ትንቢተ ሚክያስ 4
4
1በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። 2ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፥ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ። 3በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፥ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፥ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። 4የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም። 5ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፥ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።
6በዚያ ቀን አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የባከነችውንና ያስጨነቅኋትንም አከማቻለሁ፥ 7አንካሳይቱንም ለቅሬታ፥ ወደ ሩቅም የተጣለችውን ለብርቱ ሕዝብ አደርጋታለሁ፥ ከዚያም ወዲያ እስከ ዘላለም ድረስ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል። 8አንተም የመንጋ ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ አምባ፥ ወደ አንተ ትመጣለች፥ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ትደርሳለች።
9አሁንስ ለምን ትጮኺአለሽ? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የደረሰብሽ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ ስለ ጠፋብሽ ነውን? 10የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጠሽ ውለጂ፥ አሁን ከከተማ ትወጫለሽና፥ በሜዳም ትቀመጫለሽ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ፥ በዚያም ያድንሻል፥ በዚያም እግዚአብሔር ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል።
11አሁንም፦ ርኩስ ትሁን፥ ዓይናችንም በጽዮን ላይ ይይ የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል። 12ነገር ግን የእግዚአብሔርን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፥ እንደ ነዶ ወደ አውድማ አከማችቶአቸዋልና። 13የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ጥፍርሽንም ናስ አደርጋለሁና ተነሺ አሂጂ፥ ብዙ አሕዛብንም ታደቅቂአለሽ፥ ትርፋቸውንም ለእግዚአብሔር፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትቀድሻለሽ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 4: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ