የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 11

11
1ሕዝቡም ክፉ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ነደደች፥ የሰፈሩንም ዳር በላች። 2ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እሳቲቱም ጠፋች። 3የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ስለነደደች የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው። 4በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? 5በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤ 6አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም አሉ። 7መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር። 8ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ። 9ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በላዩ ይወርድ ነበር። 10ሙሴም ሕዝቡ በወገኖቻቸው፥ ሰው ሁሉ በድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም ተቈጣ። 11ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፦ ለምን በባሪያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? 12አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ፦ ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቅፍ በብብትህ እቀፋቸው የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወለድሁትንስ? 13በፊቴ ያለቅሳሉና፦ የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት እወስዳለሁ? 14እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም። 15እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ። 16እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፥ ወደ መገናኛውም ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው። 17እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም እነጋገርሃልሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። 18ሕዝቡንም በላቸው፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ። 19አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤ 20ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ። 21ሙሴም፦ እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ አልህ። 22እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ ያጠግባቸው ዘንድ ይሰበሰብላቸዋልን? አለ። 23እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው። 24ሙሴም ወጣ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። 25እግዚአብሔር በደመናው ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋል ግን አልተናገሩም። 26ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። 27አንድ ጐበዝ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ ብሎ ለሙሴ ነገረው። 28ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው። 29ሙሴም፦ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን? አለው። 30ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ። 31ነፋስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ ላይ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ነበረ። 32በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በነጋውም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ አሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። 33ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፥ የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ። 34የጐመጁ ሕዝብ በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም የምኞት መቃብር ተብሎ ተጠራ። 35ሕዝቡም ከምኞት መቃብር ወደ ሐጼሮት ተጓዙ በሐጼሮትም ተቀመጡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}