁ ብዙዎች አይደሉም፤ እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርት ወልጄአችኋለሁና።
መምህራንን ስለ መምሰል
16 #
1ቆሮ. 11፥1፤ ፊል. 3፥17። ወንድሞቻችን ሆይ! እኔን እንድትመስሉ እማልዳችኋለሁ፤ 17ስለዚህም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዳስተማርሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሄድሁበትን መንገድ ይገልጥላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር የታመነና ልጄ ወዳጄ የሆነ ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ። 18እነሆ፥ ወደ እናንተ ስላልመጣሁ ከእናንተ ወገን የታበዩ ሰዎች አሉ። 19እንኪያስ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ፈጥኜ እመጣለሁ፤ ነገር ግን የትዕቢተኞችን ነገር አልሻም፤ ኀይላቸውን እሻለሁ እንጂ። 20የእግዚአብሔር መንግሥት በኀይል እንጂ በቃል አይደለምና። 21እንዴት ሆኜ ወደ እናንተ ልመጣ ትወዳላችሁ? በበትር ነውን? ወይስ በፍቅርና በቅንነት መንፈስ?
Currently Selected:
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ