1 ቆሮንቶስ 14:21-40
1 ቆሮንቶስ 14:21-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በኦሪትም፥ “ይህን ሕዝብ በሌሎች ቋንቋዎችና በሌላ አንደበት እናገራቸዋለሁ፤ እንዲሁም ሆኖ አይሰሙኝም ይላል እግዚአብሔር” ብሎአል። አሁንም ቋንቋ መናገር ለማያምኑ ሰዎች ለምልክት ነው፤ ለሚያምኑ ግን አይደለም፤ ትንቢትም ለሚያምኑ ነው እንጂ ለማያምኑ አይደለም። ሕዝቡ ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰቡ፥ ሁሉም በልዩ ልዩ ቋንቋ ቢናገሩ፥ አላዋቂዎች፥ ወይም የማያምኑ ቢመጡ አብደዋል ይሉአቸው የለምን? ሁሉም ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምኑ ወይም አላዋቂዎች ቢመጡ ሁሉ ይከራከሩአቸው የለምን? ሁሉስ ያሳፍሩአቸው የለምን? በልባቸው የደበቁትም ይገለጣል፤ ከዚህ በኋላ ያ የማያምነው ተመልሶ ይጸጸታል፤ በግንባሩም ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል፥ በእውነት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለም ይናገራል። አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ ሁላችሁ በምትሰበሰቡበት ጊዜ መዝሙር አላችሁ፤ ትምህርት አላችሁ፤ መግለጥ አላችሁ፤ በቋንቋ መናገር አላችሁ፤ መተርጐምም አላችሁ፤ ሁሉም ለሚታነጽበት ጥቅም አድርጉት። በቋንቋ የሚናገር ቢኖር ሁለት ሁለት፥ ወይም ቢበዛ ሦስት ሦስት እየሆኑ በተራ ይናገሩ፤ ሌላውም ይተርጕምለት። የሚተረጕም ከሌለ ግን በቤተ ክርስቲያን በቋንቋ የሚናገረው ዝም ይበል፤ በእግዚአብሔር መካከልና በእርሱ መካከል ይናገር። ነቢያትም ቃላቸው ለቤተ ክርስቲያን ይታወቅ ዘንድ ሁለት ሁለት፥ ወይም ሦስት ሦስት ሆነው ይናገሩ። ተቀምጦ ሳለ ምሥጢር የተገለጠለት ቢኖር ፊተኛው ዝም ይበል። ሁሉ እንዲማር፥ ሁሉም ደስ እንዲለው፥ እንዲጸናም ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁና። የነቢያት ሀብት ለነቢያት ይሰጣልና። በቅዱሳን ጉባኤ ሁሉ እንደሚደረግ፥ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና። ሴቶችም በቤተ ክርስቲያን ዝም ይበሉ፤ ሊታዘዙ እንጂ ሊናገሩ አልተፈቀደምና፤ ኦሪትም እንዲህ ብሎአልና። ለሴት በቤተ ክርስቲያን መናገር ክልክል ነው፤ ሊማሩ ከወደዱ ደግሞ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ። የእግዚአብሔር ቃል ከእናንተ ብቻ ወጥቶአልን? ወይስ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እናንተ ብቻ ደርሶአልን? ራሱን እንደ ነቢይ አድርጎ ወይም መንፈስ ቅዱስ እንዳደረበት አድርጎ የሚቈጥር ቢኖር፥ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነውና ይህን የጻፍሁላችሁን ይወቅ። ነገር ግን ይህን የማያውቅ ቢኖር እግዚአብሔርን አያውቀውም። አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ ትንቢትን ለመናገር ቅኑ፤ በቋንቋ የሚናገረውንም አትከልክሉት። ነገር ግን ሁሉን በአገባብና በሥርዐት አድርጉ፤
1 ቆሮንቶስ 14:21-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሕግም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፣ በባዕዳንም አንደበት፣ ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፤” ይላል ጌታ። ስለዚህ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፣ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፣ አብደዋል አይሉምን? ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፣ በሁሉ ይወቀሣል፤ በሁሉ ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፣ “እግዚአብሔር በርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን። በልሳን የሚናገር ቢኖር፣ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ ሌላው ደግሞ ይተርጕም፤ የሚተረጕም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ይመዝኑ። ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፣ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፣ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ። የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይታዘዛሉ፤ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው። ሴቶች በጉባኤ ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም፤ ሴቶች ለማወቅ የሚፈልጉት አንዳንድ ነገር ካለ፣ ባሎቻቸውን በቤት ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በጉባኤ መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው። የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከእናንተ ነውን? ወይስ የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነውን? ማንም ነቢይ ነኝ የሚል ወይም መንፈሳዊ ስጦታ አለኝ የሚል ቢኖር፣ ይህ የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ፤ ይህን የማያውቅ ቢሆን ግን እርሱም አይታወቅ። ስለዚህ፣ ወንድሞች ሆይ፤ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉም በአግባብና በሥርዐት ይሁን።
1 ቆሮንቶስ 14:21-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎችና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ፥ እንዲህም ቢሆን አይሰሙኝም ይላል ጌታ ተብሎ በሕግ ተጽፎአል። እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ፦ አብደዋል አይሉምን? ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረ ይገለጣል እንዲሁም፦ እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም፤ የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል። ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ። የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፤ እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው። ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና። ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና፥ ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ። ምን ነው? የእግዚአብሔር ቃል የወጣ ከእናንተ ነውን? ወይስ ወደ እናንተ ብቻ ደርሶአልን? ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።
1 ቆሮንቶስ 14:21-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህም፦ “ ‘በተለያዩ ቋንቋዎች በሚናገሩ ሰዎችና በባዕድ ሰዎች አፍ ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር” ተብሎ በሕግ ተጽፎአል። ስለዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ምልክት የሚሆነው ለማያምኑ ሰዎች ነው እንጂ ለሚያምኑ ሰዎች አይደለም፤ የትንቢት ቃል መናገር ግን ምልክት የሚሆነው ለሚያምኑት ሰዎች እንጂ ለማያምኑ ሰዎች አይደለም። ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ ክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች ቢናገርና የማያውቁ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢመጡ ተናጋሪዎችን “እነዚህ ሰዎች አብደዋል” አይሉምን? ነገር ግን እያንዳንዱ የትንቢት ቃል ቢናገርና የማያምን ወይም የማያውቅ ሰው ቢመጣ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይወቀሳል፤ እንዲሁም በሚሰማው ቃል ሁሉ ይፈረድበታል። በልቡ የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ በግንባሩም ተደፍቶ “በእርግጥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነው!” በማለት ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ምን ማድረግ ይገባል? ለጸሎት በምትሰበሰቡበት ጊዜ ከእናንተ አንዱ የመዘመር ስጦታ አለው፤ ሌላው የማስተማር ስጦታ አለው፤ አንዱ ስውር የሆነውን ነገር የመግለጥ ስጦታ አለው፤ አንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ስጦታ አለው፤ ሌላው የመተርጐም ስጦታ አለው። ታዲያ፥ ይህ ሁሉ ስጦታ ክርስቲያኖችን የሚያንጽ መሆን አለበት። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ቢኖሩ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በየተራ ይናገሩ፤ እነርሱ የሚናገሩትንም ሌላ ሰው ይተርጒም። የሚተረጒም ሰው ከሌለ ግን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩት በስብሰባ ላይ ዝም ይበሉ፤ ለራሳቸውና ለእግዚአብሔር ብቻ ይናገሩ። ትንቢት የሚናገሩ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ፤ ሌሎቹ ግን የተነገረውን አዳምጠው በጥንቃቄ ያመዛዝኑ። በስብሰባ ላይ ለሚገኝ ሌላ ሰው አንዳች ራእይ ቢገለጥለት፤ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። እያንዳንዱ እንዲማርና እንዲጽናና ሁላችሁም በየተራ የእግዚአብሔርን መልእክት መናገር ትችላላችሁ። የነቢያት የትንቢት መንፈስ ለነቢያት ይታዘዛል። በእግዚአብሔር ሕዝብ አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ዘንድ እንደሚደረገው እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። ሴቶች በጸሎት ስብሰባ ጊዜ ዝም ይበሉ፤ ሕግ እንደሚያዘው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም። አንዳንድ ነገርን ማወቅ ቢፈልጉ ባሎቻቸውን በቤታቸው ይጠይቁ፤ በጸሎት ስብሰባ ጊዜ ሴት እንድትናገር ተገቢ አይደለም። ለመሆኑ የእግዚአብሔር ቃል የመጣው ከእናንተ ነው? ወይስ የእግዚአብሔር ቃል የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነው? እኔ ነቢይ ነኝ ወይም እኔ መንፈሳዊ ስጦታ አለኝ የሚል ሰው ቢኖር ይህ የጻፍኩላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ። ይህን የማያውቅ ቢኖር እርሱም አይታወቅም። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገርንም አትከልክሉ። ነገር ግን ሁሉ ነገር በአግባብና በሥነ ሥርዓት ይሁን።
1 ቆሮንቶስ 14:21-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፥ በባዕዳንም አንደበት ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፥ ይላል ጌታ” ተብሎ በኦሪትም ተጽፎአል። በዚህ ዓይነት፥ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑት አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፥ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፥ አብደዋል አይሉምን? ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፥ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይወቀሳል፤ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፥ “እግዚአብሔር በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን። በልሳን የሚናገር ቢኖር፥ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ አንዱ ደግሞ ይተርጉም፤ የሚተረጉም ሰው ከሌለ ግን፥ በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ያመዛዝኑ። ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፥ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ። የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይታዘዛሉ፤ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ፥ የሁከት አምላክ አይደለም። በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው። ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም፤ ሴቶች ለማወቅ የሚፈልጉት አንዳንድ ነገር ካለ፥ ባሎቻቸውን በቤት ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በቤተ ክርስቲያን መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው። የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከእናንተ ነውን? ወይስ የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነውን? ማንም ነቢይ ነኝ የሚል ወይም መንፈሳዊ ሰው ነኝ የሚል ቢኖር፥ ይህ የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ፤ ይህን አላውቅም የሚል ቢኖር እርሱም አይታወቅ። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፤ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉም በአግባብና በሥርዓት ይሁን።