ትንቢተ ዘካርያስ 4
4
1ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ ከእንቅልፋ እንደሚነቃ ሰው አነቃኝ። 2እርሱም፦ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ እነሆ፥ ሁለንተናው ወርቅ የሆነውን መቅረዝ አየሁ፥ የዘይትም ማሰሮ በራሱ ላይ ነበረ፥ ሰባትም መብራቶች ነበሩበት፥ በራሱም ላይ ለነበሩት መብራቶች ሰባት ቧንቧዎች ነበሩአቸው። 3ሁለት የወይራ ዛፎች፥ አንዱ በማሰሮው በስተ ቀኝ አንዱም በስተ ግራው ሆነው፥ በአጠገቡ ነበሩ አልሁ። 4ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ፦ ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። 5ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውም መልአክ መልሶ፦ እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም፦ ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁ። 6መልሶም፦ ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፦ በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 7ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፥ ሰዎችም፦ ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል ብሎ ተናገረኝ።
8የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9የዘሩባቤል እጆች ይህን ቤት መሠረቱ፥ የእርሱም እጆች ይፈጽሙታል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። 10የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? እነዚህ ሰባቱ ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፥ እነዚህም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸው።
11እኔም መልሼ፦ በመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉ እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድር ናቸው? አልሁት። 12ሁለተኛም መልሼ፦ በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ ሆነው የወርቁን ዘይት የሚያፈስሱ እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድር ናቸው? አልሁት። 13-14እርሱም መልሶ፦ እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ አላውቅም አልሁት። እርሱም፦ በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ የተቀቡት እነዚህ ናቸው አለኝ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 4: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ