የማርቆስ ወንጌል 14:3-16

የማርቆስ ወንጌል 14:3-16 አማ54

እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። አንዳንዶችም፦ ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል። ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ።