መጽሐፈ ነህምያ 13
13
1በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ፥ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ። 2የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው፥ ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት መለሰው። 3ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ድብልቁን ሕዝብ ሁሉ ከእስራኤል ለዩ።
4ከዚህም አስቀድሞ በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሾሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሴብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ፥ 5ለሌዋውያን፥ ለመዘምራን፥ ለበረኞቹ እንደ ሕጉ የተሰጣቸውን የእህሉን ቁርባንና ዕጣኑን፥ ዕቃዎቹንም፥ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት፥ ለካህናቱም የሆነውን የማንሣት ቁርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር። 6እኔ ግን በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበርና በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም። ከጥቂት ዘመንም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ለመንሁ፥ 7ወደ ኢየሩሳሌምም መጣሁ፥ ኤልያሴብም በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ። 8እጅግም አስከፋኝ፥ የጦብያንም የቤቱን ዕቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጪ ጣልሁ። 9ጓዳዎቹንም እንዲያነጹ አዘዝሁ፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃዎች የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ።
10ለሌዋውያንም እድል ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፥ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደ ሄዱ ተመለከትሁ። 11እኔም፦ የእግዚአብሔር ቤት ስለ ምን ተተወ? ብዬ ከአለቆቹ ጋር ተከራከርሁ። ሰበሰብኋቸውም፥ በየስፍራቸውም አቆምኋቸው። 12ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ። 13በዕቃ ቤቶችም ላይ ካህኑን ሰሌምያን፥ ጸሐፊውንም ሳዶቅን፥ ከሌዋውያኑም ፈዳያን ሾምሁ፥ ከእነርሱም ጋር የመታንያ ልጅ የዘኩር ልጅ ሐናን ነበረ፥ እነርሱም የታመኑ ሆነው ተገኙ፥ ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው ማከፋፈል ነበረ። 14አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ፥ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ።
15በዚያም ወራት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጥመቂያን የሚረግጡትን፥ ነዶም የሚከመሩትን፥ የወይኑን ጠጅና የወይኑን ዘለላ በለሱንም ልዩ ልዩም ዓይነት ሸክም በአህዮች ላይ የሚጭኑትን፥ በሰንበትም ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያስገቡትን አየሁ፥ ገበያ ባደረጉበትም ቀን አስመሰከርሁባቸው። 16ደግሞም በእርስዋ የተቀመጡ የጢሮስ ሰዎች ነበሩ፥ እነርሱም ዓሣዎችን ልዩ ልዩም ዓይነት ሸቀጥ አምጥተው በሰንበት ቀን በኢየሩሳሌም ለይሁዳ ልጆች ይሸጡ ነበር። 17ከይሁዳም ታላላቆች ጋር ተከራከርሁና፦ ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድር ነው? የሰንበትንስ ቀን ታረክሳላችሁን? 18አባቶቻችሁ እንደዚህ አድርገው አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ በእኛና በዚህ ከተማ ላይ አምጥቶ አልነበረምን? እናንተም ሰንበትን በማርከሳችሁ በእስራኤል ላይ መዓትን ትጨምራላችሁ አልኋቸው።
19ከዚህ በኋላ ከሰንበት በፊት በኢየሩሳሌም በሮች ድንግዝግዝታ በሆነ ጊዜ በሮችዋ እንዲዘጉ፥ ሰንበትም እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ። በሰንበትም ቀን ሸክም እንዳይገባ ከብላቴኖቼ በአያሌዎቹ በሮችዋን አስጠበቅሁ። 20ሁሉም አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በኢየሩሳሌም ውጭ አድረው ገበያ አድርገው ነበር። 21እኔም አስመሰከርሁባቸውና፦ በቅጥሩ ውጭ ለምን ታድራላችሁ? እንደ ገና ብታደርጉት እጆቼን አነሣባችኋለሁ አልኋቸው። ከዚያም ወዲያ በሰንበት ቀን እንደ ገና አልመጡም። 22ሌዋውያኑንም ራሳቸውን እንዲያነጹ፥ መጥተውም በሮቹን እንዲጠብቁ፥ የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ ነገርኋቸው። አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ራራልኝ።
23ደግሞም በዚያ ወራት የአዛጦንና የአሞንን የሞዓብንም ሴቶች ያገቡትን አይሁድ አየሁ። 24ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ በአዛጦን ቋንቋ ይናገሩ ነበር፥ በአይሁድም ቋንቋ መናገር አያውቁም ነበር። 25ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ፥ ረገምኋቸውም፥ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታሁ፥ ጠጉራቸውንም ነጨሁ፥ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው፦ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተና ለልጆቻችሁ አትውሰዱ። 26የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በዚህ ነገር ኃጢአት አድርጎ የለምን? በብዙ አሕዛብም መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፥ በአምላኩም ዘንድ የተወደደ ነበረ፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ አንግሦት ነበር፥ እርሱንም እንኳ እንግዶች ሴቶች አሳቱት። 27በውኑ ይህን ሁሉ ታላቅ ክፋት እንሠራ፥ እንግዶችንም ሴቶች በማግባት አምላካችንን እንበድል ዘንድ እናንተን እንስማ?
28ከዋነኛውም ካህን ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ ለሖሮናዊው ለሰንበላጥ አማች ነበረ፥ ከእኔም ዘንድ አባረርሁት። 29አምላኬ ሆይ፥ ክህነትን የክህነትንና የሌዋውያንንም ቃል ኪዳን ስላፈረሱ አስባቸው።
30ከእንግዳ ነገርም ሁሉ አነጻኋቸው፥ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው በየሰሞናቸው፥ 31በየጊዜውም ለእንጨት ቁርባን ለበኩራቱም ሥርዓት አደረግሁ። አምላኬ ሆይ፥ በመልካም አስበኝ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 13: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ