ኦሪት ዘኊልቊ 8:1-14

ኦሪት ዘኊልቊ 8:1-14 አማ54

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ መብራቶቹን ስትለኩስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው። አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ። መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ፤ እስከ አገዳውና እስከ አበቦቹ ድረስ ከተቀጠቀጠ ሥራ ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አደረገ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ሁሉ ምላጭ ያሳልፉ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ይታጠቡም። ወይፈንን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ። ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ። ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው። አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ። ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው። እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ።