የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 11:16-30

ኦሪት ዘኊልቊ 11:16-30 አማ54

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፥ ወደ መገናኛውም ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው። እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም እነጋገርሃልሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። ሕዝቡንም በላቸው፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ። አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ። ሙሴም፦ እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ አልህ። እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ ያጠግባቸው ዘንድ ይሰበሰብላቸዋልን? አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው። ሙሴም ወጣ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔር በደመናው ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋል ግን አልተናገሩም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐበዝ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው። ሙሴም፦ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን? አለው። ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}