ዘኍልቍ 21:1-7

ዘኍልቍ 21:1-7 NASV

በኔጌብ ይኖር የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ እስራኤል በአታሪም መንገድ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ። በዚያ ጊዜ እስራኤል፣ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ከሰጠኸን ከተሞቻቸውን ፈጽሞ እንደመስሳለን” ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልመና ሰምቶ ከነዓናውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰዎቹንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ከዚህ የተነሣም ስፍራው ሖርማ ተባለ። እስራኤላውያን በኤዶም ዞረው ለመሄድ ስላሰቡ ከሖር ተራራ ተነሥተው ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ ተጓዙ፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በመንገድ ሳለ ትዕግሥቱ ዐለቀ፤ በእግዚአብሔርና በሙሴም ላይ ተነሥተው፣ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብጽ ያወጣችሁን ለምንድን ነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ! ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” ሲሉ ተናገሩ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር መርዘኛ እባቦች ሰደደባቸው፤ ሕዝቡን ነደፉ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሞቱ። ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥቶ፣ “በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ በመናገራችን በድለናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አለ፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ።