1 ቆሮንቶስ 2:13-16
1 ቆሮንቶስ 2:13-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህም ትምህርታችን ከሰው የተገኘ ትምህርት አይደለም፤ የአነጋገር ጥበብም አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ የገለጸው ትምህርት ነው እንጂ፤ መንፈሳዊ ጥበብም ከመንፈስ ቅዱስ የሚሆነውን መርምረው ለሚያውቁ ለመንፈሳውያን ነው። ለሥጋዊ ሰው ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ይመስለዋልና፥ አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቅ አይችልም። መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፤ እርሱን ግን የሚመረምረው የለም። የእግዚአብሔርን አሳብ ማን ያውቃል? መካሩስ ማን ነው? እኛ ግን ክርስቶስ የሚገልጠው ዕውቀት አለን።
1 ቆሮንቶስ 2:13-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው። መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለርሱ ሞኝነት ነው፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ፣ ሊረዳው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። “ያስተምረው ዘንድ፣ የጌታን ልብ ያወቀ ማን ነው?” እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።
1 ቆሮንቶስ 2:13-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።
1 ቆሮንቶስ 2:13-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ እኛ መንፈሳዊውን ነገር ለመንፈሳውያን ሰዎች የምናስተምረው ከሰው በሚገኘው ጥበብ ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈስ በሚገኘው ጥበብ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ የሌለው ሥጋዊ ሰው ግን ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚሰጠውን ስጦታ መቀበል አይችልም፤ የስጦታው ታላቅነት የሚመረመረው በእግዚአብሔር መንፈስ አማካይነት ስለ ሆነ ሊያስተውለው አይችልም፤ እንዲያውም ይህ ለእርሱ ሞኝነት መስሎ ይታየዋል። የእግዚአብሔር መንፈስ ያለው ግን ሁሉን ነገር መመርመር ይችላል፤ እርሱ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። ይህም፦ “የጌታን ሐሳብ ማን ሊያውቀው ይችላል? ሊመክረውስ የሚችል ማን ነው?” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።
1 ቆሮንቶስ 2:13-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህን ደግሞ፥ መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን፥ መንፈስ በሚያስተምረን ቃል እንናገራለን እንጂ ከሰው ጥበብ በሚገኝ ቃል አይደለም። ፍጥረታዊ ሰው ግን የእግዚአብሔርን መንፈስ ነገር አይቀበለውም፤ ይህ ለእርሱ ሞኝነት ነው፥ ምክንያቱም በመንፈስ የሚመረመር ነውና፥ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ይመረምራል፤ እሱ ግን በማንም አይመረመርም። ሊመክረውስ የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልቦና አለን።