1 ቆሮንቶስ 3:5-15

1 ቆሮንቶስ 3:5-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እን​ግ​ዲህ ጳው​ሎስ ምን​ድን ነው? አጵ​ሎ​ስስ ምን​ድን ነው? እነ​ር​ሱስ በቃ​ላ​ቸው የአ​መ​ና​ችሁ አገ​ል​ጋ​ዮች ናቸው፤ ለእ​ያ​ን​ዳ​ን​ዱም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ሰጠው ነው። እኔ ተከ​ልሁ፤ አጵ​ሎ​ስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አሳ​ደገ። አሁ​ንም የሚ​ተ​ክ​ልም ቢሆን፥ የሚ​ያ​ጠ​ጣም ቢሆን የሚ​ጠ​ቅ​መው ነገር የለም፤ የሚ​ያ​ሳ​ድግ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነው እንጂ። የሚ​ተ​ክ​ልም፥ የሚ​ያ​ጠ​ጣም አንድ ናቸው፤ ሁሉም እንደ ድካ​ማ​ቸው ዋጋ​ቸ​ውን ይቀ​በ​ላሉ። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሥራ እን​ተ​ባ​በ​ራ​ለ​ንና፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አገ​ል​ጋ​ዮች ነንና፤ እና​ን​ተም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሕንፃ ናችሁ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ሰጠኝ ጸጋ መጠን እንደ ብልህ የጠ​ራ​ቢ​ዎች አለቃ ሆኜ እኔ መሠ​ረት ጣልሁ፤ ሌላ​ውም በእ​ርሱ ላይ ያን​ጻል፤ እያ​ን​ዳ​ንዱ ግን በእ​ርሱ ላይ እን​ዴት እን​ደ​ሚ​ያ​ንጽ ይጠ​ን​ቀቅ። ነገር ግን ከተ​መ​ሠ​ረ​ተው በቀር ሌላ መሠ​ረት ሊመ​ሠ​ርት የሚ​ችል የለም፤ መሠ​ረ​ቱም ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ነው። በዚህ መሠ​ረት ላይ በወ​ር​ቅና በብር፥ በከ​በረ ድን​ጋ​ይና በእ​ን​ጨት፥ በሣ​ርና በአ​ገዳ የሚ​ያ​ንጽ ቢኖ​ርም፥ የእ​ያ​ን​ዳ​ንዱ ሥራ ይገ​ለ​ጻል፤ እሳ​ትም በፈ​ተ​ነው ጊዜ ቀኑ ይገ​ል​ጠ​ዋል፤ የእ​ያ​ን​ዳ​ን​ዱ​ንም ሥራ እሳት ይፈ​ት​ነ​ዋል። ሥራው ጸንቶ የተ​ገ​ኘ​ለት ሰው ዋጋ​ውን የሚ​ቀ​በል እርሱ ነው። ሥራው የተ​ቃ​ጠ​ለ​በት ግን ዋጋ​ውን ያጣል፤ እር​ሱም ከእ​ሳት እን​ደ​ሚ​ድን ሰው ይድ​ናል።

1 ቆሮንቶስ 3:5-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው በሰጣቸው መጠን የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም ወደ እምነት የመጣችሁት በእነርሱ አማካይነት ነው። እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም። የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል። እኛ የእግዚአብሔር የሆንን ዐብሮ ሠራተኞች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ፣ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ። ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መጠን፣ እንደ አንድ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልሁ፤ ሌላውም በላዩ ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ከተመሠረተው መሠረት በቀር ሌላ መሠረት መጣል የሚችል ማንም የለም፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ወይም በብር፣ በከበረ ድንጋይ ወይም በዕንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ ቢያንጽ፣ ሥራው እንዴት እንደ ሆነ ይታያል፤ ምክንያቱም ያ ቀን ወደ ብርሃን ያመጣዋል። በእሳት ስለሚገለጥ እሳቱ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ምንነት ይፈትናል። ማንም የገነባው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤ ሥራው የተቃጠለበት ግን ሽልማት ይቀርበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ ይሁን እንጂ የሚድነው በእሳት ውስጥ በጭንቅ እንደሚያልፍ ሆኖ ነው።

1 ቆሮንቶስ 3:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል።

1 ቆሮንቶስ 3:5-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? እነርሱ እናንተ እንድታምኑ ያደረጉአችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ እያንዳንዳቸው የሚያገለግሉትም ጌታ ለያንዳንዳቸው በመደበላቸው ሥራ ነው፤ እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ ለሥራው ዋና የሆነው ተክሉን ያሳደገው እግዚአብሔር ነው እንጂ የተከለም ሆነ ውሃ ያጠጣ ምንም አይደለም። የተከለም ሆነ ውሃ ያጠጣ እኩል ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላል። እኛ ለእግዚአብሔር አብረን የምንሠራ አገልጋዮች ነን፤ እናንተም የእግዚአብሔር እርሻና የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ። እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መጠን እንደ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልኩ፤ ሌላውም እኔ በጣልኩት መሠረት ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በዚያ ላይ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት። አንድ ጊዜ ከተመሠረተው መሠረት በቀር ማንም ሌላ መሠረት መጣል አይችልም፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፥ ወይም በብር በከበረ ድንጋይ፥ ወይም በእንጨት፥ በሣር ወይም በገለባ የሚገነባ ቢኖር የእያንዳንዱ ሰው ሥራ የሚገለጥበት የፍርድ ቀን ይመጣል፤ በዚያን ቀን የእያንዳንዱ ሰው ሥራ ምን ዐይነት እንደ ሆነ በእሳት ተፈትኖ ይገለጣል። አንድ ግንበኛ በመሠረቱ ላይ የሠራው ሥራ በእሳት ተፈትኖ ሳይጐዳ ጸንቶ ከቆመ ግንበኛው ዋጋውን ያገኛል። ሥራው በእሳት ተቃጥሎ የተደመሰሰበት ግንበኛ ግን ዋጋው ይቀርበታል፤ ይሁን እንጂ እርሱ ራሱ፥ በእሳት ውስጥ አልፎ ሳይቃጠል እንደሚቀር ሰው ይድናል።

1 ቆሮንቶስ 3:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አጵሎስ እንግዲህ ምንድነው? ጳውሎስስ ምንድነው? በእነርሱ በኩል ያመናችሁ፥ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደሰጣቸው፥ አገልጋዮች ናቸው፤ እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ሆነ ወይም የሚያጠጣ ቢሆን ምንም አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ክፍያ ይቀበላል። ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና፤ የእግዚአብሔር እርሻ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ። የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልኩ፤ ሌላውም በዚያ ላይ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በዚያ ላይ እንዴት እንደሚያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም፤ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፥ በብር፥ በከበሩ ድንጋዮች፥ በእንጨት፥ በሣር፥ በገለባ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ፥ ያ ቀን በገሃድ ያሳያልና፤ የእያንዳንዱም ሥራ ምን መሆኑን እሳቱ ራሱ ይፈትነዋል። ማንም በዚያ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ ሆኖም ግን በእሳት አልፎ ይሆናል።