1 ቆሮንቶስ 14:13-19
1 ቆሮንቶስ 14:13-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በማያውቀው ቋንቋ የሚናገር ሰውም መተርጐም እንዲችል ይጸልይ። በማላውቀው ቋንቋ የምጸልይ ከሆንሁ ቃሌ ብቻ ይጸልያል፤ ልቤ ግን ባዶ ነው። እንግዲህ ምን አደርጋለሁ በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በማስተዋልም እማልዳለሁ፤ በመንፈሴ እዘምራለሁ፤ በማስተዋልም እዘምራለሁ። አንተ በመንፈስ ብታመሰግን፥ ያ የቆመው ያልተማረው በአንተ ምስጋና ላይ እንዴት አሜን ይላል? የምትናገረውንና የምትጸልየውን አያውቅምና። እነሆ፥ አንተስ መልካም ታመሰግናለህ፤ ነገር ግን ሌላው እንዴት ይታነጻል? እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ ከሁላችሁ ይልቅ እኔ በቋንቋዎች እናገራለሁና። ነገር ግን ሌሎችን አስተምር ዘንድ፥ በቋንቋ ከሚነገር ብዙ ቃል ይልቅ በቤተ ክርስቲያን በአእምሮዬ አምስት ቃላትን ልናገር እሻለሁ።
1 ቆሮንቶስ 14:13-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ በልሳን የሚናገር ሰው የሚናገረውን መተርጐም እንዲችል ይጸልይ። በልሳን በምጸልይበት ጊዜ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። ታዲያ፣ ምን ማድረግ አለብኝ? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲህማ ካልሆነ እግዚአብሔርን በመንፈስ በምታመሰግንበት ጊዜ፣ ለነገሩ እንግዳ የሆነ ሰው አንተ የምትናገረውን ካልተረዳ፣ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ፣ “አሜን” ሊል ይችላል? አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም። ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፣ ዐሥር ሺሕ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፣ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል።
1 ቆሮንቶስ 14:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ። በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም። ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።
1 ቆሮንቶስ 14:13-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገር ሰው የመተርጐም ችሎታ እንዲኖረው ይጸልይ። በተለያዩ ቋንቋዎች ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል እንጂ አእምሮዬ ፍሬአልባ ነው። ታዲያ፥ ምን ማድረግ ይገባኛል? በመንፈሴ እጸልያለሁ፤ በአእምሮዬም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈሴ እዘምራለሁ፤ በአእምሮዬም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲህማ ካልሆነ አንተ በመንፈስ እግዚአብሔርን ስታመሰግን፥ አንተ የምትለውን የማያውቅ እንግዳ ሰው ለምስጋና ጸሎትህ “አሜን” ሊል እንዴት ይችላል? እርግጥ አንተ ያቀረብከው የምስጋና ጸሎት በጥሩ ሁኔታ ነው፤ ነገር ግን ሌላው ሰው አይታነጽበትም። እኔ ከሁላችሁ ይበልጥ በተለያዩ ቋንቋዎች ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ነገር ግን በተለያዩ ቋንቋዎች በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ቃሎችን ከምናገር ይልቅ ሌሎችን ለማስተማር ስል በቤተ ክርስቲያን አምስት ቃላትን በሚታወቅ ቋንቋ በአእምሮዬ መናገር እወዳለሁ።
1 ቆሮንቶስ 14:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ በልሳን የሚናገር ሰው የሚናገረውን መተርጐም እንዲችል ይጸልይ። በልሳን በምጸልይበት ጊዜ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ፍሬ አልባ ነው። ታዲያ፥ ምን ማድረግ አለብኝ? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲህማ ካልሆነ፥ በመንፈስ በምትባርክበት ጊዜ፥ አንተ የምትለውን የማያውቅ እንግዳ ሰው ካልተረዳ፥ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ፥ “አሜን” ሊል ይችላል? አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም። ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፥ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፥ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል።