የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 6

6
1እንዲህም ሆነ፥ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንበላጥና ጦብያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፥ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር። 2ሰንባላጥና ጌሳም፦ መጥተህ በኦኖ ቆላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ ብለው ላኩብኝ፥ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ያስቡ ነበር። 3እኔም፦ ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም፥ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ስለ ምን ሥራው ይታጐላል? ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው። 4እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፥ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው። 5ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ጊዜ ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፥ 6በእጁም ውስጥ፦ አንተና አይሁድ ዓመፅ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል። 7ደግሞም፦ ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፥ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፥ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር የሚል ክፍት ደብዳቤ ነበረ። 8እኔም፦ አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት። 9እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም፦ እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ፥ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ።
10እኔም ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ቤት ገባሁ፥ እርሱም ተዘግቶ ነበርና፦ በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ የመቅደሱንም ደጆች እንዝጋ፥ እነርሱ መጥተው ይገድሉሃልና፥ በሌሊትም ይገድሉህ ዘንድ ይመጣሉና አለ። 11እኔም፦ እንደ እኔ ያለ ሰው የሸሸና፥ ነፍሱንስ ያድን ዘንድ ወደ መቅደስ የገባ ማን ነው? እኔስ አልገባም አልሁት። 12እግዚአብሔርም ልኮት እንዳልነበረ፥ በእኔ ላይ ግን ትንቢት እንደተናገረ፥ እነሆ፥ አወቅሁ፥ ጦብያና ሰንበላጥም ገዝተውት ነበር። 13ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ ዘንድ ተገዝቶ ነበር። 14አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ሥራቸው ጦብያንና ሰንባላጥን ያስፈራሩኝም ዘንድ የወደዱትን ነቢይቱን ኖዓድያን የቀሩትንም ነቢያት አስብ።
15ቅጥሩም በኤሉል ወር በሀያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጨረሰ። 16ጠላቶቻችንም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ በራሳቸውም አሳብ እጅግ ተዋረዱ፥ ይህም ሥራ በእግዚአብሔር እንደ ተደረገ አወቁ። 17-18ጦብያም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማች ስለ ነበረ፥ ልጁም ይሆሐናን የቤራክያን ልጅ የሜሱላምን ሴት ልጅ ስላገባ፥ በይሁዳ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ተማምለው ነበርና በዚያ ወራት ብዙ የይሁዳ አለቆች ወደ ጦብያ ደብዳቤዎች ይልኩ ነበር፥ የጦብያም ደብዳቤዎች ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር። 19ደግሞም በፊቴ ስለ እርሱ መልካም ይናገሩ ነበር፥ ቃሌንም ያወሩለት ነበር፥ ጦብያም ሊያስፈራራኝ ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ