የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ አብድዩ 1:15-21

ትንቢተ አብድዩ 1:15-21 አማ54

የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና፥ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፥ አዎን ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ። ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይሆናሉ፥ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፥ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ። እግዚአብሔርም ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፥ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፥ ከዔሳውም ቤት ቅሬታ የለውም። የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቈላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፥ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፥ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል። ይህም የእስራኤል ልጆች የጭፍራቸው ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፥ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፥ መንግሥቱም ለእግዚአብሔር ይሆናል።