የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 29

29
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የቀረበ ልዩ ልዩ ስጦታ
1ንጉሥ ዳዊት ለመላው ጉባኤ እንዲህ ሲል አስታወቀ፤ “እነሆ እግዚአብሔር የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ወጣትና የሥራ ልምድ የሌለው ነው፤ ይህ የሚሠራው ቤት፥ ቤተ መንግሥት ሳይሆን እግዚአብሔር አምላካችን የሚመለክበት ቤተ መቅደስ ስለ ሆነ መከናወን ያለበት ሥራ እጅግ ከባድ ነው። 2የምችለውን ያኽል፥ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ የሚሆኑትን ዕቃዎች ወርቅ ለወርቅ ሥራ፥ ብር ለብር ሥራ፥ ነሐስ ለነሐስ ሥራ፥ ብረት ለብረት ሥራ፥ እንጨት ለእንጨት ሥራ መርግድና የተለያዩ ቀለማት ያላቸው በፈርጥ የሚገቡ ድንጋዮች፥ የከበረ ድንጋይና በየዐይነቱ ብዙ ዕብነ በረድ አዘጋጅቼአለሁ። #1ዜ.መ. 22፥5። 3ከእነዚህ ካዘጋጀኋቸው ነገሮች ሁሉ በላይ እኔ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ካለኝ ታላቅ ፍቅር የተነሣ ከራሴ ንብረት ብዙ ብርና ወርቅ ሰጥቼአለሁ፤ 4በዚህ መሠረት መቶ ሺህ ኪሎ የኦፊር ወርቅና ሁለት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ የሚሆን ንጹሕ ብር የቤተ መቅደሱን ግንቦች ለማስጌጥና፥ 5የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ለሚሠሩአቸው ዕቃዎች መሥሪያ የሚውል ሰጥቼአለሁ፤ ከእናንተስ መካከል በፈቃዱ ለእግዚአብሔር በልግሥና የሚሰጥ ሌላ ማን አለ?”
6ከዚህ በኋላ የጐሣ አለቆች፥ የየነገዱ መሪዎች፥ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች የመንግሥት ባለሥልጣኖች በፈቃዳቸው ስጦታ ሰጡ። 7ከመቶ ሰባ ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ ከሦስት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ በላይ የሚሆን ብር፥ ወደ ስድስት መቶ ኻያ ሺህ ኪሎ የሚጠጋ ነሐስና ከሦስት ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ኪሎ በላይ የሆነ ብረት በፈቃዳቸው ለመስጠት ወሰኑ፤ 8የከበረ ድንጋይ የነበራቸው ሁሉ የሌዋዊው የጌርሾን ጐሣ አባል የሆነው ይሒኤል ለሚያስተዳድረው ለቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት በስጦታ ስም አቀረቡ፤ 9ሕዝቡ በፈቃዳቸውና በሙሉ ልብ ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰጡ፤ እጅግ ብዙ ሀብት ገቢ በመሆኑም ደስ አላቸው፤ ንጉሥ ዳዊትም ከመጠን በላይ ደስ ተሰኘ።
ዳዊት እግዚአብሔርን አመሰገነ
10እዚያም በመላው ጉባኤ ፊት ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፦ “የቀድሞ አባታችን የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገንክ ሁን! 11አንተ ታላቅና ኀያል ነህ፤ በክብር፥ በውበትና በግርማም የተሞላህ ነህ፤ በሰማይና በምድር ያለው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤ አንተ ከሁሉ በላይ ከፍ ያልክና በሁሉም ላይ ሥልጣን ያለህ ንጉሥ ነህ፤ #ማቴ. 6፥13። 12ብልጽግናና ክብር ሁሉ የሚገኘው ከአንተ ነው፤ አንተ ሁሉን ትገዛለህ፤ ኀይልና ብርታት ያንተ ናቸው፤ የወደድከውንም ታላቅና ብርቱ ማድረግ ይቻልሃል። 13አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ ክቡር ስምህንም እናወድሳለን።
14“ይህን ስጦታ በፈቃደኛነት መስጠት እንችል ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው? ሁሉ ነገር ከአንተ የተቀበልነው ስጦታ ነው፤ እነሆ የአንተ የነበረውንም መልሰን ሰጥተንሃል፤ 15እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ቀድሞ አባቶቻችን እኛም በአንተ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ነን፤ በምድር ላይ ያለው ዘመናችን ተስፋ የሌለው እንደ ጥላ ነው። 16አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ሀብት የሰበሰብነው ለቅዱስ ስምህ ክብር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ነው፤ ይሁን እንጂ ሁሉም የተገኘው ከአንተ ነው፤ ሁሉም የአንተ ነው፤ 17አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ፈትነህ፥ ታማኝ በሆነ ሕዝብ እንደምትደሰት ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም እኔ ይህን ሁሉ በፈቃዴ ለአንተ የሰጠሁት፥ በታማኝነትና በቅንነት ነው፤ ደግሞም እዚህ የተሰበሰበው ሕዝብህ ለአንተ ስጦታ በማቅረቡ፥ እጅግ መደሰቱን ተገንዝቤአለሁ፤ 18የቀድሞ አባቶቻችን የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ ታላቅ ፍቅር በሕዝብህ በእስራኤላውያን ልብ ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር አድርግ፤ ዘወትርም ለአንተ ታማኞች እንዲሆኑ አድርጋቸው፤ 19አንተ የምታዘውን፥ ትእዛዞችህን ደንቦችህንና ድንጋጌዎችህን ሁሉ እንዲፈጽምና ይህን ሁሉ ዝግጅት ያደረግኹለትን ቤተ መቅደስ እንዲሠራ ለልጄ ለሰሎሞን ከሙሉ ልብ የመነጨ ፈቃደኛነትን ስጠው።”
20ከዚህ በኋላ ዳዊት ሕዝቡን “አምላካችሁን እግዚአብሔርን አመስግኑ!” አለ፤ መላው ጉባኤም የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ወደ መሬት ለጥ ብለውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ለንጉሡም ክብር ሰጡ።
21በማግስቱ ብዙ እንስሶችን ዐርደው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡ እንዲመገቡ ሰጡአቸው፤ በተጨማሪም አንድ ሺህ ኰርማዎችን፥ አንድ ሺህ የበግ አውራዎችንና አንድ ሺህ የበግ ጥቦቶችን መሥዋዕት አድርገው በማረድ ሙሉ በሙሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠሉአቸው፤ የወይን ጠጅ መባም አቀረቡ፤ 22ስለዚህ በዚያን ቀን በእግዚአብሔር ፊት እየበሉና እየጠጡ እጅግ ደስ ተሰኙ።
ለሁለተኛ ጊዜም ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑን አረጋገጡ፤ በእግዚአብሔር ስም ቀብተው ንጉሣቸው አደረጉት፤ ሳዶቅንም ቀብተው ካህናቸው አደረጉት፤ 23በዚህ ዐይነት ሰሎሞን በአባቱ እግር ተተክቶ እግዚአብሔር ባጸናው ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ እርሱም ሁሉ ነገር የተሳካለት ንጉሥ ሆነ፤ መላውም የእስራኤል ሕዝብ ታዘዙለት፤ #1ነገ. 2፥12። 24ባለሥልጣኖችና ወታደሮች ሁሉ ሌሎቹ የዳዊት ልጆች እንኳ ሳይቀሩ ለንጉሥ ሰሎሞን ታማኝ ዜጎች እንደሚሆኑ ቃል ገቡ። 25እግዚአብሔር በአገሪቱ ሕዝብ ሁሉ ፊት ሰሎሞንን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከዚህ በፊት እስራኤልን ከገዛ ከማንኛውም ንጉሥ ይበልጥ የተከበረ እንዲሆንም አደረገው።
የዳዊት ዘመነ መንግሥት ታሪክ ባጭሩ
26የእሴይ ልጅ ዳዊት መላው እስራኤልን ገዛ፤ 27የግዛቱም ዘመን አርባ ዓመት ሲሆን በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌም ደግሞ ሠላሳ ሦስት ዓመት ገዛ፤ #2ሳሙ. 5፥4-5፤ 1ዜ.መ. 3፥4። 28ብዙ ሀብትና ክብር ካገኘም በኋላ በዕድሜ እጅግ ሸምግሎ ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሰሎሞን ነገሠ፤ 29ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለው የንጉሥ ዳዊት ታሪክ ሳሙኤል፥ ናታንና ጋድ ተብለው በሚጠሩት ሦስት ነቢያት በጻፉአቸው የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል፤ 30ዳዊት እንዴት እንዳስተዳደረ፥ ምን ያኽል ኀይል እንደ ነበረውና በእርሱ፥ በእስራኤልና በዙሪያ ባሉት ነገሥታት ላይ ስለ ደረሰባቸው ነገር ሁሉ በእነዚሁ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ