1 ዜና መዋዕል 29:3-17
1 ዜና መዋዕል 29:3-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቤት ስለ ወደድሁ፥ ለመቅደሱ ከሰበሰብሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና እነሆ፥ ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። የእግዚአብሔር ቤት ግንቦች ይለበጡበት ዘንድ ከኦፌር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህ መክሊትም ጥሩ ብር፤ በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በዚች ቀን በፈቃዱ አገልግሎቱን ለእግዚአብሔር የሚፈጽም ማን ነው?” የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ልጆች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በእግዚአብሔር ቤት ሥራ የተሾሙና የንጉሡ ግንበኞች በፈቃዳቸው አቀረቡ። ለእግዚአብሔርም ቤት ሥራ አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና ዐሥር ሺህ ዳሪክ፥ ዐሥር ሺህም መክሊት ብር፥ ዐሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ። የከበረ ዕንቍም ያላቸው ሰዎች ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በኢዩኤል እጅ ሰጡ። ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ታላቅ ደስታ ደስ አለው። ንጉሡ ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ አባታችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ቡሩክ ነህ። አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኀይል፥ ክብርም፥ ድልና ጽንዕ የአንተ ነው፤ ነገሥታቱና ሕዝቡ ሁሉ በፊትህ ይደነግጣሉ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፤ አቤቱ፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ የሥልጣን ሁሉ ጌታ ነህ፤ ኀይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ኀያል ነህ፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኀይልን ለመስጠት ዓለምን ሁሉ በእጅህ የያዝህ ነህ። አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ፥ እንገዛልሃለን፤ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን። ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው? አባቶቻችን ስደተኞች እንደ ነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፤ አትጸናምም። አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ለቅዱስ ስምህ ቤት እሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀሁት ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፤ ሁሉም የአንተ ነው። አምላኬ ሆይ፥ ልብን እንደምትመረምር፥ ጽድቅንም እንደምትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንዳቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ።
1 ዜና መዋዕል 29:3-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህም በቀር ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር የተነሣ፣ ለዚህ ለተቀደሰ ቤት ከዚህ በፊት ከሰጠሁት በተጨማሪ፣ ለዚሁ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የግል ሀብቴ የሆነውን ወርቅና ብር እሰጣለሁ፤ ይህም ሦስት ሺሕ መክሊት የኦፊር ወርቅና ሰባት ሺሕ መክሊት ንጹሕ ብር ለቤተ መቅደሱ የግድግዳ ግንብ ማስጌጫ እንዲሁም ለወርቁ ሥራ፣ ለብሩ ሥራ፣ በየእጅ ጥበብ ባለሙያ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሆን ነው። ታዲያ ዛሬ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመቀደስ ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው?” ከዚያም የቤተ ሰብ መሪዎች፣ የነገዱ የእስራኤል ሹማምት፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም በንጉሡ ሥራ ላይ የተመደቡ ሹማምት በፈቃዳቸው ሰጡ፤ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ የሰጡትም ዐምስት ሺሕ መክሊት ወርቅ፣ ዐሥር ሺሕ ዳሪክ ወርቅ፣ ዐሥር ሺሕ መክሊት ብር፣ ዐሥራ ስምንት ሺሕ መክሊት ናስ አንድ መቶ ሺሕ መክሊት ብረት ነው። የከበሩ ድንጋዮች ያለውም ሁሉ፣ በጌርሶናዊው በይሒኤል አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አስገባ። ስጦታው በገዛ ፈቃድና በፍጹም ልብ የቀረበ በመሆኑ፣ አለቆቹ ለእግዚአብሔር ስላደረጉት የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሕዝቡ ደስ አለው፤ ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ እጅግ ደስ አለው። ዳዊትም በመላው ጉባኤ ፊት እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል አመሰገነ፤ “የአባታችን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአንተ ምስጋና ይሁን። እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤ አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ። ባለጠግነትና ክብር የሚገኘው ከአንተ ነው፤ አንተም የሁሉ ገዥ ነህ፤ ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለሁሉም ብርታትን ለመስጠት፣ ብርታትና ኀይል በእጅህ ነው። አምላካችን ሆይ፤ አሁንም እናመሰግንሃለን፤ ለከበረው ስምህም ውዳሴ እናቀርባለን። “ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ቸርነት እናደርግ ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው? እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በፊትህ መጻተኞችና እንግዶች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤ ተስፋ ቢስም ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ለተቀደሰው ስምህ ቤተ መቅደስ እንሠራልህ ዘንድ ይህ በብዛት ያዘጋጀነው ሁሉ፣ ከእጅህ የተገኘና ሁሉም የአንተ ነው። አምላኬ ሆይ፤ ልብን እንደምትመረምርና ቅንነትን እንደምትወድድ ዐውቃለሁ፤ እኔም ይህን ሁሉ የሰጠሁት በበጎ ፈቃድና በቀና መንፈስ ነው። አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በበጎ ፈቃዱ እንዴት እንደ ሰጠ አይቻለሁ።
1 ዜና መዋዕል 29:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ፥ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። የቤቶቹ ግንብ ይለበጡበት ዘንድ ከኦፊር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህም መክሊት ጥሩ ብር፥ በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚቀድስ ማን ነው?” የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ነገዶች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በንጉሡም ሥራ ላይ የተሾሙት በፈቃዳቸው አቀረቡ። ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና ዐሥር ሺህ ዳሪክ፥ ዐሥር ሺህም መክሊት ብር፥ ዐሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ። ዕንቍም ያለው ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በይሒኤል እጅ ሰጠ። ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ በታላቅ ደስታ ደስ አለው። ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን ባረከ፤ ዳዊትም አለ “አቤቱ፥ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ! ከዘላለም እስከ ዘላለም ተባረክ። አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኀይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፤ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኀይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኀይልን ለመስጠት በእጅህ ነው። አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ! እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን። ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው? አባቶቻችንም ሁሉ እንደ ነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፤ አትጸናም። አቤቱ አምላካችን ሆይ! ለቅዱስ ስምህ ቤት እንሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፤ ሁሉም የአንተ ነው። አምላኬ ሆይ! ልብን እንድትመረምር፥ ቅንነትንም እንድትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንዳቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ።
1 ዜና መዋዕል 29:3-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእነዚህ ካዘጋጀኋቸው ነገሮች ሁሉ በላይ እኔ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ካለኝ ታላቅ ፍቅር የተነሣ ከራሴ ንብረት ብዙ ብርና ወርቅ ሰጥቼአለሁ፤ በዚህ መሠረት መቶ ሺህ ኪሎ የኦፊር ወርቅና ሁለት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ የሚሆን ንጹሕ ብር የቤተ መቅደሱን ግንቦች ለማስጌጥና፥ የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ለሚሠሩአቸው ዕቃዎች መሥሪያ የሚውል ሰጥቼአለሁ፤ ከእናንተስ መካከል በፈቃዱ ለእግዚአብሔር በልግሥና የሚሰጥ ሌላ ማን አለ?” ከዚህ በኋላ የጐሣ አለቆች፥ የየነገዱ መሪዎች፥ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች የመንግሥት ባለሥልጣኖች በፈቃዳቸው ስጦታ ሰጡ። ከመቶ ሰባ ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ ከሦስት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ በላይ የሚሆን ብር፥ ወደ ስድስት መቶ ኻያ ሺህ ኪሎ የሚጠጋ ነሐስና ከሦስት ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ኪሎ በላይ የሆነ ብረት በፈቃዳቸው ለመስጠት ወሰኑ፤ የከበረ ድንጋይ የነበራቸው ሁሉ የሌዋዊው የጌርሾን ጐሣ አባል የሆነው ይሒኤል ለሚያስተዳድረው ለቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት በስጦታ ስም አቀረቡ፤ ሕዝቡ በፈቃዳቸውና በሙሉ ልብ ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰጡ፤ እጅግ ብዙ ሀብት ገቢ በመሆኑም ደስ አላቸው፤ ንጉሥ ዳዊትም ከመጠን በላይ ደስ ተሰኘ። እዚያም በመላው ጉባኤ ፊት ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፦ “የቀድሞ አባታችን የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገንክ ሁን! አንተ ታላቅና ኀያል ነህ፤ በክብር፥ በውበትና በግርማም የተሞላህ ነህ፤ በሰማይና በምድር ያለው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤ አንተ ከሁሉ በላይ ከፍ ያልክና በሁሉም ላይ ሥልጣን ያለህ ንጉሥ ነህ፤ ብልጽግናና ክብር ሁሉ የሚገኘው ከአንተ ነው፤ አንተ ሁሉን ትገዛለህ፤ ኀይልና ብርታት ያንተ ናቸው፤ የወደድከውንም ታላቅና ብርቱ ማድረግ ይቻልሃል። አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ ክቡር ስምህንም እናወድሳለን። “ይህን ስጦታ በፈቃደኛነት መስጠት እንችል ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው? ሁሉ ነገር ከአንተ የተቀበልነው ስጦታ ነው፤ እነሆ የአንተ የነበረውንም መልሰን ሰጥተንሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ቀድሞ አባቶቻችን እኛም በአንተ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ነን፤ በምድር ላይ ያለው ዘመናችን ተስፋ የሌለው እንደ ጥላ ነው። አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ሀብት የሰበሰብነው ለቅዱስ ስምህ ክብር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ነው፤ ይሁን እንጂ ሁሉም የተገኘው ከአንተ ነው፤ ሁሉም የአንተ ነው፤ አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ፈትነህ፥ ታማኝ በሆነ ሕዝብ እንደምትደሰት ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም እኔ ይህን ሁሉ በፈቃዴ ለአንተ የሰጠሁት፥ በታማኝነትና በቅንነት ነው፤ ደግሞም እዚህ የተሰበሰበው ሕዝብህ ለአንተ ስጦታ በማቅረቡ፥ እጅግ መደሰቱን ተገንዝቤአለሁ፤
1 ዜና መዋዕል 29:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ፥ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። የቤቶቹ ግንብ እንዲለብጡበት ከኦፊር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህም መክሊት ጥሩ ብር፥ በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለጌታ የሚቀድስ ማን ነው?” የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ነገዶች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በንጉሡም ሥራ ላይ የተሾሙት በፈቃዳቸው አቀረቡ። ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና ዐሥር ሺህ ዳሪክ፥ ዐሥር ሺህም መክሊት ብር፥ ዐሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ። ዕንቁም ያለው ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በይሒኤል እጅ ሰጠ። ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለጌታ በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ፍጹም ደስ ተሰኘ። ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት ጌታን ባረከ፤ ዳዊትም እንዲህ አለ፦ “አቤቱ፥ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ! ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ተባረክ። አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን መስጠት በእጅህ ነው። አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ! እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን። ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል በፈቃደኝነት ልናቀርብልህ የምንችል እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው? አባቶቻችንም ሁሉ እንደ ነበሩ እኛ በፊትህ እንግዶችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፥ አይጸናም። አቤቱ አምላካችን ሆይ! ለቅዱስ ስምህ ቤት እንድንሠራ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፥ ሁሉም የአንተ ነው። አምላኬ ሆይ! ልብን እንደምትመረምር፥ ቅንነትንም እንደምትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱና ደስ ተሰኝቶ እንዳቀረበልህ አይቻለሁ።