የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 15:1-20

የማርቆስ ወንጌል 15:1-20 አማ54

ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም፦ አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ አንተ አልህ ብሎ መለሰለት። የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። ጲላጦስም ደግሞ፦ አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። ጲላጦስም፦ የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤ የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ፦ እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው። እነርሱም ዳግመኛ፦ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፦ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን፦ ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ። ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች