የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ቆሮንቶስ 15:1-58

1 ቆሮንቶስ 15:1-58 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን፣ ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወድዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቈጠር ለእኔ ደግሞ ታየ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፣ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ እንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው። ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቷል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኗልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ “ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሏልና፤ ነገር ግን፣ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፣ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል። ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። በኤፌሶን ከአራዊት ጋር የታገልሁት ለሰው አስተያየት ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ፤” እንደሚሉት መሆናችን ነው። አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኀጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው። ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንስሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። እንዲሁም ሰማያውያን አካላት አሉ፤ ምድራውያን አካላት አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው። የፀሓይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል። የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፣ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፏል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን ፍጥረታዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደ ለበስን፣ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፤ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ድንገት በቅጽበተ ዐይን ነው። መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ “ሞት በድል ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። እንዲሁም፣ “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?” የሞት መንደፊያ ኀጢአት ነው፤ የኀጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።

1 ቆሮንቶስ 15:1-58 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ ያስ​ተ​ማ​ር​ኋ​ች​ሁ​ንና የተ​ቀ​በ​ላ​ች​ሁ​ትን ያላ​ች​ሁ​በ​ትን፥ በእ​ር​ሱም የም​ት​ድ​ኑ​በ​ትን ወን​ጌል አሳ​ስ​ባ​ች​ኋ​ለሁ። ያስ​ተ​ማ​ር​ኋ​ች​ሁን ታስቡ እንደ ሆነ በቃሌ አስ​ተ​ም​ሬ​አ​ች​ኋ​ለሁ፤ ያለ​ዚያ ግን ማመ​ና​ችሁ ከንቱ ነው። እኔ የተ​ማ​ር​ሁ​ትን አስ​ቀ​ድሜ መጽ​ሐፍ እን​ደ​ሚል እን​ዲህ ብዬ አስ​ተ​ማ​ር​ኋ​ችሁ፥ “ክር​ስ​ቶስ ስለ ኀጢ​አ​ታ​ችን ሞተ። ተቀ​በረ፤ እንደ ተጻ​ፈም በሦ​ስ​ተ​ኛው ቀን ተነሣ።” ለጴ​ጥ​ሮስ ታየው፤ ከዚ​ህም በኋላ ለዐ​ሥራ አንዱ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ታያ​ቸው። ከዚ​ህም በኋላ ከአ​ም​ስት መቶ ለሚ​በዙ ወን​ድ​ሞች በአ​ንድ ጊዜ ታያ​ቸው፤ ከእ​ነ​ርሱ ብዙ​ዎቹ እስከ ዛሬ አሉ፤ አን​ዳ​ን​ዶቹ ግን አን​ቀ​ላ​ፍ​ተ​ዋል። ከዚ​ህም በኋላ ለያ​ዕ​ቆብ ታየው፤ ኋላም ለሐ​ዋ​ር​ያት ሁሉ፤ ከሁ​ሉም በኋላ ጭን​ጋፍ ለም​መ​ስል ለእኔ ታየኝ። ከሐ​ዋ​ር​ያት ሁሉ እኔ አን​ሣ​ለ​ሁና፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቤተ ክር​ስ​ቲ​ያን ስለ አሳ​ደ​ድሁ ሐዋ​ርያ ተብዬ ልጠራ የማ​ይ​ገ​ባኝ፥ ነገር ግን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጸጋ አሁን እኔ ባለ​ሁ​በት አለሁ፤ ለእ​ኔም የሰ​ጠኝ ጸጋው ለከ​ንቱ የሆ​ነ​ብኝ አይ​ደ​ለም፤ እኔም ከሁሉ ይልቅ ደከ​ምሁ፤ ነገር ግን በእኔ ላይ ያደ​ረው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጸጋ አጸ​ናኝ እንጂ እኔ አይ​ደ​ለ​ሁም። አሁ​ንም እኔም ብሆን፥ እነ​ር​ሱም ቢሆኑ እን​ዲህ እና​ስ​ተ​ም​ራ​ለን፤ እና​ን​ተም እን​ዲሁ አም​ና​ች​ኋል። ክር​ስ​ቶስ ከሙ​ታን ተለ​ይቶ ተነ​ሥ​ቶ​አል ብለን ለሌ​ላው የም​ና​ስ​ተ​ምር ከሆነ፥ እን​ግ​ዲህ ከመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ ሙታን አይ​ነ​ሡም የሚሉ እን​ዴት ይኖ​ራሉ? ሙታን የማ​ይ​ነሡ ከሆነ ክር​ስ​ቶ​ስም ከሙ​ታን ተለ​ይቶ አል​ተ​ነ​ሣማ፤ ክር​ስ​ቶ​ስም ከሙ​ታን ካል​ተ​ነሣ እን​ግ​ዲ​ያስ ትም​ህ​ር​ታ​ችን ከንቱ ነው፤ የእ​ና​ን​ተም እም​ነ​ታ​ችሁ ከንቱ ነው። እኛም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ላይ የሐ​ሰት ምስ​ክ​ሮች ሆነ​ናል፤ ክር​ስ​ቶ​ስን አስ​ነ​ሣው ብለ​ና​ልና፥ እን​ግ​ዲያ ሳያ​ስ​ነ​ሣው ነውን?። ሙታን የማ​ይ​ነሡ ከሆነ ክር​ስ​ቶ​ስም ከሙ​ታን አል​ተ​ነ​ሣማ። ክር​ስ​ቶ​ስም ከሙ​ታን ካል​ተ​ነሣ ማመ​ና​ችሁ ከንቱ ነው፤ ገናም በኀ​ጢ​አ​ታ​ችሁ አላ​ችሁ። እን​ግ​ዲ​ያስ በክ​ር​ስ​ቶስ አም​ነው የሞቱ ጠፍ​ተ​ዋላ። በዚህ ዓለም ሕይ​ወት ብቻ ክር​ስ​ቶ​ስን ተስፋ ከአ​ደ​ረ​ግ​ነው ከሰው ሁሉ ይልቅ ጉዳ​ተ​ኞች ነን። አሁ​ንም ክር​ስ​ቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስ​ቀ​ድሞ ተነ​ሥ​ቶ​አል። በመ​ጀ​መ​ሪ​ያው ሰው ሞት መጥ​ቶ​አ​ልና፤ በሁ​ለ​ተ​ኛው ሰው ትን​ሣኤ ሙታን ሆነ። ሁሉ በአ​ዳም እን​ደ​ሚ​ሞት እን​ዲሁ በክ​ር​ስ​ቶስ ሁሉ ሕያ​ዋን ይሆ​ናሉ። ነገር ግን ሰው ሁሉ በየ​ሥ​ር​ዐቱ ይነ​ሣል፤ በመ​ጀ​መ​ሪያ ከሙ​ታን የተ​ነሣ ክር​ስ​ቶስ ነው፤ ከዚያ በኋላ በክ​ር​ስ​ቶስ ያመኑ እርሱ በሚ​መ​ጣ​በት ጊዜ ይነ​ሣሉ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አብ መን​ግ​ሥ​ቱን እጅ ባደ​ረገ ጊዜ፥ ገዥም ሁሉ፥ ንጉ​ሥም ሁሉ፥ ኀይ​ልም ሁሉ በተ​ሻረ ጊዜ፥ ያን​ጊዜ ፍጻሜ ይሆ​ናል። ጠላ​ቶቹ ሁሉ ከእ​ግሩ በታች እስ​ኪ​ወ​ድቁ ድረስ ይነ​ግሥ ዘንድ አለ​ውና። ከዚያ በኋላ የመ​ጨ​ረ​ሻው ጠላት ይሻ​ራል፤ ይኸ​ውም ሞት ነው። ሁሉን ከእ​ግሩ በታች አስ​ገ​ዝ​ቶ​ለ​ታ​ልና፥ “ሁሉ ይገ​ዛ​ለት” ባለ ጊዜ ግን ሁሉን ከሚ​ያ​ስ​ገ​ዛ​ለት በቀር እንደ ሆነ የታ​ወቀ ነው። ሁሉም በተ​ገ​ዛ​ለት ጊዜ ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሁሉ ቦታ በሁሉ ይሆን ዘንድ፥ ያን ዕለት ወል​ድም ሁሉን ላስ​ገ​ዛ​ለት ይገ​ዛል። ያለ​ዚ​ያማ ለምን ያጠ​ም​ቃሉ? ሙታን እን​ዲ​ነሡ አይ​ደ​ለ​ምን? ሙታን የማ​ይ​ነሡ ከሆ​ነስ ለምን ያጠ​ም​ቃሉ? እን​ግ​ዲህ እኛስ ሁል​ጊዜ መከ​ራን ስለ​ምን እን​ቀ​በ​ላ​ለን? ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ በሆ​ነ​ውና በእ​ና​ንተ ላይ ባለኝ ትም​ክ​ህት ሁል​ጊዜ እገ​ደ​ላ​ለሁ። በውኑ በኤ​ፌ​ሶን ከአ​ውሬ ጋር የታ​ገ​ልሁ ለሰው ብዬ ነውን? ምንስ ይጠ​ቅ​መ​ኛል? ሙታን የማ​ይ​ነሡ ከሆነ እን​ግ​ዲህ እን​ብላ እን​ጠጣ፥ ነገም እን​ሞ​ታ​ለን። ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን አያ​ስ​ቱ​አ​ችሁ፤ ክፉ ነገር መል​ካም ጠባ​ይን ያበ​ላ​ሻ​ልና። ለጽ​ድቅ ትጉ፤ አት​ሳቱ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የማ​ያ​ው​ቁት ሰዎች አሉና፤ ነገር ግን እን​ድ​ታ​ፍሩ ይህን እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ሙታን እን​ዴት ይነ​ሣሉ? የሚ​ነ​ሡስ በምን አካ​ላ​ቸው ነው? የሚል አለ። አንተ ሰነፍ! አንተ የም​ት​ዘ​ራው እን​ኳን ካል​ፈ​ረሰ አይ​በ​ቅ​ልም። የም​ት​ዘ​ራ​ውም የስ​ንዴ ቢሆን፥ የሌ​ላም ቢሆን የም​ት​ዘ​ራት ቅን​ጣት ብቻ ናት እንጂ ይህ ኋላ የሚ​ገ​ኘው አገ​ዳው አይ​ደ​ለም። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን እንደ ወደደ አገ​ዳን ይሰ​ጠ​ዋል፤ ለእ​ያ​ን​ዳ​ንዱ ዘርም አገ​ዳው እየ​ራሱ ነው። የፍ​ጥ​ረቱ ሁሉ አካል አንድ አይ​ደ​ለ​ምና፤ የሰው አካል ሌላ ነው፤ የእ​ን​ስ​ሳም አካል ሌላ ነው፤ የወፍ አካ​ልም ሌላ ነው፤ የዓሣ አካ​ልም ሌላ ነው። ሰማ​ያዊ አካል አለ፤ ምድ​ራዊ አካ​ልም አለ፤ ነገር ግን በሰ​ማይ ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው፤ በም​ድ​ርም ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው። የፀ​ሐይ ክብሩ ሌላ ነው፤ የጨ​ረ​ቃም ክብሩ ሌላ ነው፤ የከ​ዋ​ክ​ብ​ትም ክብ​ራ​ቸው ሌላ ነው፤ ኮከብ ከኮ​ከብ በክ​ብር ይበ​ል​ጣ​ልና። የሙ​ታን ትን​ሣ​ኤ​ያ​ቸው እን​ዲሁ ነው፥ በሚ​ፈ​ርስ አካል ይዘ​ራል፤ በማ​ይ​ፈ​ርስ አካል ይነ​ሣል። በው​ር​ደት ይዘ​ራል፤ በክ​ብር ይነ​ሣል፤ በድ​ካም ይዘ​ራል፤ በኀ​ይል ይነ​ሣል። ሥጋዊ አካል ይዘ​ራል፤ መን​ፈ​ሳዊ አካል ይነ​ሣል፤ ሥጋዊ አካል አለና መን​ፈ​ሳዊ አካ​ልም ደግሞ አለ። መጽ​ሐፍ እን​ዲሁ ብሎ​አ​ልና የመ​ጀ​መ​ሪ​ያው ሰው አዳም በነ​ፍስ ሕያው ሆኖ ተፈ​ጠረ፤ ሁለ​ተ​ኛው አዳም ግን ሕይ​ወ​ትን የሚ​ሰጥ መን​ፈስ ነው። ነገር ግን አስ​ቀ​ድሞ ሥጋ​ዊው፥ ቀጥ​ሎም መን​ፈ​ሳ​ዊው ነው እንጂ፥ መን​ፈ​ሳ​ዊው መጀ​መ​ሪ​ያው አይ​ደ​ለም። መጀ​መ​ሪ​ያው ሰው ከመ​ሬት የተ​ገኘ መሬ​ታዊ ነው፤ ሁለ​ተ​ኛው ሰው ከሰ​ማይ የወ​ረደ ሰማ​ያዊ ነው። መሬ​ታ​ው​ያኑ እን​ደ​ዚያ እንደ መሬ​ታ​ዊው ናቸው፤ ሰማ​ያ​ው​ያ​ኑም እን​ደ​ዚያ እንደ ሰማ​ያ​ዊው ናቸው። የመ​ሬ​ታ​ዊ​ውን መልክ እንደ ለበ​ስን እን​ዲሁ የሰ​ማ​ያ​ዊ​ውን መልክ ደግሞ እን​ለ​ብ​ሳ​ለን። ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ ይህን እን​ነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለን፦ ሥጋ​ዊና ደማዊ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ግ​ሥት አይ​ወ​ር​ስም፥ የሚ​ፈ​ር​ሰው የማ​ይ​ፈ​ር​ሰ​ውን አይ​ወ​ር​ስም። እነሆ፥ አንድ ምሥ​ጢ​ርን እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ፥ ሁላ​ችን የም​ን​ሞት አይ​ደ​ለም። ነገር ግን የኋ​ለ​ኛው መለ​ከት ሲነፋ ሁላ​ችን እንደ ዐይን ጥቅሻ በአ​ንድ ጊዜ እን​ለ​ወ​ጣ​ለን፤ መለ​ከት ይነ​ፋል፤ ሙታ​ንም የማ​ይ​ፈ​ርሱ ሁነው ይነ​ሣሉ፤ እኛም እን​ለ​ወ​ጣ​ለን። ይህ የሚ​ፈ​ር​ሰው የማ​ይ​ፈ​ር​ሰ​ውን፥ ይህም የሚ​ሞ​ተው የማ​ይ​ሞ​ተ​ውን ይለ​ብስ ዘንድ አለ​ውና። ይህ የሚ​ፈ​ር​ሰው የማ​ይ​ፈ​ር​ሰ​ውን በለ​በሰ ጊዜ፥ የሚ​ሞ​ተ​ውም የማ​ይ​ሞ​ተ​ውን በለ​በሰ ጊዜ፤ “ሞት በመ​ሸ​ነፍ ተዋጠ” ተብሎ የተ​ጻ​ፈው ያን​ጊዜ ይፈ​ጸ​ማል። “ሞት ሆይ፥ እን​ግ​ዲህ መው​ጊ​ያህ ወዴት አለ? መቃ​ብር ሆይ፥ አሸ​ና​ፊ​ነ​ትህ ወዴት አለ?” የሞት መው​ጊያ ኀጢ​አት ናት፥ የኀ​ጢ​አ​ትም ኀይ​ልዋ ኦሪት ናት። በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ድል መን​ሣ​ትን ለሰ​ጠን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምስ​ጋና ይሁን። አሁ​ንም የተ​ወ​ደ​ዳ​ችሁ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ የጸ​ና​ች​ሁና የማ​ት​ና​ወጡ ሁኑ፤ ዘወ​ትር በጎ ምግ​ባ​ርን አብ​ዝ​ታ​ችሁ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አበ​ር​ክቱ፤ ስለ ጌታ​ችን መድ​ከ​ማ​ችሁ ለከ​ንቱ እን​ዳ​ይ​ደለ ታው​ቃ​ላ​ች​ሁና።

1 ቆሮንቶስ 15:1-58 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፦ መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ። ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ፦ ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ደግሞም፦ ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፦ ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል። እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው? በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ። እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። ነገር ግን ሰው፦ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው። ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው። የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና። የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።

1 ቆሮንቶስ 15:1-58 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አሁን ደግሞ ወንድሞች ሆይ! ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ፤ ይህም የወንጌል ቃል እናንተ የተቀበላችሁትና ጸንታችሁ የቆማችሁበት ነው። እኔ ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ በእርሱ ትድናላችሁ፤ አለበለዚያ ግን ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልኩትን በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፍኩላችሁ፤ ያስተላለፍኩላችሁም ነገር በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈው ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ የሚል ነው። እርሱ ለጴጥሮስ ታየ፤ ኋላም ለዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ታየ፤ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ተከታዮቹም በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ ከእነርሱ አብዛኞቹ እስከ አሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን ሞተዋል። ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ታየ፤ ለሐዋርያትም ሁሉ ታያቸው። በመጨረሻም እንደ ጭንጋፍ ለሆንኩት ለእኔ ደግሞ ታየኝ። እኔ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያሳደድኩ ስለ ሆነ ከሐዋርያት ሁሉ ያነስኩና ሐዋርያም ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ። ነገር ግን እኔ አሁን የሆንኩትን ሆኜ የምገኘው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው፤ የተሰጠኝም ጸጋ ያለ ፍሬ አልቀረም፤ እንዲያውም ከሌሎቹ ይበልጥ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያደረገው ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። እንግዲህ እኔም ሆንኩ እነርሱ የምናስተምረው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው። ነገር ግን ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ የምናስተምር ከሆነ ከእናንተ አንዳንዶቹ ከሞት መነሣት የለም እንዴት ይላሉ? ከሞት መነሣት ከሌለ ክርስቶስ ከሞት አልተነሣም ማለት ነው፤ ክርስቶስ ከሞት ካልተነሣ የእኛም ትምህርት ሆነ የእናንተም እምነት ከንቱ መሆኑ ነው፤ ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በማስተማራችን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነናል ማለት ነው፤ እንግዲህ የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ እግዚአብሔር ክርስቶስንም ከሞት አላስነሣውም ማለት ነው። የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ ክርስቶስም ከሞት አልተነሣም ማለት ነው። ክርስቶስ ከሞት ያልተነሣ ከሆነ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ ገና በኃጢአታችሁ ውስጥ ትኖራላችሁ ማለት ነው፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱት ጠፍተዋል ማለት ነው፤ በክርስቶስ ተስፋ የምናደርገው ለዚህ ዓለም ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የሚታዘንልን መሆናችን ነው፤ ነገር ግን ክርስቶስ ለሞቱት ከሞት የመነሣት በኲር ሆኖ በእርግጥ ከሞት ተነሥቶአል። ሞት የመጣው በአንዱ ሰው በአዳም ምክንያት እንደ ሆነ ከሞት መነሣትም የሚመጣው በአንዱ ሰው በክርስቶስ ምክንያት ነው። በአዳም ምክንያት ሰው ሁሉ እንደሚሞት እንዲሁም በክርስቶስ ምክንያት ሰው ሁሉ ሕይወትን ያገኛል። ይህም የሚሆነው ለእያንዳንዱ በየተራው ነው፤ ክርስቶስ ከሞት የመነሣት የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፤ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት ከሞት ይነሣሉ። ቀጥሎም እርሱ ግዛትንና ሥልጣንን ኀይልንም ሁሉ አጥፍቶ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ በሚያስረክብበት ጊዜ የዓለም ፍጻሜ ይሆናል። እግዚአብሔር ጠላቶቹን ሁሉ በሥልጣኑ ሥር እስኪያደርግለት ድረስ ክርስቶስ መንገሥ ይገባዋል። ተሸንፎ በመጨረሻ የሚደመሰሰው ጠላት ሞት ነው። “እግዚአብሔር ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር አድርጎለታል” የሚል ተጽፎአል፤ ነገር ግን “ሁሉ ነገር በሥልጣኑ ሥር ሆኖአል” ሲባል ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር ያደረገለትን እግዚአብሔር አብን አይጨምርም። ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥልጣን ሥር ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር አብ ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር በአደረገለት በእግዚአብሔር አብ ሥልጣን ሥር ይሆናል። እንግዲህ የሞቱ ሰዎች የማይነሡ ከሆነ ስለ ሞቱ ሰዎች የሚጠመቁ ሁሉ ትርፋቸው ምንድን ነው? የሞቱ ሰዎች ከቶ የማይነሡ ከሆነ ሰዎች በእነርሱ ምትክ ስለምን ይጠመቃሉ? እኛስ ብንሆን በየሰዓቱ ለአደጋ እየተጋለጥን የምንኖረው ለምንድን ነው? ወንድሞች ሆይ! እኔን በየቀኑ ሞት ያጋጥመኛል፤ ይህንንም የምነግራችሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት እርግጠኛ ስለ ሆነ ነው። እንደ ሰው አስተሳሰብ እኔ በኤፌሶን ከአራዊት ጋር መታገሌ ጥቅሜ ምንድን ነው? ሙታን ከሞት የማይነሡ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት ኑ እንብላ፤ እንጠጣ” እንደ ተባለው መሆኑ ነው። አትታለሉ፤ “መጥፎ ጓደኛ ጥሩውን ጠባይ ያበላሻል።” ወደ ልቡናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአትም አትሥሩ፤ በእናንተ መካከል አንዳንዶች እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉ። ይህንንም የምለው እንድታፍሩ ብዬ ነው። አንድ ሰው “የሞቱ ሰዎች የሚነሡት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሡ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዐይነት ነው?” ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፤ አንተ ሞኝ! የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም፤ አንተ ስትዘራም የስንዴ ዘር ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኋላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም። እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደ ፈለገ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ ዐይነት አይደለም፤ የሰው ሥጋም አንድ ዐይነት ነው፤ የእንስሳ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የወፎች ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። እንዲሁም ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊው አካል ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የምድራዊውም አካል ክብር ሌላ ዐይነት ነው። የፀሐይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ የከዋክብትም ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ የተለየ ክብር አለው። ከሞት የሚነሡ ሰዎች ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል፤ የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል፤ ደካማ ሆኖ የተዘራው ኀይለኛ ሆኖ ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል ሆኖ የተዘራው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይነሣል። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ፍጡር ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው ሥጋዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው አይደለም፤ መንፈሳዊው የመጣው ከሥጋዊው በኋላ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከመሬት ስለ ሆነ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው የመጣው ከሰማይ ነው። ከመሬት የሆኑት ከመሬት እንደተፈጠረው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑት ከሰማይ እንደመጣው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደምንመስል የሰማያዊውንም ሰው መልክ እንመስላለን። ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤ ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት። ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል። እንዲሁም፥ “ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል። የሞት መንደፊያ ኀይል ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ፤ ለጌታ ሥራ የምትደክሙት በከንቱ አለመሆኑን ዐውቃችሁ፥ ሳታቋርጡ ዘወትር የጌታን ሥራ ለመሥራት ትጉ።

1 ቆሮንቶስ 15:1-58 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞች ሆይ! አሁን የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፥ ያመናችሁት በከንቱ ካልሆነ በስተቀር፥ የምትድኑበትን ወንጌል ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ለኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላም ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ እስካሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ደግሞ ታየ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፥ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ እንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ ይልቁን ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ሆኖም ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው። ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፥ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነው። ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፥ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፥ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፥ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። በክርስቶስም ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በእርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደመጣ፥ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፥ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፥ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት። ከዚያም ግዛትን፥ ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፥ ያንጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የሚደመሰሰው የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ “ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሏልና፤ ነገር ግን፥ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፥ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል። ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክህት አረጋግጣለሁ። እንደ ሰው አስተሳሰብ በኤፌሶን ከአራዊት ጋር መታገሌ ምን ሊፈይድልኝ ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፤ ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና ይህንንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው። ነገር ግን አንዱ፥ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚወጡትስ በምን ዓይነት አካል ነው?” ብሎ ቢጠይቅ። አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዘር ቅንጣት እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዓይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንሰሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዓይነት ነው። እንዲሁም ሰማያውያን አካሎች አሉ፤ ምድራውያን አካሎች አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካሎች ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካሎች ክብር ሌላ ነው። የፀሓይ ክብር አንድ ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል። የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ አካላዊ ሰውነት ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። አካላዊ ሰውነት አለ፤ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፥ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን አካላዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደለበስን፥ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ! ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፥ ድንገት፥ በቅጽበተ ዐይን፥ መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፥ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መውጊያህስ የት አለ?”። የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ድካማችሁ በጌታ ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር በማወቅ፥ ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ።