መጽሐፈ ሩት 1:6-18

መጽሐፈ ሩት 1:6-18 አማ54

እርስዋም በሞዓብ ምድር ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘ እንጀራም እንደ ሰጣቸው ስለ ሰማች፥ ከሞዓብ ምድር ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች። እርስዋም ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከተቀመጠችበት ስፍራ ወጣች፤ ወደ ይሁዳም ምድር ሊመለሱ በመንገድ ሄዱ። ኑኃሚንም ምራቶችዋን “ሂዱ፤ ወደ እናቶቻችሁም ቤት ተመለሱ፤ በእኔና በሞቱት እንዳደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ቸርነት ያድርግላችሁ። እግዚአብሔር በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ፤” አለቻቸው። ሳመቻቸውም፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ። እነርሱም “ከእንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን፤” አሉአት። ኑኃሚንም አለች “ልጆቼ ሆይ! ተመለሱ፤ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ የሚሆኑ ልጆች በሆዴ አሉኝን? ልጆቼ ሆይ! ተመለሱ፤ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፤ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትቆያላችሁን? ስለ እነርሱስ ባል ማግባት ትተዋላችሁን? ልጆቼ ሆይ! እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ።” ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ዖርፋም አማትዋን ሳመች፤ ሩት ግን ተጠጋቻት። ኑኃሚንም “እነሆ፥ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ፤” አለቻት። ሩትም “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዘሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፤ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ እንዲሁም ይጨምርብኝ፤” አለች። ኑኃሚንም ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ እርስዋን ከመናገር ዝም አለች።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}