የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 15:1-20

ማርቆስ 15:1-20 NASV

ወዲያውም በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፣ ከጸሐፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋራ ከተማከሩ በኋላ፣ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም፣ “አንተው አልኸው፣” በማለት መለሰለት። የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። ጲላጦስም፣ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ፤ በብዙ ነገር ከስሰውሃል” ሲል እንደ ገና ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰም፤ ጲላጦስ ተገረመ። በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋራ የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ለመኑት። ጲላጦስም፣ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ። ጲላጦስም እንደ ገና፣ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም እንደ ገና፣ “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ” አላቸው። እነርሱ ግን፣ “ስቀለው!” እያሉ የባሰ ጮኹ። ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሠኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹ ፕራይቶሪዮን ወደ ተባለ ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ። ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት። ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት፤ ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች