1 ቆሮንቶስ 15:54-58
1 ቆሮንቶስ 15:54-58 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን በለበሰ ጊዜ፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በለበሰ ጊዜ፤ “ሞት በመሸነፍ ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ያንጊዜ ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፥ እንግዲህ መውጊያህ ወዴት አለ? መቃብር ሆይ፥ አሸናፊነትህ ወዴት አለ?” የሞት መውጊያ ኀጢአት ናት፥ የኀጢአትም ኀይልዋ ኦሪት ናት። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል መንሣትን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሁንም የተወደዳችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ የጸናችሁና የማትናወጡ ሁኑ፤ ዘወትር በጎ ምግባርን አብዝታችሁ ለእግዚአብሔር አበርክቱ፤ ስለ ጌታችን መድከማችሁ ለከንቱ እንዳይደለ ታውቃላችሁና።
1 ቆሮንቶስ 15:54-58 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ “ሞት በድል ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። እንዲሁም፣ “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?” የሞት መንደፊያ ኀጢአት ነው፤ የኀጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
1 ቆሮንቶስ 15:54-58 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።
1 ቆሮንቶስ 15:54-58 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል። እንዲሁም፥ “ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል። የሞት መንደፊያ ኀይል ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ፤ ለጌታ ሥራ የምትደክሙት በከንቱ አለመሆኑን ዐውቃችሁ፥ ሳታቋርጡ ዘወትር የጌታን ሥራ ለመሥራት ትጉ።
1 ቆሮንቶስ 15:54-58 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፥ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መውጊያህስ የት አለ?”። የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ድካማችሁ በጌታ ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር በማወቅ፥ ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ።