1 ቆሮንቶስ 15:50-55
1 ቆሮንቶስ 15:50-55 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን ሆይ፥ ይህን እንነግራችኋለን፦ ሥጋዊና ደማዊ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፥ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢርን እነግራችኋለሁ፥ ሁላችን የምንሞት አይደለም። ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን እንደ ዐይን ጥቅሻ በአንድ ጊዜ እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋል፤ ሙታንም የማይፈርሱ ሁነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን፥ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ይለብስ ዘንድ አለውና። ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን በለበሰ ጊዜ፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በለበሰ ጊዜ፤ “ሞት በመሸነፍ ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ያንጊዜ ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፥ እንግዲህ መውጊያህ ወዴት አለ? መቃብር ሆይ፥ አሸናፊነትህ ወዴት አለ?”
1 ቆሮንቶስ 15:50-55 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፤ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ድንገት በቅጽበተ ዐይን ነው። መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ “ሞት በድል ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። እንዲሁም፣ “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?”
1 ቆሮንቶስ 15:50-55 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?
1 ቆሮንቶስ 15:50-55 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤ ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት። ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል። እንዲሁም፥ “ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል።
1 ቆሮንቶስ 15:50-55 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ! ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፥ ድንገት፥ በቅጽበተ ዐይን፥ መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፥ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መውጊያህስ የት አለ?”።