መኃልየ መኃልይ 5
5
1እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ወደ ገነቴ ገባሁ፥
ከርቤዬን ከሽቱዬ ጋር ለቀምሁ፥
እንጀራዬን ከማሬ ጋር በላሁ፥
የወይን ጠጄን ከወተቴ ጋር ጠጣሁ።
ባልንጀሮቼ ሆይ፥ ብሉ፥
ወዳጄ ሆይ፥ ጠጪ፥ እስክትረኪ ድረስ ጠጪ።
2እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፥
የውዴ ቃል ነው፥ እርሱም ደጁን ይመታል፥
እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥
በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ
ሞልቶበታልና ክፈችልኝ።
3ቀሚሴን አወለቅሁ፥ እንዴት እለብሰዋለሁ?
እግሬን ታጠብሁ፥ እንዴት አሳድፈዋለሁ?
4ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥
አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ።
5ለውዴ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፥
እጆቼ በደጁ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥
ጣቶቼ ፈሳሹን ከርቤ አንጠበጠቡ።
6ለውዴ ከፈትሁለት፥
ውዴ ግን ፈቀቅ ብሎ አልፎ ነበር።
ነፍሴ ከቃሉ የተነሣ ደነገጠች፥
ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፥
ጠራሁት፥ አልመለሰልኝም።
7ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፥
መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፥
ቅጥር ጠባቂዎችም የዓይነ ርግብ መሸፈኛዬን ወሰዱት።
8እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ አምላችኋለሁ፥
ውዴን ያገኛችሁት እንደ ሆነ፥
እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ንገሩት።
9አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥
ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው?
ይህን የሚያህል አምለሽናልና
ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው?
10ውዴ ነጭና ቀይ ነው፥
ከእልፍ የተመረጠ ነው።
11ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፥
ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቁራ ጥቁረትም ጥቁር ነው።
12ዓይኖቹ በሙሉ ፈሳሽ አጠገብ እንዳሉ
በወተት እንደ ታጠቡ በፈሳሽ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ
እንደ ርግቦች ናቸው።
13ጕንጩና ጕንጩ የሽቱ መደብ
እርከን እንዳለበት እንደ ሽቱ አትክልት ናቸው፥
ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥
የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠበጥባሉ።
14እጆቹ የቢረሌ ፈርጥ እንዳለበት እንደ ወርቅ ቀለበት ናቸው፥
አካሉ ብልሃተኛ እንደ ሠራው
በሰንፔር እንዳጌጠ እንደ ዝሆን ጥርስ ነው።
15እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ እንደ ተመሠረቱ
እንደ ዕብነ በረድ ምሰሶች ናቸው፥
መልኩ እንደ ሊባኖስና እንደ ዝግባ ዛፍ መልካም ነው።
16አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፥
እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥
ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው።
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 5: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ