የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥ የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካሁኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፦ እግዚአብሔር በእስራኤል ማኅበር ፊት የመታው ምድር፥ አጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባሪያዎችህ እንስሶች አሉን። እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ሆነ ይህን ምድር ለባሪያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን። ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች አላቸው፦ ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን? እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ? ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በሰደድኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ። ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ በሄዱ ጊዜ፥ ምድሪቱንም ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቁጣ ነደደ፥ እርሱም፦ በእውነት እግዚአብሔርን ፈጽመው ከተከተሉ ከእነዚህ ከቄኔዛዊው ከዮፎኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር፥ ከግብፅ የወጡት ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጥ ዘንድ የማልሁበትን ምድር አያዩም ብሎ ማለ። የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ጸና፥ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው። እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ቆማችኋል። እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ሕዝቡን በምድረ በዳ ደግሞ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ።
ኦሪት ዘኊልቊ 32 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኊልቊ 32:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos