ኦሪት ዘኊልቊ 21:1-7

ኦሪት ዘኊልቊ 21:1-7 አማ54

በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ። እስራኤልም ለእግዚአብሔር፦ እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት። ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ። ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ፦ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፦ በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት።