የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍል 32:1-15

ዘኍል 32:1-15 NASV

እጅግ ብዙ የሆነ የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች የነበሯቸው የሮቤልና የጋድ ነገዶች የኢያዜርና የገለዓድ ምድር ለከብት ምቹ ስፍራዎች መሆናቸውን አዩ። ስለዚህ ወደ ሙሴ፣ ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ማኅበረ ሰቡ መሪዎች መጥተው እንዲህ አሉ፤ “አጣሮት፣ ዲቦን፣ ኢያዜር፣ ኒምራ፣ ሐሴቦን፣ ኤልያሊ፣ ሴባማ፣ ናባውና፣ ባያን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ሕዝብ ፊት እንዲሸነፍ ያደረገው ይህ ሁሉ ምድር ለከብት ምቹ ነው፤ እኛ አገልጋዮችህም ከብቶች አሉን። በፊትህ ሞገስ ያገኘን ከሆነ ይህ ምድር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በርስትነት ይሰጠን፤ ዮርዳኖስንም እንድንሻገር አታድርገን።” ሙሴም የጋድንና የሮቤልን ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወገኖቻችሁ ወደ ጦርነት ይሂዱ? እስራኤላውያን ተሻግረው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጧቸው ለምንድን ነው? አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። ወደ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ካዩ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ እስራኤላውያንን ተስፋ አስቈረጧቸው። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፤ ‘በፍጹም ልባቸው ስላልተከተሉኝ ከግብፅ ከወጡት፣ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች አንዳቸውም ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ልሰጥ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም፤ እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልባቸው ተከትለውታልና፣ ከቄኔዛዊው ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር አንዳቸውም አያዩዋትም።’ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ቍጣ በእስራኤል ላይ ስለ ነደደ፣ በፊቱ ክፉ ነገር ያደረገው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው። “እናንት የኀጢአተኞች ልጆች ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቈጣ ታደርጋላችሁ። እርሱን ከመከተል ብትመለሱ አሁንም ይህን ሁሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ይተወዋል፤ ለሚደርስበትም ጥፋት ምክንያቱ እናንተው ትሆናላችሁ።”